ምንም እንኳን ጦርነቱ ተጠናክሮ ቢቀጥልም ተስፋ መቁረጥ እንደማይገባ አባ ፓቶን አስገነዘቡ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የቅድስት ሀገር ተንከባካቢ ካህኑ ከናቲቪቲ ቤተ መቅደስ ወይም ባዚሊካ አጠገብ በሚገኘው በቅድስት ካትሪን ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያውን የገና ወር እሑድ ቅዳሴን ለመምራት በየዓመቱ የሚከወነውን ወደ ቤተልሔም የመግባት ትሁፊታዊ ጉዞ አድርገዋል።
አባ ፍራንቸስኮ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ተወለደባት የፍልስጤማዊያን ከተማ ወደ ሆነችው ቤተልሄም ቅዳሜ ህዳር 21 ቀን 2017 ዓ.ም. መጀመሪያ በእስራኤል ፖሊሶች ከዚያም በፍልስጤም ፖሊሶች ታጅበው ዓመታዊውን ትሁፊታዊ የክብር ጉዞ በማድረግ የገቡ ሲሆን፥ በወቅቱም በአካባቢው ባለስልጣናት እና ነዋሪዎች ሞቅ ያለ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
የጦርነት እና የኢኮኖሚ ቀውስ አስከፊ ድባብ የሰፈነባት የቤተልሔም ከተማ
በጦርነት እና በኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ሆነው ሁለተኛውን የገና በዓል ለማክበር እየተዘጋጁ ላሉት የቤተልሄም ከተማ ህዝቦች ይህ ጊዜ በጣም አሳዛኝ ወቅት እንደሆነ የተናገሩት ካህኑ፥ በጎረጎሳዊያኑ አቆጣጠር በ 2023 በሃማስ እና በእስራኤል መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበትን የ ‘ናቲቪቲ ባዝሊካ’ን ለመጎብኘት በሚመጡ መፈሳዊ ነጋዲያን ትጨናነቅ የነበረቿ ከተማ ባዶ እንደሆነች፥ በዚህም ምክንያት የአብዛኛው ህዝብ የመተዳደሪያው ምንጭ የነበረው ቱሪዝም በማሽቆልቆሉ የአካባቢው የንግድ ተቋማት መዘጋታቸው፥ እንዲሁም ነዋሪዎቹ የድንበር አጥሮችን ተሻግረው እየሩሳሌም ውስጥ ለመስራት ስላልቻሉ ህዝቡ ለመኖር የሚያስችለው ምንም አይነት ገቢ እንደሌለው ገልጸዋል።
በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ እና የእስራኤላውያን ታጋቾችን ለማስለቀቅ ሲደረግ የነበረውን ተከታታይ የድርድር ጥረቶችን እንደገና ለማስጀመር በቅርብ ጊዜ የተደረጉ አዳዲስ ጥረቶች በቅድስት ሀገር በጦርነት ውስጥ ሆኖ የሚከበር የመጨረሻው የገና በዓል ይሆናል የሚል የተስፋ ጭላንጭል ቢተውም በቤተልሔም ያለው ድባብ አስፈሪ እንደሆነ ተገልጿል።
ተስፋን ጠብቆ ማቆየት
አባ ፓቶን ይህንን ተስፋ ቅዳሜ እና እሁድ በተካሄደው የቅዳሴ ሥነ ስርዓት ላይ በድጋሚ የገለጹ ሲሆን፥ ቅዳሜ ምሽት በተካሄደ የጸሎት ሥነ ስርዓት ላይ “በተለይ ዓለም ከእኛ የራቀ እና ተስፋችንን ሊነጥቀን መስሎ ሲታየን በፍፁም ተስፋ መቁረጥ አይገባም” በማለት ቤተልሄም የሚገኘውን ምዕመን አበረታተዋል።
ተንከባካቢ ካህኑ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የጎረጎሳዊያኑን የ 2025 የተስፋ ኢዮቤልዩ ዓመት ሲከፍቱ ለህዝቡ ባስተላለፉት መልዕክት “ተስፋን እንዲጠብቁ እና እንዲያስፋፉ እንዲሁም የተስፋ ተጓዦች እንዲሆኑ” አሳስበው እንደነበር አስታውሰው፥ “ክፋት፣ ተስፋ መቁረጥ እና ሕመም በበዛበት፣ እንዲሁም በሚያስጨንቀን እና የሚያቆስለን በዚህ አሰቃቂ ጦርነት ፊት ዓይናችንን ከፍ አድርገን ወደ አምላካችን ከመመልከት ውጭ ሌላ አማራጭ የለንም” ብለዋል።
አባ ፓቶን እሁድ ዕለት በተካሄደው ሥርዓተ ቅዳሴ ላይ ለተገኙት ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ ምዕመን ባሰሙት ቃለ ምዕዳን “ኢየሱስ እንደተናገረው መመልከት እና መጸለይን መማር አለብን” ሲሉ በድጋሚ አሳስበዋል።
በጋዛ ደብር ውስጥ የሚገኝ የአንድ ወጣት ምስክርነት
አባ ፓቶን በኢየሩሳሌም የቅድስት ሀገር ተንከባካቢ እና የፓትርያርኩ ረዳት ከሆኑት አባ ኢብራሂም ፋልታስ ጋር ባሳረጉት ስርዓተ ቅዳሴ ወቅት በጋዛ በሚገኘው ቅዱስ ቤተሰብ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ከተጠለሉት በመቶዎች ከሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን መካከል አንዱ የሆነውን የወጣት ሱሃይል አቦ ዳውድን ምስክርነት አንስተው የነበረ ሲሆን፥ ወጣቱ ለቫቲካኑ ‘ላ ኦዘርቫቶሬ ሮማኖ’ ጋዜጣ “ከጋዛ የተፃፈ” በሚል ርዕስ በፃፈው መልዕክት ላይ ‘እጅግ አስፈሪ በሆነው የቦምብ ፍንዳታ ታጅቦ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር እንደሚጸልይ፥ ይሄንንም ሲያደርጉ ህይወቱ በእግዚአብሔር እጅ እንዳለ ስለሚሰማው ከፍተኛ የደኅንነት ስሜት እንደሚሰማው’ ገልጿል።
ወጣቱ በማከልም ከጥቂት ቀናት በፊት አያቱ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን የፃፈ ሲሆን፥ አባ ፓቶን ይሄንን አስመልክተው ሲገልጹ፥ “ወጣቱ እነዚህን ስሜቶች የገለጸበት ቃላት በሚያሳዝኑ ሁኔታ ሳይሆን በአመስጋኝነት እና በተስፋ የተሞሉ ነበሩ፥ ምክንያቱም አያቱ የሞቱት እንደ ክርስቲያን ነው” በማለት አብራርተዋል።
ከዚህም ባለፈ ካህኑ የወጣቱን መልእክት በከፊል በመጥቀስ፣ “ለሰጠን ስጦታዎች እና ጸጋዎች እግዚአብሔርን በየዕለቱ እናመሰግነዋለን፥ ለሀገራችን እና ለዓለም ሰላም እና ደህንነት በየእለቱ እንጸልያለን፥ ጦርነት ውስጥ ብንሆንም በቅርቡ እንደሚያበቃ ተስፋ አለን፥ እናም የሚመጡት ቀናት የተሻሉ ይሆናሉ” ብሎ የፃፈውን አስታውሰዋል።
“ይህ ሁል ጊዜ ንቁ የመሆን እና የአመስጋኝነት ጸሎት ተስፋን ለማቆየት አስፈላጊ ነው” ያሉት የቅድስት ሃገር ተንከባካቢ ካህን በመጨረሻም፥ “ዓይናችሁን ከመንግሥተ ሰማያት፣ ከአባቱ ዘንድ ወደ ሚመጣው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከፍ አርጉ፣ ክፋት በሕይወታችን ላይ እንደ ማዕበል ሲመጣ ተስፋ አትቁረጡ” በማለት ደምድመዋል።