ፈልግ

በኤርቢል ከተማ የሚገኘው የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ በኤርቢል ከተማ የሚገኘው የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ 

በኢራቋ ኤርቢል ከተማ የሚገኘው ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የገናን በዓል በጋራ አከበሩ

በኢራቅ የኩርዲስታን ክልል ውስጥ ያለውን ልዩ የሆነ አብሮ የመኖር እና በልዩነት ውስጥ ተከባብሮ የመኖር ተምሳሌትነት በሚያሳይ መልኩ በኤርቢል ከተማ በሚገኘው የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚማሩ የተለያየ እምነት ያላቸው ተማሪዎች በየዓመቱ እንደሚያደርጉት የዘንድሮውን የብርሃነ ልደት በዓል በጋራ ለማክበር ተሰባስበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በኢራቅ የኩርዲስታን ክልል ዋና ከተማ በሆነችው ኤርቢል የሚገኘው የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ መሰረት ያላቸው ተማሪዎች የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ልደት በጋራ አክብረዋል።

ዩኒቨርሲቲው የበአሉን አከባበር አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ እንደሚያመለክተው እንዲህ አይነቱ ክስተት ተቋሙ ሁሉንም ሰው ያለ አድልዎ የሚያቅፍ፣ የትምህርት እና ሰብአዊ ተቋም የመሆን ግቡን ያሳያል ብሏል።

ዓመታዊ ልማድ
በግቢው ውስጥ በየዓመቱ የሚከበረው የብርሃነ ልደቱ ክብረ በዓል ልማዳዊ የአንድነት ምልክት እየሆነ የመጣ ሲሆን፥ በበዓሉ ዕለትም ሙስሊሞች ከክርስቲያኖች ጋር በመሆን የገና ዛፍን ማስጌጥን ጨምሮ በወቅቱ በሚደረጉ ሁሉም ዝግጅቶች ላይ ይሳተፋሉ።

ይህ ተማሪዎቹ እርስ በእርስ በመገናኘት እና ሃሳብ በመለዋወጥ ጥሩ ጊዜ የሚያሳልፉበት ትእይንት በተማሪዎቹ ዘንድ ተናፋቂ እየሆነ በመምጣቱ ክብረ በዓሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ጉጉት የሚጠበቅ ልማዳዊ ዓመታዊ ክብረ በዓል ሆኗል።

በጋራ ማክበር
ከፍተኛ ተቋሙ “የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ” የሚል ስያሜ ቢኖረውም፥ በዚህ ዓመት ከተለያዩ ሃይማኖቶች የተውጣጡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች በበዓሉ ላይ የተገኙ ሲሆን፥ ይህም የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች እና ዩኒቨርሲቲው በአካባቢው ላይ ያገኙት እምነት እና ተቀባይነት እየጨመረ መምጣቱን ያሳያል ተብሏል።

በዚህ የትምህርት ዘመን ዩኒቨርሲቲው የተለያየ የሀይማኖት እና የባህል ዳራ ያላቸው 750 ተማሪዎችን በመቀበል እያስተናገደ የሚገኝ ሲሆን፥ ይህም ተቋሙ ከተመሠረተ ወዲህ ከፍተኛው ቁጥር እንደሆነ ተገልጿል።

ማንም የተገለለ የለም
ዛሬ የአካዳሚክ ልህቀት፣ የባህል ብዝሃነት እና በተለያዩ ሀይማኖቶች መሃል ተከባብሮ አብሮ የመኖር ምልክት የሆነው የካቶሊክ ዩኒቨርስቲ በኤርቢል ከተማ የተመሰረተው በጣሊያን ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ በተደረገ ድጋፍ ነው።

ከተለያዩ ሀይማኖቶች የተውጣጡ በርካታ ምሁራን የሚገኙበት ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ባህላዊ እና ሀይማኖታዊ እሳቤ ያላቸው ሰዎች በጋራ የሚኖሩበት አካዳሚያዊ አካባቢን ፈጥሯል።

ከዚህም በላይ የበርካታ መንግሥታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ዋና መዳረሻ፣ እንዲሁም የተለያዩ የህክምና፣ ሳይንሳዊ እና ትምህርታዊ ኮንፈረንሶች የሚካሄዱበት ተቋም ሆኗል። 
 

25 December 2024, 13:33