ፈልግ

በታይላንድ የሚገኙ በርካታ የቡዳ እምነት መሪዎች ካርዲናል አዩሶን ለማስታወስ ተሰብሰበዋል በታይላንድ የሚገኙ በርካታ የቡዳ እምነት መሪዎች ካርዲናል አዩሶን ለማስታወስ ተሰብሰበዋል  

የካቶሊክ እና የቡዳ እምነት መሪዎች ብፁዕ ካርዲናል አዩሶን ለማስታወስ በባንኮክ መሰብሰባቸው ተገለጸ

በታይላንድ የሚገኙ በርካታ የቡዳ እና የካቶሊክ እምነት መሪዎች በቅርቡ ያረፉትን፣ በጳጳሳዊ ምክር ቤት፣ የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት የነበሩትን ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል ኣዩሶ ለማስታወስ በባንኮክ በሚገኘው ታዋቂው የቡዳ እምነት ቤተ መቅደስ ውስጥ ተሰብስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በጳጳሳዊ ምክር ቤት፣ የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት የነበሩትን ሟቹን ብፁዕ ካርዲናል ሚጌል አንጄል አዩሶን ለማስታወስ በባንኮክ በሚገኝ ታዋቂ የቡዳ እምነት ቤተ መቅደስ ውስጥ እሑድ ኅዳር 1/2017 ዓ. ም. በተዘጋጀው ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተዋል።

ይህ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ክስተት በካቶሊክ እና በቡዳ ማኅበረሰቦች መካከል ያለውን ጥልቅ ትስስር በታይላንድ አጉልቶ ያሳየ ሲሆን፥ ግንኙነቱ ብፁዕ ካርዲናል ሚጌል አንጄል አዩሶ በሃይማኖቶች መካከል መግባባትን ለማጎልበት ያደረጉትን ያላሰለሰ ጥረት ማጠናከሩ ታውቋል።

የዋት ፍራ ቼቱፎን አበ ምኔት፣ ብፁዕ አቡነ ሶምዴት ፍራህ ማሃ ቲራቻን የካርዲናሉን ዕረፍት በማስመልከት የቀረበውን ሥነ-ሥርዓት የመሩ ሲሆን፥ በዚህ ሥነ-ሥርዓት ላይ አሥር የቡዳ እምነት መነኮሳት ሥነ-ሥርዓቱን ለመምራት የተዘጋጁ ጸሎቶችን በዝማሬ አቅርበዋል።

የታይላንድ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ሊቀ መንበር አቡነ ጆሴፍ ቹሳክ ሲሪሱት በጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተነበበውን የቅዱስ ዮሐንስን ወንጌል በመጥቀስ እንደተናገሩት፥ “የስንዴ ቅንጣት በምድር ላይ ወድቃ ካልሞተች እንደ እህል ትቀራለች፤ ከሞተች ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች” ሲሉ አስረድተዋል።

ጥቅሱ የሃይማኖታዊ ግንኙነቶችን በመገንባት ረገድ የብፁዕ ካርዲናል ሚጌል አንጄል አዩሶን ዘላቂ ውርስ አፅንዖት የሰጠ ሲሆን፣ ክስተቱ በቡዳ እምነት መነኮሳት እና በካቶሊክ ቀሳውስት መካከል ያለውን አንድነትን እና መከባበርን ከማሳየት በተጨማሪ ስለ ካርዲናል አዩሶ የህይወት ተልእኮ ልብ የሚነካ ማሳሰቢያ ሆኖ አገልግሏል።

ካርዲናል አዩሶ በሃይማኖቶች መካከል በሚደረግ ውይይት ዓለም አቀፋዊ መሪ የነበሩ ሲሆን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በኅዳር ወር 2015 ዓ. ም. በታይላንድ ውስጥ በተካሄደው እና ከመላው ዓለም የተወጣጡ ከ150 በላይ ልዑካን በተሰበሰቡበት ሰባተኛው የቡዳ እና የክርስትና እምነቶች ስብሰባ ላይ ተገኝተዋል።

“ካሩና እና አጋፔ የቆሰለውን የሰው ልጅ እና ምድርን በውይይት መፈወስ” በሚል መሪ ቃል፣ ርህራሄ እና ፍቅር ማህበረሰባዊ እና አካባቢያዊ ተግዳሮቶችን ለመፍታት መንገዶች እንደሆኑ አፅንዖት ሰጥቷል። ስብሰባው በሃይማኖቶች መካከል እያደገ ያለውን ትብብርን የሚያመለክት ጉልህ ምልክት የነበረ ሲሆን፥ የታይላንድ ቡዳ እምነት መሪዎች ርኅራኄን በማስተዋወቅ እና ለዓለማቀፋዊ ቀውሶች የጋራ ኃላፊነትን በመስጠት ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ እና ብፁዕ ካርዲናል አዩሶ ስጦታን ማበርከታቸው ይታወሳል።

በስፔን የተወለዱት ካርዲናል አዩሶ ሕይወታቸውን በሃይማኖቶች መካከል ውይይት በማድረግ አሳልፈዋል። በግብፅ እና በሱዳን ሚስዮናዊ ሆነው ያካበቱትን ልምድ በማሳደግ በክርስትና እና በእስልምና እምነቶች መካከል ግንኙነቶችን በማጎልበት ረገድ ትልቅ አስተዋጽዖን አበርክተዋል።

በእርሳቸው የሚመራው የቅድስት መንበር ጳጳሳዊ ምክር ቤት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2019 በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በአል አዝሃር ታላቁ ኢማም አህመድ አል ታይብ መካከል የሰብአዊ ወንድማማችነት ሠነድ እንድፈረም ማመቻቸቱ ይታወሳል።

ብፁዕ ካርዲናል አዩሶ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር አብረው ሙስሊም ማኅበረሰብ በብዛት በሚኖሩባቸው አገሮች ታሪካዊ ጉብኝቶችን በማድረግ እና ክርስቲያኖች አናሳ በሆኑባቸው ክልሎች ውስጥ ሰላምን እና መግባባትን አበረታተዋል። ለአንድነት የሰጡት የማይናወጥ ቁርጠኝነት በዓለም አቀፍ ደረጃ በሃይማኖት ማኅበረሰቦች ዘንድ የማይጠፋ አሻራን ጥሏል።

 

02 December 2024, 16:39