ፈልግ

በታይላንድ “ተጨማሪ ሰላም” በሚል ርዕሥ የተዘጋጀ የተማሪዎች ውድድር በታይላንድ “ተጨማሪ ሰላም” በሚል ርዕሥ የተዘጋጀ የተማሪዎች ውድድር  

የታይላንድ ወጣቶች ከሃይማኖታዊ መግባባት ጋር ሰላምን በማስተዋወቅ ላይ እንደሚገኙ ተገለጸ

በታይላንድ ከሚገኙ ከ40 በላይ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ከ200 በላይ ተማሪዎች በዋና መዲናዋ ባንኮክ ውስጥ በሚገኝ የቴክኖሎጂ ተቋም ተገናኝተው በሃይማኖቶች መካከል ስምምነትን ለመፍጠር የሚያግዙ መፍትሄዎች በማቅረብ ውይይት አድርገዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ተጨማሪ ሰላም” በሚል ርዕሥ ኅዳር 21/2017 ዓ. ም. በቀረቡ የተለያዩ ፕሮጀክቶች መካከል በተካሄደው ውድድር ከ40 በላይ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ 10 የፍጻሜ እጩዎች ያቀረቧቸው ሃሳቦች በአገሪቱ ውስጥ አንገብጋቢ ከሆነው ሃይማኖታዊ መግባባት እና በሰላም አብሮ ከመኖር ጋር የተያያዙ መሆናቸው ታውቋል።

ውድድሩን ለማዘጋጀት ተነሳሽነቱ የተገኘው ባለፈው ሐምሌ “ተጨማሪ ሰላም” በሚል ርዕሥ በተዘጋጀው ውድድር ላይ የተሳተፈው የኤክትራ ትምህርት ቤት የተማሪዎች ቡድን አንድ መቶ ሺህ የታይላንድ ባት በማሸነፉ እንደ ሆነ ታውቋል። ቡድኑ የገንዘብ ድጋፉን ተጠቅሞ በተለያዩ የሃይማኖት ቡድኖች መካከል ውይይትን ለማስፋፋት የታለመውን ፕሮጀክት ተግባራዊ በማድረግ ለውድድሩ ዋና ንድፍ ሆኖ ያገለግላል።

 በውድድሩ ወቅት ተማሪዎች ያቀረቡት የሃይማኖታዊ መግባባትን ምሳሌ
በውድድሩ ወቅት ተማሪዎች ያቀረቡት የሃይማኖታዊ መግባባትን ምሳሌ

የውድድሩ የመጨረሻዎቹ ተሳታፊዎች እንደ ሃይማኖታዊ መድልዎ እና በወጣቶች መካከል የሃይማኖቶች አለ መግባባትን የመሳሰሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሚያግዙ የተለያዩ ስልቶችን አቅርበዋል። መሳጭ የሆኑ ትምህርታዊ ጨዋታዎችን ከመፍጠር እና ፊልሞችን ከማዘጋጀት ጀምሮ ዘፈኖችን እና ተጨማሪ ዘዴዎችን በመጠቀም ስለ ሃይማኖቶች መስማማት እና ለግጭቶች ምክንያት የሚሆኑ ሃሳቦች የተጠቆሙበት እንደ ነበር ተመልክቷል።

የ “ተጨማሪ ሰላም” ቡድን መሪ የሆኑት ቹላባት ታንቲቻይቦሪቦን እንደተናገሩት፥ የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች በፍቅር፣ በርህራሄ እና በአክብሮት እሴቶች እንደሚመሩ፣ ይህም የሚያሳየው ልዩነቶች ቢኖሩንም አንዱ ከሌላው መማር፣ እርስ በርስ መገናኘት እና በጋራ ማደግ የሚቻል መሆኑን አስረድተዋል።

“ተጨማሪ ሰላም” በሚል ርዕሥ የተዘጋጀ የተማሪዎች ውድድር
“ተጨማሪ ሰላም” በሚል ርዕሥ የተዘጋጀ የተማሪዎች ውድድር

ቹላባት በማከልም ትምህርት ቤታቸው ብዝሃነትን እና አካታችነትን የሚያበረታታ ቢሆንም በውጭ ያለው ሰፊው እውነታ አሁንም ፈታኝ እንደሆነ እና በሃይማኖቶች መካከል የሚታየው ዘላቂ ግጭት መለያየትን እንደሚፈጥር በመጠቆም ብዙ ሰዎች በሃይማኖታዊ ልዩነቶች ላይ መወያየት እንደማይፈልጉ እና ይህም የጋራ መግባባት ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት እንደሚያደናቅፈው አስረድተዋል።

“ሁሉም ሃይማኖቶች ሰላምን የሚያስተምሩ ከሆነ ለምን ሁሉም ሃይማኖቶች ሰላም ማግኘት አይችሉም?” የሚለው የ “ተጨማሪ ሰላም” ፕሮጀክት ዋና ጥያቄ መሆኑን ቹላባት ገልጸዋል። ውድድሩ ይበልጥ እርስ በርሱ የሚስማማ የወደፊት ሁኔታን በመቅረጽ ረገድ ለወጣቶች ወሳኝ ሚና አጽንዖት ሰጥቷል። የሳራሳስ ኤክትራ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር የሆኑት ፒሱት ዮንግካሞል ማኅበራዊ ችግሮችን በመፍታት ትክክለኛነት እና አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ፒሱት በማከልም፥ “ዛሬ እያንዳንዳችሁ ለውጡ እዚህ እና አሁን መጀመሩን አሳይታችሁናል። ባቀረባችሁት ገለጻ እና ሃሳብ ከዚህ ዝግጅት ባለፈ ቀጣይነት ያለው የሰላም እና የተስፋ ዘር ዘርግታችኋል” ብለዋል። “እውነተኛነታችሁ ከፍተኛ ሃብታችሁ ነው” ያሉት የሳራሳስ ኤክትራ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ፒሱት ዮንግካሞል ለውድድሩ ተሳታፊዎች በስጡት ምክር፥ “ታማኝነታችሁ የለውጥ ፈጣሪነት ጉዞአችሁን ሊመራ ይገባል” በማለት አሳስበዋል።

“ተጨማሪ ሰላም” በሚል ርዕሥ የተዘጋጀው የተማሪዎች ውድድር
“ተጨማሪ ሰላም” በሚል ርዕሥ የተዘጋጀው የተማሪዎች ውድድር

“ተጨማሪ ሰላም” በሚል ርዕሥ በቀረበው ዝግጅት የውይይት እና የትብብር ሃይል አጉልቶ ያሳየ እንደ ነበር የገለጹት የእስያ አኅጉር ካቶሊካዊ የዜና ተቋም ዋና ዳይሬክተር ፒተር ሞንታይንቪቺንቻይ፥ ተማሪዎቹ አሳሳቢ ጉዳዮችን ለመፍታት ላሳዩት ጥረት አመስግነዋል።

የዜና ተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፒተር በማከልም፥ “እናንተ ዛሬ ያደረጋችሁት ነገር ከተጠበቀው በላይ ነው፣ በተለይም እንዲህ ያለውን አስቸጋሪ እና አሳሳቢ ርዕሠ ጉዳይ ለመፍታት ድፍረት በማሳየት ረገድ በዝግጅቱ ላይ የቀረቡት የመፍትሄ ሃሳቦች ሁላችንም ተስፋ የምናደርገው እና እርስ በርስ መደማመጥ የሚለውን የሲኖዶሳዊነት አካሄድ ሃይል ያሳያል” ብለዋል።

ውድድሩ የሳራሳስ ኤክትራ ትምህርት ቤት ተልዕኮን መሠረት ያደረገ እና የሁለት ቋንቋ ተናጋሪ ካቶሊካዊ ተቋም እንደሆነ ታውቋል። የትምህርት ቤቱ ቀጣይነት ባለው ቁርጠኝነቱ በሃይማኖቶች መካከል ያለው ሰፊ ግንዛቤ የአንድነት እና የሰላም እይታ እንደሚያሳይም ተመልክቷል።

የታይላንድ ወጣቶች የፈጠራ ችሎታቸውን እና ቁርጠኝነታቸውን በማስተላለፍ የተወሳሰቡ ማኅበራዊ ጉዳዮችን ብቻ ሳይሆን የበለጠ ሰላማዊ እና ሁሉን አቀፍ ማኅበረሰብን ለማምጣት የተስፋ ዘሮችን እየዘሩ እንደሚገኙ ተመልክቷል።

ዝግጅቱ የሙዚቃ ኮንሴትንም ያካተተ ነበር
ዝግጅቱ የሙዚቃ ኮንሴትንም ያካተተ ነበር

 

04 December 2024, 14:17