ከ 2007 እስከ 2017 ዓ.ም. ባሉት ዓመታት በናይጄሪያ 145 ካህናት መታገታቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በናይጄሪያ ባለፉት አስርት ዓመታት በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ካህናቶች፣ የክህነት ተማሪዎች እና በሃዋሪያዊ ሥራ ሠራተኞች ላይ እየተፈጸመ ያለው አሰቃቂ የጠለፋ ሁኔታ በሃገሪቷ ለማስለቀቂያ ገንዘብ ተብሎ የሚደረገው የእገታ ተግባር እየጨመረ መሄዱን ያሳያል ተብሏል።
ባለፈው ሳምንት ፊደስ የተባለው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የዜና ኤጀንሲ ባደረገው ጥናት ከ 2007 እስከ 2017 ዓ.ም. በድምሩ 145 ካህናት ታፍነው መወሰዳቸውን፣ አስራ አንድ ካህናት ደግሞ መገደላቸውን፣ እንዲሁም አራቱ ደግሞ እስከ አሁን ድረስ የደረሱበት እንዳልታወቀ ዘግቧል።
በቅርብ ጊዜ ከተከሰቱ ክስተቶች መካከል የካቲት 26 ቀን 2017 ዓ.ም. በካዱና ግዛት ውስጥ በሚገኘው የካፋንቻን ሀገረ ስብከት ካህን የሆኑት አባ ሲልቬስተር ኦኬቹኩ ከታገቱ ከአንድ ቀን በኋላ መገደላቸውን ‘ኤሲ አፍሪካ ኤጀንሲ’ የተባለ የሚዲያ ተቋም ዘግቧል።
ይህ ተግባር ከመፈጸሙ ከሁለት ቀናት በፊት በኤዶ ክፍለ ሀገር በአውቺ ሀገረ ስብከት ውስጥ ታጣቂዎች አንድ አንድሪው ፒተር የተባለ የክህነት ተማሪ አባ ፊሊፕ ኤኩዌሊ ከተባሉ ሌላ ካህን ጋር ካገቷቸው በኋላ የክህነት ተማሪውን በአሰቃቂ ሁኔታ የገደሉ ሲሆን፥ ካህኑ በመጨረሻም ከአስር ቀናት እስራት በኋላ መጋቢት 4 ቀን 2017 ዓ.ም. መፈታታቸው ተገልጿል።
አፈና፡ በናይጄሪያ ውስጥ ትልቅ እና ቀጣይነት ያለው ጉዳይ መሆኑ
በነዳጅ ዘይት በበለፀገው የኒጀር ዴል ክልል ውስጥ ታጣቂ ቡድኖች የውጭ የነዳጅ ዘይት ተቋማት ኃላፊዎችን ማፈን ከጀመሩበት ከዘጠናዎቹ ዓመታት ጀምሮ በናይጄሪያ ውስጥ የእገታ ተግባር ትልቅ ጉዳይ እየሆነ መምጣቱ የተነገረ ሲሆን፥ እገታው የሚፈጸምበት ትልቁ ምክንያት መንግሥት የነዳጅ ምርት በማህበረሰቡ ውስጥ እያደረሰ ስላለው ብክለት አስቸኳይ የሆነ መፍትሄ እንዲሰጥ ግፊት ለማድረግ እንደሆነም ተነግሯል።
ከ 2001 ዓ.ም. ጀምሮ እስላማዊው የቦኮ ሃራም ታጣቂዎች በተለይ በናይጄሪያ ሰሜናዊ ምስራቅ እና ሰሜናዊ ምዕራብ፣ በተማሪዎች ላይ የጅምላ ጠለፋዎችን ጨምሮ በርካታ እገታዎችን በመፈጸም ተጠያቂ የተደረገ ሲሆን፥ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የእገታ ተግባር ከሀገሪቱ የከፋ የኢኮኖሚ ሁኔታ ጋር ተያይዞ እየተስፋፋ የመጣ ኢንዱስትሪ መሆኑ ይነገራል። በዚህም አንፃር ከ 2003 ዓ.ም. ጀምሮ ለገንዘብ ተብሎ የሚፈጸም የእገታ ተግባር በበርካታ የሃገሪቱ ክፍሎች መስፋፋቱ የተነገረ ሲሆን፥ የሃገሪቱን ዋና ከተማ አቡጃን ጨምሮ በሁሉም 36ቱ የሃገሪቱ ግዛቶች፣ በተለይም ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ በከፍተኛ ሁኔታ እንደተሰራጨ መረጃዎች ያመላክታሉ።
ከሃምሌ 2014 እስከ 2015 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ 3,620 ሰዎች በ582 የአፈና ድርጊቶች ታፍነው የተወሰዱ ሲሆን፥ ለእነዚህም ሰዎች የማስለቀቂያ ገንዘብ ተብሎ 5 ቢሊዮን ኒያራ ወይም 3.88 ሚሊዮን ዶላር ለቤዛ መከፈሉን መረጃዎች ያሳያሉ።
የንግድ ሰዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ ‘ጥሩ የኑሮ ሁኔታ’ ላይ አሉ ተብሎ የሚታሰቡ የቤተክርስትያን ሰራተኞች ከጊዜ ወደ ጊዜ ኢላማ የመደረግ እድላቸው መጨመሩም ጭምር ተነግሯል።
በካዱና ግዛት ካህናት በብዛት መታገታቸው
ፊደስ የዜና ኤጀንሲ ዘገባ እንደሚያመለክተው ክስተቱ በተለይ በተወሰኑ ግዛቶች ማለትም እንደ ኦዌሪ፣ ኦኒትሻ እና ካዱና ግዛቶች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች የታገቱባቸው ክልሎች እንደሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፥ በክልሎቹ ምንም እንኳን ከፍተኛ ቁጥር ያለው አፈና ቢፈጸምም አብዛኞቹ የታገቱ ካህናት የአከባቢው ፖሊስ ባደረገው የማዳን ስራዎች የማስለቀቂያ ገንዘብ ተከፍሎ ሊለቀቁ እንደቻሉ ተገልጿል። ከእነዚህም ውስጥ በካዱና ግዛት 24 ካህናት ታግተው ሰባቱ ደግሞ የተገደሉባት ክልል በመሆን ክልሏ በጣም አደገኛ ከሚባሉት ውስጥ ግንባር ቀደም ለመሆን የቻለች ሲሆን፥ ይህ ከፍተኛ የሟቾች ቁጥር የአሸባሪዎች እንቅስቃሴ፣ የአመጽ እና የሃይማኖታዊ ውጥረቱ እየጨመረ መምጣቱን የሚያሳይ እና ይህም ለካህናቱ የበለጠ አደገኛ ክልል ያደርገዋል ተብሏል።
ከፍተኛ የሟች ቁጥር ካስመዘገቡት ሌሎች የናይጄሪያ ክልሎች ውስጥ በአቡጃ ሁለት ካህናት የሞቱባት ሲሆን፥ በቤኒን አንድ ካህን እንዲሁም በኦኒትሻ አንድ ካህን እንደተገደሉ ዘገባው ከጠቆመ በኋላ፥ ታፍነው የተወሰዱ ካህናት የጠፉባቸውን የናይጄሪያ ግዛቶችን በመዘርዘር ከእነዚህም ውስጥ የካዱና፣ ቤኒን እና ኦዌሪ ግዛቶች እንደሚገኙበት አብራርቷል።
በሌጎስ፣ ኢባዳን እና ካላባር አነስተኛ የእገታ ጉዳዮች ተመዝግበዋል
በአንጻሩ የሌጎስ፣ ኢባዳን እና ካላባር ግዛቶች አነስተኛ የእገታ ጉዳዮች ሪፖርት የተደረጉ ሲሆን፥ በእነዚህ አካባቢዎች የታገቱ ካህናት በሙሉ በሰላም መለቀቃቸውን መረጃው በማመላከት፥ በተለየ ሁኔታ ሌጎስ በጠንካራ የፀጥታ እርምጃዎች እና በዝቅተኛ የሃይማኖት ተኮር ጥቃቶች እንቅስቃሴ ምክንያት በጣም ደህንነቱ የተጠበቀ አከባቢ ሆኖ ተመዝግቧል።
‘ተቀባይነት የሌለው ልማድ ነው’
ኤሲአይ የተባለው የካቶሊክ ሚዲያ የምዕራብ አፍሪካ ክልላዊ ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ (RECOWA) ባለፈው ሳምንት ያወጣውን መግለጫ በመጥቀስ ድርጊቶቹ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን በማንሳት፣ በመላው የምዕራብ አፍሪካ ሃገራት በተለይም በናይጄሪያ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ካህናት ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት በጽኑ ያወገዘ ሲሆን፥ ብጹአን ጳጳሳቱ የአንድ ካህን ወይም የኃይማኖት ተከታይ የመታገት ዜና ሳይነገር አንድ ወር እንደማያልፍ ጠቁመው፥ የታገቱ ሰዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጸሎት እንዲደረግ ጥሪ በማቅረብ፥ እንዲሁም ከፍተኛ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች የሚያገለግሉ ካህናት ምንም እንኳን የሚያጋጥሟቸው አደጋዎች ከባድ ቢሆኑም፥ ድሆችን እና የተገለሉ ሰዎችን የማገልገል ተልዕኳቸውን በጽናት እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።