በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የጎማ ሃገረ ስብከት ጳጳስ ወታደራዊ እርምጃ መፍትሄ እንደማይሆን ገለጹ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምሥራቃዊ ክፍል በመንግስት ታጣቂዎች እና በሩዋንዳ በሚደገፉት የኤም 23 አማፂያን ቡድን መካከል ያለው ውጥረት እና ግጭት ተጠናክሮ መቀጠሉ የተገለጸ ሲሆን፥ በሃገሪቷ ሰላምን ለማስፈን የተደረጉ በርካታ ሙከራዎች ያልተሳኩ ቢሆንም፥ የጎማ ሃገረ ስብከት ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ዊሊ ንጉምቢ ንጌሌ ለቫቲካን ዜና እንደተናገሩት ግጭቱ ከተከሰተበት ጥር ወር መጨረሻ ጀምሮ እስከ አሁን “ሁኔታው ብዙም የተለወጠ አይመስልም” በማለት የጉዳዩን አሳሳቢነት ገልጸው፥ ሆኖም ግን ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ በዘለቀው በነዚህ ሁሉ ግጭቶች እና ችግሮች መካከል ህዝቡ ያሳየውን ጽናት እና ቁርጠኝነት አወድሰዋል።
“ሰዎች በፍርሃት ውስጥ ናቸው”
የጎማ ከተማ በ ኤም 23 አማፂያን ቁጥጥር ስር ከዋለ ሁለት ወር ሊሞላው እንደሆነ የገለጹት ጳጳሱ፥ ሆኖም ግን ሁኔታው እስከ አሁን ብዙም መሻሻል እንዳላሳየ ገልፀው፥ “ልዩነቱ አሁን ጦርነቱ በጎማ ሳይሆን ወደ ሌሎች የሀገረ ስብከቱ አካባቢዎች መስፋፋቱ ብቻ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
ጠለፋ እና ግድያ በአከባቢው “አዲስ ልማድ” በመሆን እና የግጭቱ አካል እየሆኑ በመምጣታቸው፥ በዚህም ምክንያት ሰዎች “በፍርሀት እየኖሩ ነው” ብለዋል።
የህዝቡ የዕለት ተዕለት ኑሮው በከፍተኛ ሁኔታ መቀየሩን ያስታወሱት ጳጳሱ “ታጣቂ ሽፍታዎቹ ገንዘብ ለመስረቅ እና ንብረት ለመዝረፍ ወደ መኖሪያ ቤት ስለሚመጡ ሌሊት መተኛት የማይቻል ሆኗል” ሲሉ ተናግረዋል።
በዐቢይ ጾም ወቅት ድህነት መባባሱ
በእነዚህ ሁሉ ግጭቶች እና ችግሮች መካከል የካቲት 26 የዐቢይ ጾም መግቢያን ለማክበር የብጹእ አቡነ ንጌሌ ቤተ ክርስቲያን በበርካታ ምዕመናን የተሞላ ሲሆን፥ ጳጳሱ እንደተናገሩት “በከተማዋ ባሉ ሁሉም አጥቢያዎች የጸጥታው ሁኔታ አስቸጋሪ ቢሆንም፣ የነበረው ሥነ ስርዓት ደማቅ ነበረ” ሲሉ በአድናቆት ገልጸዋል።
ከደህንነት ጥያቄም ባሻገር፥ በጥር ወር መጨረሻ ላይ አማፅያኑ በጎማ ከተማ ላይ ጥቃት ካደረሱ በኋላ ባንኮች ተዘግተው ስለነበር የኢኮኖሚው ሁኔታም መባባሱን የጠቆሙት ብጹእነታቸው፥ “የአከባቢው ነዋሪዎች፣ በተለይም ነጋዴዎች በሕይወት ለመትረፍ የሚያስችላቸውን መንገድ አጥተዋል” በማለት የችግሩን አሳሳቢነት ከገለጹ በኋላ፥ ከዚህም ባለፈ የመንግስት ሰራተኞች ደሞዛቸውን እያገኙ እንዳልሆነ እና ወላጆች ለልጆቻቸው ትምህርት ቤት ለመክፈል እንደተቸገሩ አብራርተዋል።
ግጭቱ ቢኖርም የዐቢይ ጾምን በአግባቡ መፆም ይገባል
በአካባቢው ያለው የድህነት መጠን እየጨመረ በሄደበት በአሁኑ ወቅት የምንፆመውን የዐቢይ ፆም መጪው ጊዜ የተሻለ ሰላም የሚመጣበት እና ተስፋ የምናደርግበት እንዲሆን ክርቲያኖች ፆም ጸሎት በማድረግ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ በመግለጽ፥ በተጋረጠባቸው ፈተናዎች እንኳን ሳይቀር “ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው በተለይም ለድሆች፣ እንዲሁም አብዛኞቹ የወታደር ቤተሰቦች ለሆኑት በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ሰዎች አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ አሳስበዋል።
የዐብይ ጾም ወቅትን በአግባቡ ለማሳለፍ የአካባቢው ክርስቲያኖች ከጎማ ውጭ በቁምስና ደረጃ መንፈሳዊ ጉዞዎችን እና መንፈሳዊ ልምምዶችን ያዘጋጁ ሲሆን፥ የሀገረ ስብከቱ ሃዋሪያዊ ሥራ ማዕከል ከካህናቱ ጋር ወደ አድባራት ሄደው የስብከተ ወንጌል ዘመቻ የሚያዘጋጁ ቡድኖችን እና ሃዋሪያዊ ሥራ ሰራተኞችን እያስተባበሩ እንደሚገኝ ገልጸው፥ ምንም እንኳን ስብሰባዎቹ እንደ ጠላትህን መውደድ፣ ይቅርታ ማድረግ ወይም መጋራት የመሳሰሉ ሁልጊዜ ቀላል ያልሆኑ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚዳሰሱበት ቢሆንም እነዚህ ዘመቻዎች በጣም የተሳካላቸው እንደሚሆኑ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
ብጹእ አቡነ ንጌሌ የአገሬው ክርስቲያኖች “የወንድማማችነት ፍቅርን እና ክርስቲያናዊ አንድነትን፣ ካቶሊክ ላልሆኑ ሰዎች እንኳን ሳይቀር ለሌሎች ግልጽ መሆንን መስበካቸውን ቀጥለዋል” ሲሉ አበክረው ተናግረዋል።
ወታደራዊ እርምጃ መፍትሄ አይሆንም
በአንጎላ ዋና ከተማ ሉዋንጋ በመንግስት ሃይሎች እና በኤም 23 አማፂያን መካከል የሰላም ድርድር ለማድረግ ማክሰኞ መጋቢት 9 ቀን 2017 ዓ.ም. ቀጠሮ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፥ ቀኑ ከመድረሱ ከአንድ ቀን በፊት የኤም 23 ቡድን በአባሎቻቸው ላይ የተጣለው ዓለም አቀፍ ማዕቀብ ለውይይቱ እንቅፋት እንደሆነ በመጥቀስ ከውይይቱ መውጣቱን ያስታወቀ ሲሆን፥ አንጎላ በሁለቱ ቡድኖች መካከል አስታራቂ በመሆን በርካታ ሥራዎችን ለመስራት ተዘጋጅታ እንደነበር ተገልጿል።
ብጹእ አቡነ ንጌሌ በተፈጠረው ሁኔታ የተሰማቸውን ቅሬታ በመግለጽ፥ ውይይት ሰላምን ለማምጣት አስፈላጊ ነገር እንደሆነ እንዲሁም በስልጣን ላይ ያሉት ለቀጣይ ጊዜያት ለውይይት እንደሚዘጋጁ ያላቸውን ተስፋ ከገለጹ በኋላ፥ በመጨረሻም “ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ስለሚያጠፋ እና በአካባቢው ያለውን የድህነት ልዩነት ስለሚያሰፋ ለዚህ ግጭት ወታደራዊ እርምጃ መፍትሄ አይሆንም” በማለት አጠቃለዋል።