ፈልግ

Cookie Policy
The portal Vatican News uses technical or similar cookies to make navigation easier and guarantee the use of the services. Furthermore, technical and analysis cookies from third parties may be used. If you want to know more click here. By closing this banner you consent to the use of cookies.
I AGREE
የማታ ጸሎት በላቲን ቋንቋ
መርዐ-ግብር በድምጽ የቀረበ ዘገባ
የኮት ዲቯር ምርጫ፡ ህዝቡ ለሰላም ሲጸለይ - የማህደር ምስል የኮት ዲቯር ምርጫ፡ ህዝቡ ለሰላም ሲጸለይ - የማህደር ምስል  

ብጹአን ጳጳሳት በኮት ዲቯር ነፃ እና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ

ኮት ዲቯር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለማድረግ ሰባት ወራት ብቻ የቀራት ሲሆን፥ የሀገሪቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት በሃገሪቱ ውስጥ ስላለው ወቅታዊ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታ ያላቸውን ከፍተኛ ስጋት በመግለጽ፥ በያዝነው ሳምንት ሰኞ ዕለት ታትሞ በወጣው ሃዋሪያዊ መግለጫቸው ፖለቲከኞች እና የሃገሪቱ ዜጎች ለሰላም እና ሀገራዊ አንድነት ቅድሚያ እንዲሰጡ አሳስበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

“ከምርጫ በኋላ ግጭት አንፈልግም! ጦርነት አይኖርም! ሞት አይኖርም!” በማለት የሚጀምረው የብጹአን ጳጳሳቱ ሃዋሪያዊ መግለጫ፥ ሁሉም ዜጎች የግል ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ እና ባሉበት ቦታ የሰላም ፈጣሪ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል። ፖለቲካ ሁል ጊዜ ለጋራ ጥቅም መሥራት ያለበት ክቡር ጥሪ ነው ያሉት ብጹአን ጳጳሳቱ፥ ይህም በመሆኑ የፖለቲካ ንግግሮች እና ተግባራት በአይቮሪያን ማህበረሰብ ደህንነት ላይ ያተኮሩ እና የስነምግባር መርሆዎች ላይ የተመሰረቱ መሆን አለባቸው በማለት አሳስበዋል።

ብጹአን ጳጳሳቱ አክለውም ለአሥርት ዓመታት ያክል የመገናኛ ብዙሃንን እና የሠራተኛ ማህበራትን ለፖለቲካ ዓላማ በማዋል መራጮችን ለመቀስቀስ የተሞከረውን ተግባር እንደሚያወግዙ በመግለጽ፥ ከዚህ ይልቅ የእነዚህ ህዝባዊ ተቋማት ታማኝነት ወደ ቀደመ ሥፍራው እንዲመለስ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ተለዋዋጭ የፖለቲካ ሁኔታ
የሃገሪቱ የቤተክርስቲያ መሪዎች በሃዋሪያዊ መግለጫቸው ውስጥ ስለ ፖለቲካዊ ጥቃት መስፋፋት፣ ከወጣት ወንጀለኞች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን፣ በትምህርት ቤቶች ውስጥ የአደንዛዥ ዕፅ አጠቃቀም መስፋፋትን እና በአይቮሪያን ማህበረሰብ ውስጥ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ እና የመሰብሰብ ገደቦችን በማንሳት እነዚህ ድርጊቶች እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል።

ከዚህም ባለፈ ብጹአን ጳጳሳቱ በሃገሪቱ ውስጥ የተንሰራፋውን የጉቦ ተግባርን፣ የመሬት ይዞታ ግጭቶችን እና የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን ማሰር ወይም መሰደድን በጽኑ እንደሚያወግዙ ከገለጹ በኋላ፥ ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ በዕለት ተዕለት በሚደረጉ ፖለቲካዊ ውይይቶች ውስጥ የጥላቻ ንግግሮችን የማድረግ ዝንባሌ እንደሆነ ጠቁመው፥ እነዚህ ሁሉ ነገሮች በዜጎች መካከል አለመተማመንን እንደሚያባብሱ እና ማኅበራዊ ውጥረትን እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል።

ጳጳሳቱ አይቮሪ ኮስት ባለፉት ዓመታት በተለይም የ 2002 እና 2012 ዓ.ም. ምርጫን ተከትለው ከተከሰቱ ጉዳቶች እና ግጭቶች አሁንም ሙሉ በሙሉ እንዳላገገመች በማስታወስ፥ ያለፉት አሳዛኝ ክስተቶች እንዳይደገሙ ለመከላከል የሚጠቅም የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር ሁሉም ነገር መሰራት አለበት በማለት አስጠንቅቀዋል።

ሁሉንም ዕጩዎች ያካተተ መሆን አለበት
የአይቮሪ ኮስት ብጹአን ጳጳሳት እነዚህ ፈተናዎች ቢኖሩም ዜጎች ተስፋ እንዳይቆርጡ እና ራሳቸውን ለሞት አደጋ እንዳያጋልጡ በማሳሰብ፥ መጪው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አዲስ የግጭት ምንጭ ሳይሆን አገራዊ አንድነትን እና ህብረትን ለማጠናከር እድል እንዲሰጥ በሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ሁሉን አቀፍ ውይይት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል።

የቤተክርስቲያን መሪዎቹ ለሃገሪቱ ባለስልጣናት ባስተላለፉት መልዕክት፥ መስፈርቱን የሚያሟሉ ሁሉም ፕሬዝዳንታዊ እጩዎች ያለምንም እንቅፋት በምርጫው እንዲሳተፉ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፥ ጳጳሳቱ አሁን ያለውን ያልተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ ለማረጋጋት እና ብሄራዊ እርቅን ለማምጣት የሚቻለው ግልጽ እና ፍትሃዊ የምርጫ ሂደት መከተል ብቻ መሆኑን አጥብቀው ገልጸዋል። ከዚህም ባሻገር ምንም እንኳን መንግስት እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ቢሆንም፥ አንዳንድ የብሄራዊ እርቅ ውጥኖች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዳልሆኑ መመልከታቸውን አንስተዋል።

በ 2003 ዓ.ም. ምርጫን ተከትለው ተነስተው የነበሩ ግጭቶች ባበቁበት ወቅት የእርቅ ሂደቶች ሲበረታቱ እንደነበር እና በኮት ዲቯር ብሄራዊ እርቅን ለማምጣት ከፍተኛ ጥረት እንደተደረገ የሚታወስ ሲሆን፥ የሀገሪቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ ብሄራዊ እርቅ ከምርጫ በኋላ በሀገሪቱ ሰላምን ለማስፈን ቁልፍ ሚና እንዳለው አስታውሷል።

በምርጫ ሂደት ውስጥ ግልጽነት
ከዚህም ባለፈ ብጹአን ጳጳሳቱ የምርጫ ኮሚሽኑን ገለልተኝነት አስመልክተው አሁን ባለው አደረጃጀት እና አሠራር ምክንያት ተጨባጭነቱ እና ገለልተኝነቱ ላይ ያላቸውን ጥያቄ በማንሳት፥ ፍፁም ግልፅነት እና ፍትሃዊነትን የሚያረጋግጡ እርምጃዎችን እንዲከተሉ ብሎም ኮሚሽኑ ለፍትሃዊነት ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር እንዲያሳይ እና ወደፊት በሚደረጉ ምርጫዎች ላይ የህዝብ አመኔታ ሊያሳጡ የሚችሉ ጉድለቶችን እንዲያስተካክል አሳስበዋል። በተጨማሪም በምርጫ ዝርዝሩ ላይ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት እና የውጤቱን ታማኝነት ለማረጋገጥ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት በተለይም ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ቀጣይነት ያለው ውይይት እንዲደረግ መክረዋል።

ለአንድነት በጋራ መስራት
ብጹአን ጳጳሳቱ በሃዋሪያዊ መግለጫቸው ክርስቲያን የፖለቲካ ፓርቲዎች እውነትን በመያዝ የኅብረት እና የሰላም ብርሃን ፈጣሪዎች እንዲሆኑ በማበረታታት፥ በርካታ ተግዳሮቶች እንዳሉ ቢታወቅም ነገር ግን ሁሉም የሃይማኖት መሪዎች የፖለቲካ ቁማርን እንዲቃወሙ፣ ክብራቸውን እንዲጠብቁ እና ፖለቲከኞች በቁሳዊ ነገሮች እንዳያታልሏቸው አሳስበዋል። ከዚህም በላይ የኃይማኖት መሪዎች ነቅተው መጠበቅ እንዳለባቸው እንዲሁም አንድነታቸውን እና መንፈሳዊ ቁርጠኝነታቸውን አሳልፈው መስጠት እንደሌለባቸው በማስታወስ፥ ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ የተጠናከረ ጸሎት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

መጪው ጊዜ ሰላማዊ እንዲሆን ቁርጠኝነት ያስፈልጋል
ብጹአን ጳጳሳቱ የማህበራዊ ሚዲያ ትስስሮችን ጨምሮ ለሀገር አቀፍ እና ለዓለም አቀፍ ሚዲያ ባስተላለፉት መልእክት የተረጋገጡ መረጃዎችን እና ዜናዎችን በማሰራጨት እና በማካፈል ብቻ የዲሞክራሲ ጠባቂ ሆነው እንዲሰሩ የጋበዙ ሲሆን፥ በተለይም ማህበራዊ ሚዲያዎች በይዘቶቻቸው ህዝባዊ እና መከባበርን የሚያበረታቱ መልዕክቶችን እንዲያስተላልፉ በመምከር፥ የሁሉም የምርጫ ዘገባዎች የማዕዘን ድንጋይ ሁል ጊዜ ሙያዊ ብቃት እና ሥነ ምግባራዊ አስተሳሰቦች መሆን አለባቸው ካሉ በኋላ፥ በዚህ ረገድ የሀገሪቱ ተቆጣጣሪ አካላት ሁሉን የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚዛናዊ እና ሙያዊ ሽፋን ማግኘት መቻላቸውን ለማረጋገጥ አስፈላጊ ናቸው ብለዋል።

“ጥላቻን አትንዙ” በማለት ያስጠነቀቁት ብጹአን ጳጳሳቱ፥ በተለይ ወጣቶች ማጭበርበርን በመተው ለወደፊት ሕይወታቸው ሲሉ በኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀስን መምረጥ እንዳለባቸው መክረዋል።

የጸጥታ ሃይሎች ስራቸውን እና ተግባራቸውን በሚፈጽሙበት ወቅት ገለልተኝነታቸውን እና ሙያዊ ብቃታቸውን እንዲጠቀሙ በማሳሰብ፥ ከሁሉም በላይ የዜጎችን መሰረታዊ መብቶች በማንኛውም ጊዜ ማክበር እና መጠበቅ አለባቸው ብለዋል።

መጪው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ በኮት ዲቯር በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዙሪያ ተስፋ እና ስጋት እየተስተዋሉ ባለበት በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ ብጹአን ጳጳሳት ለጋራ ንቃተ ህሊና እና ሰላም ሁሉም የበኩሉን በቁርጠኝነት እንዲወጣ በመጠየቅ፥ “ከዚህ በኋላ ምርጫን ተከትሎ የሚነሳ ብጥብጥ አንፈልግም! ጦርነት አይኖርም! ሞት አይኖርም” በማለት አቋማቸውን ገልጸዋል።
 

26 Mar 2025, 13:56
Prev
April 2025
SuMoTuWeThFrSa
  12345
6789101112
13141516171819
20212223242526
27282930   
Next
May 2025
SuMoTuWeThFrSa
    123
45678910
11121314151617
18192021222324
25262728293031