የጋዛ ቁምስና መሪ ካኅን በአካባቢው ሰላም እንዲወርድ ተማጸኑ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ጋዛ ውስጥ የማያቋርጥ የቦምብ ድብደባ እየተካሄደ በመሆኑ ክርስቲያኑ ማኅበረሰብ ጭንቀት ውስጥ ወድቀው ጸሎት በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ በመግለጽ የቁምስና መሪ ካኅን አባ ሮማኔሊ ልባዊ የሰላም ጥሪ አቅርበዋል። አባ ሮማኔሊ “ቴሬ ሳንቴ” ወይም ቅድስት አገራት ለተሰኘ መጽሔት በላኩት መልዕክት፥ “ተኩስ ማቆም ብቻ ሳይሆን ይህ ጦርነት አብቅቶ ለመላዋ ቅድስት ሀገር የሰላም ጊዜ እንዲመጣ” በማለት ተማጽነዋል።
በመጋቢት 8/2017 ዓ. ም. ምሽት ዳግም የተቀሰቀሰው ጦርነት ከ400 በላይ ሰዎችን ለሞት መዳረጉ እና ይህም ለሁለት ወራት የቆየው የተኩስ አቁም ስምምነት ማብቃቱን አስታውቋል። አባ ሮማኔሊ ስለ ምዕመናኑ ስቃይ እና ለስደተኞች እየተደረገ ስላለው ዕርዳታ ሲገልጹ፣ በቅድስት ማዜር ቴሬዛ እህቶች በኩል እንክብካቤ የሚደረግላቸውን ሕሙማንን፣ የአካል ጉዳተኞችን እና ህጻናትን አስታውሰዋል። የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት እና ካሪታስ ኢንተርናሽናልስ የተሰኘ ካቶሊካዊ የዕርዳታ ድርጅት የጦርነቱን መባባስ አውግዘው ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑትን ጥበውቃ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።
የአሜሪካ እና የዩክሬን ቤተ ክርስቲያን መሪዎች በኪየቭ መገናኘት
በዩክሬን የተኩስ አቁም ድርድር እየተካሄደ ባለበት በዚህ ሳምንት የዩክሬን የግሪክ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሲቪያቶስላቭ ሼቭቹክ ከዩናይትድ ስቴትስ ለመጡ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ልዑካን ቡድን አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የልዑካን ቡድኑን የመሩት በአሜሪካ የምሥራቅ አውሮፓ የዕርዳታ ቢሮ ሃላፊ ሆነው በቅርቡ የተሾሙት አቡነ ጄራልድ ዊንኬ ሲሆኑ፥ ሃላፊው በመጀመሪያ ተልዕኮአቸው ኪየቭን ለመጎብኘት በማሰባቸው አቡነ ሼቭቹክ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። ይህ ከአትላንቲክ አገራት ጋር ያላቸው አጋርነት የዓለም መሪዎች ዩክሬንን በተጨባጭ መንገድ እንዴት መደገፍ እንዳለባቸው እና ለሰላም እንዴት መሥራት እንደሚገባ የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል።
ጾም በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ቀጥሏል
የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት የዐብይ ጾም ጉዟቸውን እንደ ልማዳቸው እና እንደ ቀን አቆጣጠራቸው መቀጠላቸው ተገልጿል። የአርመን አብያተ ክርስቲያናት ያለውፈውን እሑድ በጠፋው ልጅ ምሳሌ ላይ በማሰላሰል ያከበሩ ሲሆን፥ ታሪኩ ውርሱን ካባከነ በኋላ የአባቱን ይቅርታ ለማግኘት በተመለሰው ልጅ ታሪክ የእግዚአብሔርን ወሰን የለሽ ምሕረት አጉልቶ የሚያሳይ እንደሆነ ተገልጿል።
በባይዛንታይን የአምልኮ ወግ የቅዱሳን ቅድሳት አጽሞች የበረከት ምንጭ መሆናቸውን የሚያሳስብ መሆኑን በመገንዘብ ምእመናን ያለፈውን እሑድ በታላቅ መንፈሳዊነት አክብረዋል። ለብርሃነ ትንሳኤው በዓል በሚዘጋጁበት ወቅት እነዚህ ሁለት ወጎች ምዕመናን በእምነታቸው እና በአስተንትኖአቸው መንፈሳቸውን የሚያዋኅዱበት እንደሆነም ተመልክቷል።