የመጋቢት 21/2017 ዓ.ም የአራተኛው የዐብይ ጾም ሳምንት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
የእለቱ ንባባት
1. መ. ኢያሱ 5፡9.10-12
2. መዝሙር 33
3. 2ቆሮ. 5፡17-21
4. ሉቃስ 15፡1-3፤ 11-32
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል
ቀራጮችና ኀጢአተኞችም ሁሉ ሊሰሙት ወደ እርሱ ይቀርቡ ነበር። ፈሪሳውያንና ጻፎችም “ይህስ ኀጢአተኞችን ይቀበላል፤ ከእነርሱም ጋር ይበላል፤” ብለው እርስ በርሳቸው አጉረመረሙ። ይህንንም ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው
የጠፋው ልጅ ምሳሌ
እንዲህም አለ “አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። ከእነርሱም ታናሹ አባቱን ‘አባቴ ሆይ! ከገንዘብህ የሚደርሰኝን ክፍል ስጠኝ፤’ አለው። ገንዘቡንም አካፈላቸው። ከጥቂት ቀንም በኋላ ታናሹ ልጅ ገንዘቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፤ ከዚያም እያባከነ ገንዘቡን በተነ። ሁሉንም ከከሰረ በኋላ በዚያች አገር ጽኑ ራብ ሆነ፤ እርሱም ይጨነቅ ጀመር። ሄዶም ከዚያች አገር ሰዎች አንዱ ጋር ተጠጋ፤ እርሱም ዐሣማ እንዲያሰማራ ወደ ሜዳ ላከው። ዐሣማዎችም ከሚበሉት ፍልፋይ ለመጥገብ ይመኝ ነበር፤ የሚሰጠውም አልነበረም። ወደ ልቡም ተመልሶ እንዲህ አለ ‘ምግብ የሚተርፋቸው የአባቴ ተቀጣሪዎች ስንት ናቸው? እኔ ግን ከዚህ በራብ እጠፋለሁ። ተነሥቼም ወደ አባቴ እሄዳለሁና “አባቴ ሆይ! በሰማይና በፊትህ በደልሁ፤ ወደፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ከተቀጣሪዎችህ እንደ አንዱ አድርገኝ፤”’ እለዋለሁ። ተነሥቶም ወደ አባቱ መጣ። እርሱም ገና ሩቅ ሳለ አባቱ አየውና አዘነለት፤ ሮጦም አንገቱን አቀፈውና ሳመው። ልጁም ‘አባቴ ሆይ! በሰማይና በፊትህ በደልሁ፤ ወደፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም፤’ አለው። አባቱ ግን አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው ‘ፈጥናችሁ ከሁሉ የተሻለ ልብስ አምጡና አልብሱት፤ በጣቱ ቀለበት በእግሩም ጫማ አጥልቁለት፤ የሰባውን ፍሪዳ አምጥታችሁ እረዱት፤ እንብላም ደስም ይበለን፤ ይህ ልጄ ሞቶ ነበርና ደግሞም ሕያው ሆኖአል፤ ጠፍቶም ነበር ተገኝቶአልም።’ ደስ ይላቸውም ጀመር።
“ታላቁ ልጁ በእርሻ ነበረ፤ መጥቶም ወደ ቤት በቀረበ ጊዜ የሙዚቃና የውዝዋዜ ድምፅ ሰማ፤ ከአገልጋዮቹም አንዱን ጠርቶ ‘ይህ ምንድነው?’ ብሎ ጠየቀ። እርሱም ‘ወንድምህ መጥቷል፤ በደኅና ስላገኘውም አባትህ የሰባውን ፍሪዳ አረደለት፤’ አለው። እርሱም ተቈጣ፤ ሊገባም አልፈለገም፤ አባቱም ወጥቶ ለመነው። እርሱ ግን መልሶ አባቱን ‘እነሆ፥ ይህን ያህል ዓመት አገለገልኩህ፤ ከትእዛዝህም ከቶ አልተላለፍሁም፤ ከወዳጆቼ ጋር እንድደሰት ለእኔ አንድ ጥቦት እንኳን ሰጥተኸኝ አታውቅም፤ ነገር ግን ይህ ልጅህ ገንዘብህን ከአመንዝራ ሴቶች ጋር አባክኖ በመጣ ጊዜ፥ የሰባውን ፍሪዳ አረድህለት፤’ አለው። እርሱ ግን እንዲህ አለው፦ ‘ልጄ ሆይ! አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፤ ለእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው፤ ዳሩ ግን ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበረ፤ ሕያው ስለ ሆነ ጠፍቶም ነበር፤ ስለ ተገኘ ደስ እንዲለን ፍሥሐም እንድናደርግ ይገባናል’።”
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንደምን ከረማችሁ!
እንደ የቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓተ አምልኮ አቆጣጠር ደንብ መሰረት ዛሬ የዐብይ ጾም አራተኛ ሰንበት እናከብራለን። ይህ የዐብይ ጾም አራተኛው እሑድ በተለምዶ "የደስታ ሰንበት" በመባል የሚታወቅ ሲሆን ትርጉሙም “ደስ ይበላችሁ” ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል የተወሰደ ነው። የዛሬው ቅዱስ ወንጌል የደስታችን ምክንያት እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ታላቅ ፍቅር በሕማማቱ፣ በሞቱ እና በትንሳኤው፣ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር እና እርስ በርሳችን ስላስታረቀን፣ እንዲሁም በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ላይ የተጠቀሰውና ጠፍቶ የነበረው ልጅ በፈጸመው ተግባር ተጸጽቶ ወደ አባቱ ቤት በተመለሰበት ወቅት አባቱ በደስታ እንደ ተቀበለው ሁሉ፣ እንዲሁም እግዚአብሔር እኛ ልጆቹ በኃጢያታችን ተጸጽተን፣ ንስሐ ገብተን ወደ ቤቱ በምንመለስበት ወቅት እግዚአብሔር እኛን ልጆቹን በደስታ እንደሚቀበል የምናሰላስልበት እለተ ሰንበት በመሆኑ የተነሳ ነው።
የዛሬው ቅዱስ ወንጌል የጠፋው ልጅ ምሳሌ ይተርካል (ሉቃ. 15፡11-32)። ሁልጊዜ በርኅራኄ እና በፍቅር ይቅር ወደሚለው ወደ እግዚአብሔር ልብ ይመራናል። ሁል ጊዜ እግዚአብሔር ይቅር ይላል። እኛ ነን እንጂ ይቅርታ ለመጠየቅ የሚሰለቸን እሱ ግን ሁል ጊዜ ይቅር ባይ ነው። ምሳሌው እግዚአብሔር እኛን የሚቀበል ብቻ ሳይሆን ድርሻው የነበረውን ንብረት ተካፍሎ ሂዶ የነበረው ልጅ ወደ ቤቱ በተመለሰ ጊዜ ልጁን ባየው ጊዜ ደስ ብሎት ግብዣ የሚያዘጋጅ አባት እንደሆነ ይነግረናል። እኛ ያ ልጅ ነን፣ እናም አብ ሁል ጊዜ ምን ያህል እንደሚወደንና እንደሚጠብቀን ለማሰብ እንችል ዘንድ ይረዳናል።
ነገር ግን በዚያው ምሳሌ ላይ በዚህ አብ ፊት ቂሙን የገለጠ ታላቅ ልጅም አለ። እኛንም ወደ ቀውስ ውስጥ ሊያስገባን ይችላል። እንደውም ይህ ታላቅ ልጅ በውስጣችን አለ እና ከጎኑ ለመሰለፍ እንፈተናለን፣ ቢያንስ በከፊል፡ ሁል ጊዜ ግዴታውን ይወጣ ነበር፣ ከቤት አልወጣም ነበር፣ እና ስለዚህ ያን ሁሉ ድርጊት ፈጽሞ፣ ንብረት ተካፍሎ፣ ገንዘቡን በትኖ መጥፎ ባህሪያትን ፈጽሞ እንደገና ወደ ቤቱ በተመለሰ ጊዜ አባቱ በደስታ ልጁን አቅፎ ስሞ፣ ድግስ አዘጋጅቶ በማየቱ ተቆጣ። እሱም ተቃወመና “እነሆ፥ ይህን ያህል ዓመት አገለገልኩህ፤ ከትእዛዝህም ከቶ አልተላለፍሁም፤ ከወዳጆቼ ጋር እንድደሰት ለእኔ አንድ ጥቦት እንኳን ሰጥተኸኝ አታውቅም፤ ነገር ግን ይህ ልጅህ ገንዘብህን ከአመንዝራ ሴቶች ጋር አባክኖ በመጣ ጊዜ፥ የሰባውን ፍሪዳ አረድህለት፤’ አለው" (ከቁ. 29-30) በቁጣም ወደ ቤት “አልገባህም!” አለ። ይህ የታላቁ ልጅ ቁጣ ነው።
እነዚህ ቃላት የታላቁን ልጅ ችግር ያሳያሉ። እሱ ከአባቱ ጋር ያለው ዝምድና የተመሰረተው ትዕዛዞችን በማክበር፣ በግዴታ ስሜት ላይ ብቻ የተመሰረተ ነበር። ይህ ደግሞ የእኛ ችግር ሊሆን ይችላል፣ በራሳችን እና በእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ችግር፡ እርሱ አባት መሆኑን አለማየት፣ እና በክልከላዎች እና ግዴታዎች የተሰራ ርቆ የሚገኝ ሃይማኖት መኖር። የዚህ ርቀት መዘዝ ደግሞ እንደ ወንድም ወይም እህት የማናየው ጎረቤታችን ግትርነት ነው። እንደውም በምሳሌው ላይ ታላቁ ልጅ ወንድሙን እንደ ወንድም አድርጎ አልቆጠረውም፣ "ያ ልጅህ" ሲል ነው የገለጸው፣ ወንድሜ አይደለም እንደሚል ተናገረ። ዞሮ ዞሮ ከቤት ውጭ መቆየትን አደጋ ላይ ይጥላል። እንዲያውም ጽሑፉ እንዲህ ይላል፡- “ሊገባም አልፈቀደም” (ቁ. 28)፣ ምክንያቱም ሌላኛው እዚያ ስለነበር ነው።
አባቱም ይህን አይቶ፣ “ልጄ ሆይ፣ አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፣ የእኔም የሆነው ሁሉ የአንተ ነው” (ቁ. 31) በማለት ለመለመን ወጣ። ለእሱ እያንዳንዱ ልጅ ሙሉ ህይወቱ መሆኑን እንዲረዳው ለማድረግ ይሞክራል። ወላጆች ይህንን ጠንቅቀው ያውቃሉ እና እንደ እግዚአብሔር ስሜት በጣም ቅርብ ናቸው። አንድ አባት በልቦለድ ውስጥ የሚናገረው ነገር በጣም ጥሩ ምሳሌ ነው፡- “አባት ስሆን እግዚአብሔርን ማን መሆኑ ተረዳው"። በዚህ ጊዜ በምሳሌው ላይ፣ አብ ልቡን ለታላቅ ልጁ ይከፍታል እና ሁለት ፍላጎቶችን ገልጿል፣ እነሱም ትእዛዛት ሳይሆኑ ለልቡ አስፈላጊ ነገሮች ናቸው፡- “ዳሩ ግን ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበረ፤ ሕያው ስለ ሆነ ጠፍቶም ነበር፤ ስለ ተገኘ ደስ እንዲለን ፍሥሐም እንድናደርግ ይገባናል’ (ቁ. 32)። እኛም አብ የሚፈልጋቸውን ሁለት ነገሮች በልባችን ውስጥ እንዳለን እንይ፡ ደስታ እና ፍሥሐ።
በመጀመሪያ ደስተኛ መሆን፤ ማለትም ንስሐ ለሚገቡ ወይም በመንገድ ላይ ላሉ ፣ በችግር ውስጥ ላሉ ወይም ከሩቅ ላሉ ሰዎች ቅርብ መሆናችንን ለማሳየት ነው። ይህን ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው? ምክንያቱም ይህ የአንድን ሰው ኃጢአት በማስታወስ የሚመጣውን ፍርሃት እና ተስፋ መቁረጥ ለማሸነፍ ይረዳል። ብዙውን ጊዜ ስህተት የሠሩ ሰዎች በልባቸው ውስጥ ነቀፋ ይሰማቸዋል። ርቀት፣ ግዴለሽነት እና ጨካኝ ቃላት አይረዱም። ስለዚ ልክ ጠፍቶ እንደተገኘው ልጅ ባት ሞቅ ያለ አቀባበል ልናደርጋላቸው ይገባል። “አባት ሆይ፣ ብዙ ነገሮችን እኮ አድርጓል” ብለው ሰዎች ቢወቅሱንም እኛ ግን ሞቅ ያለ አቀባበል ልናደርግላቸው ይገባል። ታዲያ እኛ ይህንን እናደርጋለን ወይ? በሩቅ ያሉትን እንፈልጋለን ወይ? እነርሱ ተመልሰው ሲመጡ ከእነሱ ጋር በደስታ ማክበር እንፈልጋለን? ክፍት ልብ ፣ በእውነተኛ ፍላጎት ማዳመጥ እና ግልፅ ፈገግታ ምን ያህል ጥሩ ሊሆን ይችላል ። ለማክበር፣ ምቾት እንዲሰማቸው ለማድረግ አይደለም! ጠፍቶ የተገኘው ልጅ አባት እንዲህ ሊል ይችል ነበር: "እሺ ልጄ ወደ ቤት ተመለስ፣ ወደ ሥራ ተመለስ፣ ወደ ክፍልህ ሂድ፣ እራስህን እና ስራህን አቋቁም! ይህ ደግሞ ይቅር ለማለት ጥሩ መንገድ ነበር። ግን አይሆንም! እግዚአብሔር ይቅር ሲለል እጅግ በጣም ይደሰታል፣ ይደግሳል። እና ጠፍቶ የተገኘው ልጅ አባት ልጁ ተመልሶ ስለመጣ በደስታ ያከብራል፣ ይደግሳል።
ከዚያም ልክ እንደ ጠፍቶ የተገኘው ልጅ አባት ሐሴት ልናደርግ ይገባል። ልቡ ከአምላክ ጋር የተሳሰረ ሰው የአንድን ሰው ንስሐ ሲመለከት፣ ስህተታቸው ምንም ያህል ከባድ ቢሆን ሐሴት ያደርጋሉ፣ እጅግ ደስ ይላቸዋል። እነሱ በስህተት ላይ አተኩረው አይቆዩም፣ በሰሩት ስህተት ላይ ጣታቸውን አይቀስሩም፣ ነገር ግን በበጎው ነገር ደስ ይበላችሁ የሌላ ሰው ጥቅሙ የእኔም ነውና! እና እኛ ታዲያ እንደዚህ በእንደዝ ዓይነት ሁኔታ ሌሎችን እንዴት እንደምንመለከት እናውቃለን ወይ?
አንድ ልቦለድ ታሪክ ለመጥቀስ እወዳለሁ፣ የአባትን ልብ ለማሳየት የሚረዳ ስለሆነ። ከሦስትና ከአራት ዓመታት በፊት ስለ አባካኙ ልጅ ከሙሉ ታሪክ ጋር አንድ የቲያትር ዝግጅት ነበር። እና በመጨረሻ ያ ልጅ ወደ አባቱ ለመመለስ ሲወስን ስለ ጉዳዩ ከጓደኛው ጋር ይነጋገራል እና "አባቴ እንደማይቀበለኝ፣ ይቅር እንዳማይለኝ እፈራለሁ" በማለት ተናግሯል። እናም ጓደኛው "ለአባትህ ደብዳቤ ላክና 'አባቴ ሆይ ንስሀ ገብቻለሁ፣ ወደ ቤት መመለስ እፈልጋለሁ፣ ነገር ግን ደስተኛ እንደምትሆን ወይም እንደማትሆን እርግጠኛ አይደለሁም። እኔን ለመቀበል ከፈለክ እባክህ ነጭ መሀረብ በመስኮቱ ላይ ስቀል" ብለህ ጻፍለት አለው። ልጁም ጽፎ ደብዳቤውን አስቀድሞ ላከው። ከዚያም ጉዞውን ጀመረ። እና ወደ ቤት ሲቃረብ በመንገዱ ላይ በመጨረሻው መታጠፊያ ላይ ቤቱን ከሩቅ አየ። ታዲያ ምን አየ? አንድ መሀረብ ብቻ አልነበረም የተሰቀለው፡ በነጭ መሀረብ የተሞላ ነበር፣ መስኮቶቹ፣ በሁሉም ቦታ! አብ እንዲህ በደስታ፣በሐሴት በደስታ ተቀበለን። ይህ አባታችን ነው!
ለሌሎች እንዴት መደሰት እንዳለብን እናውቃለን? ድንግል ማርያም ባልንጀሮቻችንን የምናይበት ብርሃን ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔርን ምሕረት እንዴት እንደምንቀበል እርሷ በአማላጅነቷ ትማረን።