ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ርህራሄ የእግዚአብሔር መሆኑን አስገነዘቡ።
ዛሬ ጠዋት መስከረም 6 ቀን 2012 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ፣ መስዋዕተ ቅዳሴውን ለተካፈሉት ካህናት እና ደናግል እንዲሁም ምዕመናን ባሰሙት ስብከተ ወንጌል፣ ርህራሄ የአካባቢያችን ነባራዊ እውኔታን በመገንዘብ ከልብ የምንችለውን ለማበርከት የምንነሳሳበት፣ ከእግዚአብሔር የሚሰጥ ውስጣዊ ፍላጎት መሆኑን አስረድተዋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ቅዱስነታቸው በስብከታቸው ወቅት እንደገለጹት ርህራሄ በሰዎች መካከል ልዩነትን ሳያደርጉ ልብን በመክፈት የሚደረግ ይሁን ብለዋል። ርህራሄ ወደ እውነተኛው ፍትሐዊነት እንድንደርስ ያግዛል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ርህራሄ ከዚህ በተጨማሪ ልባችን ዘግተን እንዳንቀመጥ ያደርጋል ብለዋል። የዛሬው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የሚመነጨው በዛሬው ዕለት ከተነበበው ከሉቃ. 7:11-17 ተወስዶ በተነበበው የወንጌል ክፍል መሆኑ ታውቋል። በዚህ የወንጌል ክፍል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ናይን በምትባል መንደር፣ ብቸኛ ልጇ ከሞተባት ከአንዲት መበለት ጋር የነበረውን ቆይታ የሚተርክ ታሪክ መሆኑ ታውቋል። በዚህ የወንጌል ክፍል ወንጌላዊው ሉቃስ፣ ኢየሱስ ከማለት ይልቅ ጌታም ባያት ጊዜ ራራላት እና አይዞሽ አታልቅሺ ማለቱን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ብቸኛ ልጇ የሞተባት መበለት የምትገኝበትን የሕይወት እውኔታን ኢየሱስ መመልከቱን ገልጸው፣ መመልከት ብቻም ሳይሆን የራራላት መሆኑንም አስታውሰው ርህራሄው የመነጨው ከሚታይ እውኔታ መሆኑንም አስረድተዋል።
የርህራሄ ልብ የእያንዳንዱን ነገር እውነታ በእርግጥ በዓይን ከሚታይበት አቅጣጫ መረዳት እንድንችል ያግዘናል ብለው ርህራሄ የልባችን መነጽር ነው ብለዋል። በቅዱሳት ወንጌላት ውስጥ በተደጋጋሚ ኢየሱስ ክርስቶስ በተለያዩ ሕይወት ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ርህራሄን እንደገለጸ ወይም እንዳሳየ መጠቀሱን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ርህራሄ ከእግዚአብሔርም በኩል የሚገለጽ ልባዊ ፍላጎት መሆኑን አስረድተዋል። ርህራሄ በአዲስ ዘመን ብቻ በኢየሱስ ክርስቶስ የተጀመረ ሳይሆን በብሉይ ኪዳን ውስጥ እግዚአብሔር ርህራሄውን የገለጠባቸው በርካታ አጋጣሚዎች መኖራቸውን ያስረዱት ቅዱስነታቸው፣ በኦሪት ዘጸ. 3፤7 ላይ፣ እግዚአብሔር “በግብጽ አገር የሚኖሩትን የሕዝቤን መከራ አይቻለሁ፣ ከአሰሪዎቻቸው ጭካኔ የተነሳ የሚያሰሙትን ጩሄት ሰምቻለሁ፣ ስቃዮቻቸውንም ተረድቻለሁ” በማለት ለሙሴ መናገሩን አስታውሰው፣ በዚህም የተነሳ ሕዝቡን ከችግራቸው እንዲያወጣ እግዚአብሔር ሙሴን ወድ ግብጽ አገር መላኩንም አስረድተዋል። የእኛ እግዚአብሔር የርህራሄ እግዚአብሔር ነው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ርህራሄን የሚገልጥበት ሃይልም አለው ብለዋል። ለእኛ ለልጆቹ የሰጠን አንዱ እና ታላቅ ስጦታ የርህራሄ ስጦታ እንደሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ እግዚአብሔር በርህራሄው ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ልኮልናል ብለዋል። በመሆኑም ርህራሄ የእግዚአብሔር ቋንቋ ነው ብለዋል።
እውነተኛ ርህራሄ በስሜት ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን በተግባር የሚገልጽ መሆን አለብት ብለው፣ ለምሳሌ አንድ እንስሳ ሲሞት የሚናሳየው ወይም የምንገልጸው ርህራሄ ስሜታዊ ብቻ ነው ብለው እውነተኛ ርህራሄ፣ የስዎችን ችግር ተገንዝበን የችግራቸው ተካፋይ ስንሆን እና ከደረሰባቸው ችግር እንዲወጡ የበኩላችንን እገዛ ስናደርግ ብቻ እውነተኛ ርህራሄ ይገለጣል ብለዋል። ጌታችንም ርህራሄውን የገለጠው በዚህ መንገድ ነው ብለዋል።
ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን ምሳሌ ከማቅረብ በተጨማሪ በቅዱስ ወንጌል ላይ የተገለጸውን ሌላ ምሳሌ ጠቅሰው ይህም ኢየሱስ ሐዋርያቱን ለሕዝቡ የሚበላ ነገር እንዲሰጧቸው ማዘዙንም አስታውሰው፣ ኢየሱስ የሐዋርያቱን ለዘብተኝነት በማየቱ ለሕዝቡ የሚበላ ነገር እንዲሰጡ ሐዋርያቱን ማዘዙን ገልጸው ኢየሱስ ክርስቶስ ለሕዝቡ የራራላቸው ሰብሳቢ እረኛ እንደሌለ መንጋ ተበታትንው ወይም ያለ ተንከባካቢ መቅረታቸውን በመመልከቱ ነው ብለዋል። በሌላ ወገን ሐዋርያቱም ሕዝቡ የሚገኝበትን ሁኔታ ተረድተው ማድረግ የሚችሉትን ሁሉ እንዲያደርጉላችው፣ የችግራቸው ተካፋይ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል ብለዋል። ስለዚህ ርህራሄ ልባዊ ስሜት ብቻ ሳይሆን እውነተኛነቱ የሚገለጠው በተግባር ሲታይ ነው ብለዋል።
ቅዱስነታቸው ስብከታቸውን በመቀጠል እንዳስረዱ በእርግጥ ርህራሄ የእግዚአብሔር ቋንቋ ነው ብለው ይህም የሆነበት ምሕረቱን እና ፍቅሩን የገለጠው በሰዎች መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት ሳያደርግ ለእያንዳንዳችን እንደሆነ ገልጸው በሰዎች መካከል የሚገለጥ ርህራሄ ግን ልዩነቶችን በማድረግ ሊቀርብ የሚችል መሆኑን ተናገረዋል። በዕለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ ልጇ የሞተባትን መበለት ኢየሱስ ክርስቶስ “አታልቅሺ” በማለት ማጽናናቱን አስታውሰው፣ ይህም ርሕራሄውን የገለጠበት አንዱ ምልክት ነው ብለዋል።