የጦርነት አዝማሚያ በሚታይባት ዓለማችን እውነተኛ ሰላም ዘር ሊዘራ የሚችለው በልባችን ውስጥ ብቻ ነው!
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ቀሳውስት፣ ደናግላን እና ምዕመናን በተገኙበት በትላንትናው እለት ማለትም በታኅሳስ 30/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ብሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ያሰሙት ስብከት በወቅቱ ከማርቆስ ወንጌል 6፡45-52 ተወስዶ በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መሰረቱን ያደርገ ስብከት እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በወቅቱ የሰላም መንገድ በተመለከተ እንደ ተናገሩት ሰላምን ማረጋገጥ ከተፈለገ በትንሹም ቢሆን ፍቅር መስጠት እና በጌታ መኖር እንደ ሚገባ ገልጸው እውነተኛ ሰላም በምድር ላይ ማረጋገጥ ከተፈለገ በቅድሚያ ሰላምን በልባችን ውስጥ ማረጋገጥ እና በልባችን ውስጥ መዝራት ይኖርብናል ብለዋል።
የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በስብከታቸው ጨምረው እንደገለጹት በቤተሰባችን፣ በአካባቢያችን እና በሥራ ቦታ “የጦርነት ዘር” የምንዘራ ከሆነ “ክርስቲያን ተብለን መጠራት” አንችልም፣ ጌታ መንፈስ ቅዱሱን ሰጥቶን በእርሱ እንድንኖር እና በሌሎች ላይ የጦርነት ነጋሪት ሳንጎስም እንዲሁ በቀላሉ ሌሎችን መውደድ እንችል ዘንድ እንዲያስተምረን ልንማጸነው ይገባል ብለዋል።
በእለቱ በቀዳሚነት ከአንደኛው የዮሐንስ መልእክት 4፡11-18 ላይ ተወስዶ በተነበበውና “እግዚአብሔር ፍቅር ነው፤ በፍቅር የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል፤ እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል” በሚለው የእግዚኣብሔር ቃል ላይ መስረቱን ባደርገው የስብከታቸው ሁለተኛ ክፍል ላይ ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት ክርስቲያኖች በፍቅር ኃይል ታግዘው በሰላም መንገድ ላይ መጓዝ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ስለ ሰላም ሲናገሩ እኛ ሰዎች ሁልጊዜም ቢሆን በቅድሚያ የምናስበው በዓለም ውስጥ ሰላምን ለማረጋገጥ ጦርነት ብቸኛው መንገድ እንደ ሆነ አድርገን ነው የምናስበው በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በእዚህ ሁኔታ የምንቀጥል ከሆንን ግን እውነተኛ ሰላም ለማረጋገጥ አንችልም ብለዋል። ዛሬም ቢሆን ብዙ የጦርነት እሳቶች እየተበራከቱ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት አዕምሮአችን ወዲያው የሚያስበው ሰላምን ለማረጋገጥ ጦርነት አስፈላጊ እንደ ሆነ አድርጎ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው ነገር ግን አዕምሮአችን ሰላም የሚገኘው ሰላምን በመመኘት እና ስለሰላም በመሥርት ሊሆን እንደ ሚገባው ማሰብ ይኖርበታል ብለዋል።
በእግዚኣብሔር ፍቅር መኖር
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ስብከታቸውን በቀጠሉበት ወቅት እንደ ገለጹት ሁላችንም በቤታችን ውስጥ ሰላም መኖር አለመኖሩን፣ ልባችን በሰላም ተሞልቱዋል ወይስ ደግሞ ጦርነትን ነው የሚናፍቀው? በጣም ብዙ ነገሮችን ለማግኘት በመቋመጥ ራሳችንን ታዋቂ ለማድረግ ነው እየሰራን የምንገኘው ወይስ በተቃራኒው ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች በማንሳት እያንዳንዳችን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል ብለዋል። ቅዱስነታቸው እንደ ሚሉት ከሆነ “የሰዎች ሰላም” ወይም የአንድ አገር ሰላም ለማረጋገጥ የሚያስችል ዘር በቅድሚያ “በልባችን ውስጥ መዘራት ይኖርበታል” የሚል እምነት እንዳላቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው በልባችን ውስጥ ሰላም ከሌለን በስተቀር በዓለም ውስጥ ሰላም እንዲረጋገጥ ማሰብ እንደማንችል ክርስቲያኖችን እንዲገነዘቡ ቅዱነታቸው አሳስበዋል። እናም ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በመጀመሪያ መልእክቱ (1ኛ ዮሐ. 4፡11-18) ላይ እንደ ገለጸው በውስጣችን የሰላም መንገድ እንዲኖር መሥራት ይኖርብናል፣ በእግዚኣብሔር ፍቅር መኖር የግድ ይለናል ብለዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ስብከታቸውን በቀጠሉበት ወቅት ጨምረው እንደ ገለጹት በውስጣችን ሰላም ለመፍጠር መንፈስ ቅዱስን በመላክ ሰላምን የሚያወርደው ጌታ መሆኑን” የጠቆሙት ቅዱስነታቸው ሁልጊዜ “በጌታ ከኖርን ልባችን ሰላም ያገኛል” እናም በኃጢያት ወይም በድክመት ውስጥ በምንወድቅበት ጊዜ የጌታ መንፈስ ከእዚህ ስህተት ወይም እንቅልፍ እንድንነቃ ሊያሳስበን ይችላል ብለዋል። እንደ ቅዱስነታቸው ገላለጽ ከሆነ በጌታ ፍቅር መኖር የምንችለው እርስ በእርሳችን ስንዋደድ ብቻ ነው በማለት ጨምረው ገልጸዋል።
ጦርነት ዲያቢሎስ የሚሰጠን ፈተና ነው!
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ስብከታቸውን በቀጠሉበት ወቅት ጨምረው እንደተናገሩት እውነተኛ ፍቅር የሚገለጸው እንዲሁ በይስሙላ በምናከናውናቸው ተግባሮቻችን ሳይሆን ስለሌሎች መልካም በማናገር ጭምር እንድ አሆነ ገልጸው አንድ ሰው ስለሌሎች መልካም ነገር በደንብ መናገር የማይችል ከሆነ፣ ስለሌሎች ክፉ ነገሮችን ይናገራል፣ ስለሌሎች መጥፎ ነገር መናገር ደግሞ በሌሎች ላይ ጦርነት እንደ ማወጅ ይቆጠራል ብለዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አጽንኦት ሰጥተው እንደ ገለጹት ፍቅር “በትንሽ ነገሮች” ይገለጻል። “በልቤ ውስጥ ጦርነት ካለ” በእርግጠኛነት በቤተሰቤ ፣ በአካባቢያዬ እና በሥራ ቦታዬ ጦርነት ይከሰታል” በማለት የተናገሩ ሲሆን ቅናት፣ ምቀኝነት፣ ስም ማጥፋት ወደ እርስ በእርስ ጦርነት እንድናመራ ያደርገናል ብለዋል።
“ክርስቲያኖች በሰላም መንፈስ ተሞለተው ነው የሚናገሩት ወይስ ደግሞ በጦርነት መነፈስ ተሞለትው ነው የሚናገሩት” የሚለውን ጥያቄ በማንሳት ራሳቸውን መጠየቅ ይኖርባቸዋል በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ብዙን ጊዜ በቤተሰብ ውስጥ እና በሥራ ቦታዎች የምናደርጋቸው ተግባሮቻችን ጦርነት ቀመስ የሆኑ ተግባሮች እንደ ሆኑ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።
ሰላም የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ መሆኑን የገጹት ቅዱስነታቸው መንፈስ ቅዱስ ሰላም እንድናገኝ የረዳናል፣ እኛ ራሳችን ነን ይህንን ሰላም የምናጎድፈው በእዚህም መሰረት ሁልጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተሞልተን ስለም በልባችን፣ በቤታችን በሥራ ቦታዎቻችን ይረጋገጥ ዘንድ የተቻለንን ጥረት ማደረግ ይኖርብናል ካሉ በኋላ የእለቱን ስብከት አጠናቀዋል።