ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴ ባሳረጉበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴ ባሳረጉበት ወቅት   (ANSA)

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “በመከራ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን እየረዱ የሚገኙ ሰዎችን ማመስገን ይገባናል አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመጋቢት 18/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ በአሁኑ ወቅት መላውን ዓለም እያስጨነቀ የሚገኘው እና የብዙ ሰዎችን ሕይወት በመቅጠፍ ላይ በሚገኘው በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሰዎችን በጸሎታቸው ያሰቡዋቸው ሲሆን በተጨማሪም በእዚህ ወረርሽኝ ምክንያት ተገልለው ለብቻቸው በቤታቸው ውስት ለመቆየተ የተገዱትን የእድሜ ባለጸጎች፣ በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት እየተሰቃዩ የሚገኙትን ቤተሰቦች፣ በእዚህ አስቸጋሪ ወቅት በበሽታው የተጠቁትን ሰዎች በማከም እና በማገዝ ላይ የሚገኙ ሰዎችን ሁሉ እግዚአብሔር ይረዳቸው ዘንድ ጸሎት ማድረጋቸው ተገልጹዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ሀ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ባደረጉት ስብከት እንደገለጹት ዲያቢሎስ ያነሳሳውን አጥፊ የሆነ ድርጊት ለመግታት አንዳንዴ ዝምታ አስፈላጊ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተመሳሳይ መልኩ የተቃጣበትን ጥቃት በዝምታ መጋፈጡን ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።

በእዚህ የኮሮና ቫይረስ በተስፋፋበት በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ችግር ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን በማገልገል ላይ ያሉትን ሰዎች ቅዱስነታቸው ያመሰገኑ ሲሆን ለራሳቸው ሕይወት ሳይሳሱ ሌሎችን ለማገዝ በመትጋት ላይ የሚገኙ ሰዎችን እግዚአብሔር ይረዳቸው ዘንድ ቅዱስነታቸው ጸሎታቸው እንደ ሆነ አክለው ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው ስብከታቸውን በቀጠሉበት ወቅት ጨምረው እንደ ገለጹት “በእነዚህ ቀናት ከሌላ ጊዜ በበለጠ መልኩ ብዙ ሰዎች በጭንቀት ውስጥ ይገኛሉ” በማለት የተናገሩ ሲሆን በአጠቃላይ በቂ ኑሮ ለሌላቸው ቤተሰቦች፣ ብቻቸውን ለሚኖሩ አዛውንቶች፣ በሆስፒታል ውስጥ ለሚገኙ በሽተኞች፣ በችግር ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ለመርዳት ለሚታትሩ ሰዎች በሙሉ ጸሎት ማድረጋቸውን እንደ ሚቀጥሉ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል። በምዕመናን ልብ ውስጥ ይህንን የርህራሔ መንፈስ ያነሳሳውን እግዚአብሔር ማመስገን ይኖርብናል ብለዋል።

በወቅቱ በተደረገው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ከዮሐንስ ወንጌል 7፡ 1-2. 10. 25-30 ላይ ተወስዶ በተነበበውና “በዚህ ጊዜ በኢየሩሳሌም የነበሩ አንዳንድ ሰዎች እንዲህ አሉ፤ “ሊገድሉት የሚፈልጉት ሰው ይህ አይደለምን? ይኸው እርሱ በአደባባይ ይናገራል፤ አንድም ቃል አይናገሩትም፤ ክርስቶስ ነው ብለው ባለ ሥልጣኖቹም ተቀብለውት ይሆን? ይህ ሰው ግን ከየት እንደሆነ እኛ እናውቃለን፤ ክርስቶስ ሲመጣ እኮ ከየት እንደሆነ ማንም አያውቅም።” ኢየሱስ በቤተ መቅደስ አደባባይ ሲያስተምር ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፤ “አዎን፣ እኔን ታውቁኛላችሁ፤ ከየት እንደሆንሁም ታውቃላችሁ። እኔ እዚህ ያለሁት በገዛ ራሴ አይደለም፤ ነገር ግን የላከኝ እርሱ እውነተኛ ነው። እናንተ አታውቁትም፤ እኔ ግን ከእርሱ ዘንድ ስለ ሆንሁ፣ እርሱም ስለ ላከኝ ዐውቀዋለሁ።”ስለዚህ ሊይዙት ፈለጉ፤ ነገር ግን ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም እጁን አላሳረፈበትም” በሚለው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መሰረቱን ያደረገ ስብከት እንደ ነበረ ተገልጹዋል።

በእዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሰረቱን ባደረገው ስብከት ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት ኢየሱስን ሊገሉት የተነሱትን ሰዎች ልብ ያነሳሳው ዲያቢሎስ እንደ ነበረ የገለጹ ሲሆን “ከእያንዳንዱ ክፉ አስተሳሰብ ጀርባ ዲያቢሎስ በመኖሩ የተነሳ ነው ብለዋል። ከዲያቢሎስ ጋር መሟገት አይችልም፣ ማደረግ የምንችለው ነገር ቢኖር ኢየሱስ እንዳደረገው ዝምታን መምረጥ ነው” ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን በትናንሽ ዕለታዊ ክንውኖችም እንኳ መከተል ያለብን የሕይወት ዘይቤ ሊሆን እንደ ሚገባው ቅዱስነታቸው አክለው ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው ስብከታቸውን ሲቀጥሉ የሚከተለውን ብለዋል . . .

የመጀመሪያው ንባብ (መጽሐፈ ጥበብ 2፡1. 12-22) በኢየሱስ ላይ ምን እንደሚደርስበት አስቀድሞ የተነገረ ትንቢት ነው። ቀጥሎ ስለሚከሰተው ነገር ታሪካዊ መገለጫ ይመስላል። “ ኑ ጻዲቁን እንግደለው፣ ለእኛ ጭንቀት እና ጽኑዕ ሆኖብናልና፣ ሥራችንንም ይቃወማል ሕግ በመጣሳችን ያሽሟጥጣልና፣ የትምሕርታችንንም በደል ይስብካልና። ‘እግዚአብሔርንም ማወቅ በእኔ አለ’ ይላል፣ ራሱንም የእግዚአብሔር ልጅ ያደርጋል። ሕሊናችንን የሚዘልፍ ሆኖብናል። መልኩም ለእኛ ጭንቅ ሆኖብናል። አኗኗሩም ከሌላ ጋር አይመሳሰልም፣ መንገዱም ሊዩ ነው። በእርሱ ዘንድ የተናቅን ሆነናል፣ ከርኩሰትም እንደ ሚርቅ ከመንገዳችን ይርቃል። የጻድቃንን መጨረሻ ያመሰግናል፣ እግዚአብሔር አባቱ እንደ ሆነ ይመካል” በሚለው የመጽሐፈ ጥበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሰረቱን ያደርገ ስብከት ነበር።  

ኢየሱስ በመስቀል ላይ በነበረበት ወቅት ሕዝቡ “እስቲ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆነ መጥቶ ያድነው” በማለት የተናገሩትን እናስብ። ከዚያ የድርጊት መርሃግብር “እርሱ ያለውን ትህትና ለማወቅ እና የፅናት መንፈሱን ለመፈተን፣ የሞት ፍርድ እንፍረድበት” እርሱ እንደ ተናገረው አባቱ መጥቶ ያድነው” በሚል አስተሳሰብ ተነሳስተው እየሱስን ሊገሉት ፈለጉ። ስለእርሱ የተነገሩት ትንቢቶች በትክክል የተፈጸሙ ሲሆን አይሁዳዊያንም ኢየሱስን ሊገሉት እንደ ፈለጉ መጽሐፍ ቅዱሳችን ይናገራል። ከዛም እሱን ሊይዙትም ሞክረዋል - ቅዱስ ወንጌል እንደ ሚናገረው “ነገር ግን ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም እጆቹን በእርሱ ላይ መጫን አልደፈረም” በማለት ይናገራል።

ይህ ትንቢት በጣም በዝርዝር የተቀመጠ ነው። የነዚህ ክፉ ሰዎች ተግባር ዕቅድ በዝርዝር ተቀምጡዋል፣ ጊዜ አናባክን ዓመፅ እና መከራ በእርሱ ላይ በማድረስ እርሱ ‘የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ’ የሚለውን አባባሉን እንፈታተን በማለት ይነሳሳሉ። ምን ያሕል የትዕግስት መንፈስ እንዳለው ሞክረን እንወቅ፣ ወጥመድ እናበጅለት፣ በወጥመዳችንም ውስጥ እናስገባው፣ እንጣለው በማለት በእርሱ ላይ ያላቸውን የጥላቻ መንፈስ በተግባር ለማሳየት ይነሳሳሉ፣ መጥፎ የድርጊት መርሃ ግብር ይቀርጻሉ። በእርግጥ የእዚህ ዓይነቱ ተግባር የክፉ መንፈስ ነጸብራቅ ነው፣ ከእያንዳንዱ ክፉ ሐሳብ ጀርባ ደግሞ ሁል ጊዜ ዲያቢሎስ ይገኛል። እስቲ በመጽሐፈ ኢዮብ በመጀመሪያዎቹ ምዕራፍ ውስጥ የተጠቀሰውን እንመልከት። እግዚአብሔር በኢዮብ አኗኗሩ ረክቷል።  ዲያቢሎስ ግን እንዲህ አለው- “አዎ ሁሉም ነገር ስላለው ነው አንተን የሚወድህ! ሁሉም ነገር ባይኖረው ኖሮ እንዲህ አይታዘዝህም ነበር። እስቲ እንፈትነው! እንሞክረው! አለ። እናም በመጀመሪያ ዲያቢሎስ ንብረቱን ይወስዳል፣ ከዚያም ጤናውን ይወስዳል፣ ኢዮብ በጭራሽ ራሱን ከእግዚአብሔር አልለየም ነገር፣ ግን ዲያቢሎስ የሚሠራው ሥራ ቁጣ ውስጥ እንዲገባ አድርጎት ነበር። ሁልጊዜ ከቁጣው ሁሉ ጀርባ የእግዚአብሔርን ሥራ የሚያጠፋ ዲያቢሎስ አለ። በመጥፎ ክርክር ወይም በጠላትነት መንፈስ በስተጀርባ ዲያቢሎስ አለ፣ ይህ የተለመደ እለታዊ የሆነ ፈተናችን ነው። ቁጣ በሚኖርበት አከባቢ ሁሉ ዲያቢሎስ አለ፣ ቁጣውም ስውር ነው። ዲያቢሎስ በኢየሱስ ላይ ብቻ ሳይሆን በክርስቲያኖችም ላይ ያደርሰውን ስደት እንዴት እንደሆነ እናስብ። ወደ ክህደት መንፈስ ለማምጣት እና ከእግዚአብሔር ርቀው እንዲሄዱ ለማድረግ እጅግ በጣም የተወሳሰበ መንገዱን በእኛ ላይ ይዘረጋል። በእየለቱ ተግባራችን ተለዋዋጭ በሆነ መልኩ ይህንን ይተገብራል። ተዓማኒነት ያለው የማሰብ ችሎታ እንዳይኖረን ያደርጋል።

በቁጣ ጊዜ ምን ማደረግ እንችላለን? ሁለት ነገሮች ብቻ ማከናወን ይኖርብናል። በቁጣ ከተሞሉ ሰዎች ጋር መነጋገር የለብንም፣ ምክንያቱም ከእነዚህ ሰዎች ቁጣ ጀርባ ዲያቢሎስ አለ፣ የእነዚህ ዓይነት ሰዎችን ልብ ዲያቢሎስ በቁጣ ሐሳብ ስለሞላው ከእነርሱ ጋር መነጋገር አይኖርብንም። የእነርሱ የድርጊት መርሃ ግብር ምን እንደሆነ አውቀናል። ታዲያ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ኢየሱስ እንዳደረገው ዝም ማለት ይጠበቅብናል። በእነዚህ ሁሉ ክሶች ፊት ኢየሱስ ዝም እንዳለ በቅዱስ ወንጌል ውስጥ ስናነበው አስገራሚ የሆነ ነገር ነው። በቁጣ መንፈስ ፊት ለፊት ዝም ማለት ተገቢ ነው። ኢየሱስ ምንም ዓይነት ቃል እንዳልተናገረ ሲረዱ እነርሱም ዝም ማለት ይጀምራሉ። ዝም ብሎ ኢየሱስ ፍቅር አሳይቷል። ይህ በቁጣ ፊት የጻድቃን ዝምታ የሚያሳይ ሁኔታ ነው። እናም ይህ ተገቢ ነው። ኢየሱስ መከራውን በዝምታ ተቀበለ። ዝምታ የቁጣ ተቃራኒ ነው።  በኅብረተሰቡ፣ በአከባቢው፣ በሥራ ቦታ. . . ወዘተ ቁጣ ሲያጋጥመን በዝምታ ማሳለፍ ይኖርብናል።

በሁለተኛ ደረጃ ከመጥፎ መንፈስ ጋር ለመዋጋት እንዲረዳን ጌታን እንለምናለን፣ መወያየት ሲኖርብን ብቻ መወያየት እንችል ዘንድ እንዲረዳን እንለምነው። በቁጣ ወቅት ዝም ለማለት እንችል ዘንድ ብርታቱን እንዲሰጠን እግዚአብሔርን እንለምነው። እለታዊ በሆነ መልኩ ቁጣ በሚያጋጥመን ወቅት በትዕግስት ማለፍ እንችል ዘንደ እግዚአብሔር እንዲረዳን እንጠይቀው።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ከእዚህ በላይ ያስነበብናችሁን ስብከት ካደረጉ በኋላ እራሳቸው በወቅቱ ያሳረጉትን መስዋዕተ ቅዳሴ በቴለቪዢን መስኮት በመከታተል ላይ የነበሩትን ምዕመናን እርሳቸው የሚያደርጉትን የቅዱስ ቁርባን ቡራኬ በእየቤታቸው ሆነው የሚከታተሉ ምዕመናን ከእርሳቸው ጋር በጸሎት መንፈስ በመሆን የሚከተለውን ጸሎት አብረዋቸው እንዲደግሙ ጥሪ ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው የሚከተለውን የቅዱስ ቁርባን ቡራኬ ጸሎት ከደገሙ በኋላ ስብከታቸውን አጠናቀዋል።

ኢየሱስ ሆይ! በቅዱሳት ምስጢራት ውስጥ አንተ እንደምትገኝ በእውነት አምናለሁ፤ ከሁሉ በላይ እወድሃለሁ፣ በሕይወቴ ውስጥ አንተ እንድትገኝ እመኛለሁ። በዚህ አስፈሪ ወቅት የአንተን ስጋ እና ደም መቀበል ባልችልም ከዚህ በፊት እንዳደረከው ሁሉ ዛሬም በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት በልቤ ውስጥ ግባ። ካንተ ላለመለየት ወስኜአለሁና፣በሙሉ ልቤ እቀበልሃለሁ”!

27 March 2020, 13:52
ሁሉንም ያንብቡ >