ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “የሰውን ልብ ወደ ኢየሱስ የሚስበው እግዚአብሔር አብ ብቻ ነው” አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዛሬ ሚያዝያ 22/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም ተስፋፍቶ በሚገኘው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተጎጂ ለሆኑ በተለያየ የዓለማችን ክፍሎች ይኖሩ የነበሩ ሕይወታቸውን በእዚህ ወረርሽኝ ላጡ ሰዎች ጸሎት ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን  በተለይም ስማቸው የማይታወቅ በጅምላ መቃብር የተቀበሩትን ሰዎች በጸሎታቸው ማሰባቸው ተገልጿል።

የቫቲካን ዜና

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በወቅቱ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት ኢየሱስ ወደ እዚህ ምድር የተላከው ሰዎች ቀድም ሲል የነበራቸውን እመነት እንዲቀይሩ ለማድረግ ሳይሆን ነገር ግን እምነቱን በሕይወቱ በመተግበር ምስክርነት ለመስጠት እና በጸሎቱ የሰዎችን ልብ ወደ አብ ለመሳብ እንደ ተላከ የገለጹ ሲሆን የሰውን ልብ ወደ ኢየሱስ የሚስበው ግን እርሱ እግዚአብሔር አብ ብቻ ነው ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በዕለቱ ያደረጉት ስብከት ፊልጶስና ኢትዮጰያዊው ጃንደረባ መገናኘታቸውን በሚገልጸው በሚከተለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሰረቱን ያደረግ ነበር የጌታም መልአክ ፊልጶስን፣ “ተነሥተህ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ በሚያወርደው በምድረ በዳው መንገድ ሂድ” አለው፤ እርሱም ተነሥቶ ሄደ። እነሆ የኢትዮጵያ ንግሥት የህንደኬ ባለሟልና የሀብት ንብረቷ ሁሉ አዛዥ የሆነ አንድ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ አገኘ። ይህም ሰው ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር። ሲመለስም በሠረገላ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር። መንፈስም ፊልጶስን፣ “ሂድ፤ ወደዚህ ሠረገላ ቅረብ” አለው። ፊልጶስም ፈጥኖ ወደ ሠረገላው ሄደ፤ ጃንደረባውም የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ ሰምቶ፣ “ለመሆኑ፣ የምታነበውን ታስተውለዋለህን?” አለው።

ጃንደረባውም፣ “የሚያስረዳኝ ሰው ሳይኖር እንዴት አድርጌ አስተውላለሁ” አለው፤ እርሱም ወደ ሠረገላው ወጥቶ አብሮት እንዲቀመጥ ፊልጶስን ለመነው […] ፊልጶስም አፉን ከፈተ፤ ከዚሁም መጽሐፍ ክፍል ጀምሮ ስለ ኢየሱስ ወንጌል ሰበከለት።በመጓዝ ላይ ሳሉም ውሃ ካለበት ስፍራ ደረሱ፤ ጃንደረባውም፣ “እነሆ፤ ውሃ እዚህ አለ፤ ታዲያ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምን ነገር አለ?” አለው። ፊልጶስም፣ “በፍጹም ልብህ ካመንህ መጠመቅ ትችላለህ” አለው። ጃንደረባውም፣ “ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምናለሁ” ሲል መለሰለት፤ ሠረገላውም እንዲቆም አዘዘ። ከዚያም ሁለቱ አብረው ወደ ውሃው ወረዱ፤ ፊልጶስም ጃንደረባውን አጠመቀው። ከውሃውም በወጡ ጊዜ፣ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ነጥቆ ወሰደው፤ ጃንደረባውም ከዚህ በኋላ አላየውም፤ ሆኖም ደስ እያለውም ጒዞውን ቀጠለ” (ሐዋ. 8፡ 26-26) በተጠቀሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሰረቱን ያደረገ ነበር።

የዛሬን ቅዱስ ወንጌል (ዮሐንስ 6፡ 44-51) እግዚአብሔር አብ ሐሳባችንን በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እንድናደር እንደ ሚጋብዘን የገለጹት ቅዱስነታቸው ያለዚህ ጣልቃ ገብነት የክርስቶስን ምስጢር ማወቅ አንችልም ብለዋል። ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ የነብዩ ኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ በነበረበት ወቅት አብ  አዎንታዊ የሆነ የመቅበጥበጥ ስሜት በልቡ ውስጥ እንዲቀሰቀስ እንዳደረገ በስብከታቸው የገለጹት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ይህ የእኛን ተልእኮው ይመለከታል፣ የሕዝቡን ልብ የምንለውጠው እኛ ሳንሆን አብ ራሱ ነው ማለታቸው ተገልጿል። እኛ በቀላሉ የእምነት ምስክርነት መስጠት እንችላለን፣ የሰውን ልብ ወደ እምነት የሚስበው ግን እርሱ እግዚአብሔር አብ ብቻ ነው በማለት ሰብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው አብ የሰዎችን ልብ ወደ ኢየሱስ እንዲስብ መጸለይ አስፈላጊ ነው፣ የሕይወት ምስክርነት እና ጸሎት አስፈላጊ ነገሮች ናቸው ብለዋል። ያለ በሕይወት የተደገፈ ምስክርነት እና ፀሎት በጣም ጥሩ የሆነ የግብረገብ ትምህርት ማስተማር ትችል ይሆናል፣ ብዙ ጥሩ ነገሮችን ማድረግ ትችል ይሆናል፣ ነገር ግን ጸሎት እና የሕይወት ምስክርነት ካልታከለበት አብ ሰዎችን ወደ ኢየሱስ ለመሳብ ለሚያደርገው ጥረት ሁኔታዎችን አያመቻችለትም ብለዋል። የእኛ የሕይወት ምስክርነት ለሰዎች በር ይከፍታል፣ ፀሎታችን ደግሞ  ሰዎች ልባቸውን ለአብ እንዲከፍቱ ያደርጋል በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው የሕይወት ምስክርነት እና ጸሎት ለሐዋርያዊ ተግባር እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ናቸው ብለዋል። የሕይወት ምስክርነት እና ጸሎት እያንዳንዱ ክርስቲያን በእለት ተእለት ተግባሩ ሊያንጸባርቃቸው  የሚገባቸው ነገሮች እንደ ሆኑ በመጥቀስ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “እስቲ እራሳችንን እንጠይቅ- በአኗኗሬ እመሰክራለሁ ወይ? አብ ሰዎችን ወደ ኢየሱስ እንዲስባቸው እጸልያለሁ ወይ?” በማለት ጥያቄ ያነሱ ሲሆን ወንጌልን ለመስበክ መሄድ ማለት ሰዎች የእኛን ሐይማኖት እንዲከተሉ ማደረግ ማለት አይደለም፣ ይህ በፍጹም የቅዱስ ወንጌል ተልዕኮ ሊሆን አይችልም፣ ምክንያቱም የሰዎች ልብ እንዲነካ የምናድርገው እኛ ሳንሆን እግዚአብሔር ነው፣ ሰዎችን ወደ ኢየሱስ ለመሳብ እንዲችል እኛ እምነታችንን በሕይወት በመመስከር እና ጸሎት በማድረግ መትጋት እንችል ዘንድ ጌታ ጸጋውን እንዲሰጠን እንማጸነው ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው የእለቱን ስብከት አጠናቀዏል።

30 April 2020, 10:50
ሁሉንም ያንብቡ >