ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣                ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የአገራት መሪዎች ሕዝባቸውን ለመርዳት ተባብረው እንዲሠሩ ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቅዳሜ ሚያዝያ 24/2012 ዓ. ም. በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት፣ አደራ የተጣለባቸው የአገር መሪዎች ሃላፊነታቸውን በታማኝነት እንዲወጡት፣ ለሕዝባቸው መልካም ሥራን እንዲያበረክቱ በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት መካከል ባሰሙት ስብከት፣ ዓለማችን በኮሮና ወረርሽኝ በሚሰቃይበት ባሁኑ ወቅት በእምነታችን ጸንተን እንድንቆም፣ ታማኞች ሆነን እንድንገኝ በማለት ከእግዚአብሔር ዘንድ የመንፈስ ቅዱስ ድጋፍ ለምነዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን 

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በምትከተል የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ዘንድ የብርሃነ ትንሳኤ መታሰቢያ በዓል በተከበረ በሦስተኛ ሳምንት ውስጥ በሆነው በዛሬው ዕለት ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የአገራት መሪዎችን አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው እንደገለጹት የሕዝብ አደራ ለተጣለባቸው የአገር መሪዎች መጸለይ ይኖርብናል ብለው፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ባስከተለው የመከራ እና የስቃይ ወቅት ለሕዝብ መደረግ ያለበት እገዛ እንዳይጓደል በከዝቅተኛ የመንግሥት ሃላፊነት እስከ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት በሙሉ በትጋት እንዲሰሩ የሚያስችል የእግዚአብሔር እርዳታ ለምነው፣ በመካከላቸው ልዩነቶች ቢኖሩም በአስቸጋሪ ወቅት ሕዝባቸውን ለመጥቀም ሲሉ እንዲተባበሩ አደራ ብለዋል። ዛሬ ማለዳ 300 ልዩ ልዩ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ማሕበራት በጸሎት መተባበራቸውን ገልጸዋል።

ከሐዋ. 9:31-42 ተወስዶ በተነበበው የዕለቱ ንባብ ላይ በማተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በሰማሪያ አገር ሁሉ የሚገኝ የመጀመሪያው የክርስቲያን ማህበረሰብ ሰላምን አግኝቶ ጌታን እያከበረ ከመንፈስ ቅዱስ በኩል መጽናናትን በማግኘት ከቀን ወደ ቀን በቁጥር እያደገ መምጣቱን አስታውሰዋል። ሐዋርያው ጴጥሮስም በሊዳ ወደሚኖሩት ቅዱሳን ዘንድ በመሄድ ሁለት አስደናስቂ ሥራዎችን እንደፈጸመ ገልጸው የመጀመሪያው፣ ስምንት ዓመት ሙሉ አልጋ ላይ የቆየ፣ ኤኒያ የተባለውን ሽባን በማግኘት “ኢየሱስ ክርስቶስ ፈውሶሃልና አልጋህን አንጥፍ” ብሎ ማሰናበቱን አስታውሰዋል። በዚህም የልዳ ነዋሪዎች እርሱን አይተው በኢየሱስ ማመናቸውን አስረድተዋል። ሐዋርያው ጴጥሮስ በሁለተኛ ድንቅ ሥራው፣ ታማ የሞተች ጣቢታ የተባለች ሴት ከሞት ማስነሳቱን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። ነገሮች ተሟልተው ሲገኙ ቤተክርስቲያን ታድጋለች ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ቤተክርስቲያን ስደት እና መከራ ሲያጋጥማት የክርስቲያን ማኅበረሰብ ስቃይ ውስጥ እንደሚወድቅ አስረድተዋል። ከዮሐ. 6: 60-69 ተወስዶ በተነበበው የዕለቱ ወንጌል ኢየሱስ “ሕያው አብ እንደላከኝ እና እኔም በእርሱ ሕያው እንደሆንሁ ሥጋዬን የሚበላ ሁሉ በእኔ ሕያው ይሆናል፤ እንግዲህ ከሰማይ የወረደ እንጀራ ይህ ነው፤ እርሱም አባታችሁ እንደበሉት ዓይነት አይደለም፤ ምክንያቱም ያን እንጀራ የበሉ ሞተዋል፤ ይህን እንጀራ የሚበሉ ግን ለዘለዓለም ይኖራሉ” ባላቸው ጊዜ ከደቀመዛሙርቱ መካከል ብዙዎቹ ይህን በሰሙ ጊዜ “ይህ ንግግር ከባድ ነው፤ ማን ሊቀበለው ይችላል” በማለት ማጉረምረማችውን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰባ ሁለት ደቀ መዛሙርት እና አስራ ሁለት ሐዋርያት መካከል አንዳንዶች እርሱን እንደሚክዱ በማወቅ “ከአብ ካልተሰጠ በቀር ማንም ወደ እኔ ሊመጣ አይችልም” ማለቱን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ እግዚአብሔር አብ ወደ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ በመጥራት ከችግር የምንወጣበትን መንገድ ያዘጋጅልናል ብለዋል።

ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ብዙዎቹ ኢየሱስ ክርስቶስን መከተል አቋርጠው ወደ ኋላ የተመለሱ መኖራቸውን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በኢየሱስ የማስተማር ሥራ እና በፈውስ አገልግሎቱ ቢማረኩም አዳንድ ጊዜ ከሚከተሉት ሕግ ጋር የማይጣጣሙ ንግግሮችን ሲናገር ጥለውት እንደሚሄዱ፣ በትንሳኤው ዕለት ማልደው ወደ ኢየሱስ መካነ መቃብር የሄዱት ሴቶች ወታደሮች ይዘው እንዳያሰቃዩኣቸው በሚል ስጋት ሥፍራውን ለቀው ለመሄድ መቻኮላቸውን፣ መቃብሩን ይጠብቁ የነበሩ ወታደሮችም የኢየሱስ ክርስቶስ እርጋት ቢያምኑም እምነታቸውን በመካድ መመስከር ያልፈለጉ መሆኑን አስረድተዋል።

የችግር እና የመከራ ወቅት የማይታጠፍ ምርጫን የምናደርግበት ወቅት ነው ያሉት ቅዱስነታቸው፣ እያንዳንዳችን በሕይወታችን ውስጥ መከራ ሲደርስብን፣ በቤተሰብ ፣ በጋብቻ ሕይወት ፣ በማኅበራዊ ሕይወት ፣ በሥራ ዘርፍ እና በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅትም ችግር ሲያጋጥመን ሌላ አቅጣጫን ከመያዝ ይልቅ በዓላማ ጽናት በርትተን ወደ ፊት መጓዝ እንዳለብን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። አሥራ ሁለቱን ሐዋርያት በመወከል የተናገረው ሐዋርያው ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆንክ እናውቃለን፣ አንተን አምነን ስንከተልህ ቆይተናል፤ አሁን ወደ ማን እንሄዳለን” ማለቱን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ይህ በችግር እና በመከራ ጊዜ ጥንካሬን እና ብርታት የሚሰጥ መሆኑን አስረድተው፣ በሕይወታችን ውስጥ የሰላም እና የችግር ጊዜ እንደሚኖር በማወቅ ይህን ጊዜ ለማለፍ የምንችልበትን መንገድ ማወቅ አስፈላጊ ነው ብለዋል።  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዕለቱ ባቀረቡት ስብከታቸው ፣ በቤተሰብ መካከል ፣ በጎረቤት መካከል ፣ በሥራ ቦታ ፣ በማኅበራዊ ሕይወት ፣ በአገሮች መካከል እና በዓለም ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮችን በሙሉ የምናሸንፍበትን የመንፈስ ቅዱስ ኃይል እግዚአብሔር እንዲሰጠን፣ የመከራ ጊዜን በተስፋ አልፈን በሰላም የምንኖርበትን ጊዜ በመለመን የዕለቱን ስብከታቸውን አጠቃለዋል።

02 May 2020, 19:43
ሁሉንም ያንብቡ >