ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “እኛ በኢየሱስ ውስጥ፣ ኢየሱስ ደግሞ በእኛ ውስጥ ሊኖር ይገባል” አሉ!

ዛሬ ግንቦት 05/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ውስጥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ በዚህ አሁን ባለንበት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት በተለያዩ የማሕበራዊ የመገናኛ መስመሮችን እና ኢንተርኔት በመጠቀም የመማር የማስተማር ሂደቱን በመቀጠሉ ምስጋና ማቅረባቸው የተገለጸ ሲሆን የዕለቱ መስዋዕተ ቅዳሴ የጸሎት ሐሳብ ለተማሪዎች እና መምህራኖቻቸው አሁንም ጌታ ብርታት እና ድፍረት እንዲሰጣቸው ቅዱስነታቸው ጸሎት እንዳደረጉላቸው ተገልጿል። ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት የክርስትና ሕይወት ምስጢር መገለጫ “በእኔ ኑሩ” የሚለው ሲሆን እኛ ከኢየሱስ ጋር ኢየሱስ ከእኛ ጋር መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርብናል፣ “እኛ በኢየሱስ ውስጥ፣ ኢየሱስ ደግሞ በእኛ ውስጥ ሊኖር ይገባል”  ብለዋል።

የቫቲካን ዜና

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዕለቱ ያሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በእሁኑ ወቅት የምንገኘው በአምስተኛው የፋሲካ ሳምንት ረቡዕ ዕለት ላይ ተከብሮ ባለፈው በፖርቹጋል አገር የምትገኘውና እ.አ.አ በግንቦት 13/1917 ዓ.ም የፋጢማ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለሦስት እረኛ ልጆች ለመጀመሪያ ጊዜ የተገለጸችበት እለት በሚታሰብበት የዕለቱ ሥረዓተ አምልኮ ላይ መሰረቱን ያደረገ ነበር። ቅዱስነታቸው በስርዓተ አምልኮ መግቢያ ላይ የጸሎት ሐሳባቸውን በተማሪዎች እና በመምህራን ላይ በማደረግ የሚከተለውን ጸሎት በመጸለይ ነበር የጀመሩት

ዛሬ የመማር ሂደቱ ወደ ፊት እንዲቀጥል በጥሞና በማጥናት ላይ ለሚያገኙ ተማሪዎች እና እንዲሁም አዳዲስ የማስተማሪያ መንገዶችን በመጠቀም የማስተማር ሂደቱ እንዲቀጥል ጥረት በማደረግ ላይ ለሚገኙ መምህራን -ጌታ በዚህ ጉዞ ላይ እንዲረዳቸው ፣ ብርታት እንዲሰጣቸው እና ስኬታማ እንዲያደርጋቸው እንጸልያለን።

በዕለቱ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ያደረጉት ስብከት ትኩረቱን አድርጎ የነበረው “እውነተኛው የወይን ተክል እኔ ነኝ፤ አትክልተኛውም አባቴ ነው። እርሱም በእኔ ያለውን፣ የማያፈራውን ቅርንጫፍ ሁሉ ቈርጦ ይጥለዋል፤ ፍሬ የሚያፈራውን ቅርንጫፍ ሁሉ ግን የበለጠ እንዲያፈራ ይገርዘዋል። ከነገርኋችሁ ቃል የተነሣ እናንተ አሁን ንጹሓን ናችሁ። በእኔ ኑሩ፤ እኔም በእናንተ እኖራለሁ። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ካልሆነ በቀር ብቻውን ፍሬ ሊያፈራ አይችልም፤ እናንተም በእኔ ካልኖራችሁ ፍሬ ልታፈሩ አትችሉም” (ዮሐ 15 1-8) በሚለው ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ የወይን ግንድና ቅርንጫፍ ምሳሌ ተጠቅሞ በተናገረው በዚህ ንግግር ላይ መሰረቱን ያደረገ ስብከት ነበር።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ስብከታቸውን ሲቀጥሉ እንደ ተናገሩት “የክርስቲያን ሕይወት ‘በእኔ ኑሩ’ በሚለው በጌታ ቃል ላይ መሰረቱን ያደረገ ነው” ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን ኢየሱስ የወይን ግንድ እና ቅርንጫፍ ምሳሌን ተጠቅሞ ከእርሱ ጋር መኖር እንደ ሚገባን ያስተምረናል ብለዋል።  እናም ይህ “በእኔ ኑሩ” የሚለው ቃል  በጌታ እቅፍ ውስጥ ገብቶ ማንቀላፋት ማለት አይደለም፣ ምናልባት ይህ ጥሩ እንቅልፍ ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን በምትኩ ይህ “በእኔ ኑሩ” የሚለው ቃል “ንቁ” የሆነ ቆይታን የሚያመለክት ቆይታ ሲሆን እርሱ በእኔ፣ በተቃራኒው ደግሞ እኔ በእርሱ ሁስጥ ሁኜ መኖር ማለት ነው ያሉት ቅዱስነታቸው ይህ የሚሆንበት ምክንያት ደግሞ “በእኔ ኑሩ፤ እኔም በእናንተ እኖራለሁ” ብሎ ኢየሱስ በመናገሩ የተነሳ  እርሱ በእኛ ውስጥ ብቻ ሳይሆን እኛም በእርሱ ውስጥ እንድንኖር ይጋብዘናል ብለዋል።

ይህ “በእኔ ኑሩ፤ እኔም በእናንተ እኖራለሁ” የሚለው ሐረግ  “ምስጢር” ነው፣ “የሕይወት ምስጢር ፣ በጣም ውብ የሆነ ምስጢር” ነው በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “እውነት ነው ፣ ከወይኑ ግንድ  ውጭ ያሉት ቅርንጫፎች ምንም ነገር ማድረግ አይችሉም፣ ምክንያቱም እጽዋት ውስት ያለ ፈሳሽ ወደ ቅርንጫፉ መደረስ ስለማይችል ነው፣ እጽዋት ውስት ያለ ፈሳሽ ወደ ቅርንጫፍ የማይደረስ ከሆነ ደግሞ ቅርንጫፉ ማደግ እና ፍሬ ማፍራት በፍጹም አይችልም ብለዋል። የወይኑ ዛፍ ግንድ  እንዲሁ ቅርንጫፎችን ይፈልጋል፣ ምክንያቱም ፍሬዎቹ ከዛፉ ጋር ተያይዘው እንዲቆዩ የሚያደርጉት ቅርንጫፎቹ ናቸው፣ ፍሬ ለማፍረት አንዱ ሌላውን ይፈልጋል፣ ቅርንጫፍ ብቻውን ጥቅም የለውም፣ ግንዱም ቢሆን ብቻውን ምንም ጥቅም የለውም፣ አንዱ ለአንዱ ያስፈልገዋል” ብለዋል።

“እናም የክርስቲያን ሕይወት ይህ ነው ፣ እውነት ነው ፣ የክርስትና ሕይወት ትዕዛዞቶቹን መፈጸም ነው ፣ ይህ መከናወን አለበት። የክርስትና ሕይወት በብጽዕና መንገድ ላይ መሄድ ይኖርበታል-ይህ መደረግ አለበት ፡፡ ጌታ በቅዱስ ወንጌል እንዳስተማረን የክርስትና ሕይወት የምሕረት ሥራን ማከናወን ይኖርበታል። እናም ይህ መደረግ አለበት። ነገር ግን ከእዚህ በበለጠ  መልኩ “በእኔ ኑሩ፤ እኔም በእናንተ እኖራለሁ” የሚሉት ቃላት መተግበር ይኖርባቸዋል። ቅርንጫፍ ያለ ግንድ ምንም ማደረግ እንደ ማይችል ሁሉ እኛ ያለ ኢየሱስ ምንም ማድረግ አንችልም። ጌታም እኛን ይፈልጋል፣ ከእኛ ጋር መቆየት ይፈልጋል። “በእኔ ኑሩ፤ እኔም በእናንተ እኖራለሁ” ብሏልና።

“የወይን ግንድ ፍሬያማ ለመሆን ቅርንጫፍ ያስፈልገዋል፣ ቅርንጫፍ ደግሞ በሕይወት ለመቆየት ግንድ እንደ ሚያስፈልገው ሁሉ እኛ ለጌታ፣ ጌታ ደግሞ ለእኛ ያስፈልገናል” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “ኢየሱስ እኛን ለምን ይፈልጋል?  በማለት ጥያቄ ያነሱ ሲሆን በቅዱስ ወንጌል ውስጥ እንደ ተጠቀሰው “ሰዎች መልካም ሥራችሁን አይተው አብን ያከብሩ ዘንድ” ብሎ እንደ ተናገረው ኢየሱስ እኛ ስለእርሱ በዓለም ውስጥ እንድንመሰክር ይፈልጋል ብለዋል። ኢየሱስ እኛን የሚፈልገን ስለእርሱ ምስክርነት እንድንሰጥ፣ ለስሙ ለመመሥከር ነው፣ ምክንያቱም እምነት በቅዱስ ወንጌል ምስክርነት ይገለጻልና ነው ብለዋል።

ቤተክርስቲያኗ እንድታድግ ኢየሱስ “ምስክርነቷን ይፈልጋል” እናም “በእኔ ኑሩ፤ እኔም በእናንተ እኖራለሁ”  የሚለው ምስጢር ትርጉሙ ይህ ነው፣ ኢየሱስ፣ አብ እና መንፈስ ቅዱስ በእኛ ውስጥ ይኖራሉ እኛም በኢየሱስ ውስጥ እንኖራለን ብለዋል።

በዚህ መልኩ ማሰባችን እና ማሰላሰላችን መልካም ነው፣ በኢየሱስ ውስጥ መኖር እና ኢየሱስ በእኛ ውስጥ መኖሩ አስፈላጊ ነው። ብርታት፣ ጥንካሬ፣ ትክክለኛ ፣ ነፃ ፣ ፍሬያማ ሆነን እንድንኖር በኢየሱስ ውስጥ መኖር ይኖርብናል፣ ቤተክርስቲያኗ የምታድግበትን ምስክርነት በጥንካሬ ማከናወን እንችል ዘንድ ጥንካሬ እንዲሰጠን፣ ፍሬያማ እንዲያደርገን እርሱ በውስጣችን ሊኖር ይገባል ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው የዕለቱን ስብከት አጠናቀዋል።

ይህን ዝግጅት ለማዳመጥ ከእዚህ ቀጥሎ ያለውን "ተጫወት" የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
13 May 2020, 09:58
ሁሉንም ያንብቡ >