የመንበረ ታቦት አገልጋዮች፣ በሮም ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ተገናኙ
የዚህ ዜና አጠናቃሪ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ከ70 ሺህ በላይ የመንበረ ታቦት አገልጋዮች፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ለማግኘት በሮም እንደሚገኙ ተገለጸ።
ከዓለም ዙሪያ የተወጣጡ ከ70 ሺህ በላይ የመንበረ ታቦት አገልጋዮች፣ ዛሬ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በመሰብሰብ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር እንደሚገናኙ ታውቋል። የመንበረ ታቦት አገልጋዮቹ ይህን መንፈሳዊ ጉዞ ማድረግ ከጀመሩ፣ የዘንድሮ 12ኛ ዙር መሆኑ ታውቋል። የሮም ከተማም ባሁኑ ሰዓት በእነዚህ ልጆች በመሞላቷ የደስታ ስሜት እንደሚታይባት ተስተውሏል።
ከ70 ሺህ በላይ፣ ዕድሜያቸው ከ13 እስከ 23 ዓመት የሚሆናቸው የመንበረ ታቦት አገልጋዮች፣ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ለመገናኘት ወደ ሮም ለሚያደርጉት መንፈሳዊ ጉዞ የመረጡት መሪ ጥቅስ “ሰላምን እሻ ተከተላትም።” የሚለው የዳዊት መዝሙር፣ በምዕ. 34 ቁጥር 15 ላይ የጠቀሰ እንደሆነ ታውቋል።
በዚህ መንፈሳዊ ጉዞ የሚሳተፉ ልጆች ከ18 አገሮች የተወጣጡ እንደሆነ ሲገልጽ፣ በቁጥር በልጦ የተገኙትን ተሳታፊዎች በመላክ ጀርመን የመጀመሪያ ስፍራን ስትይዝ፣ ብዛታቸውም 50 ሺህ መሆኑ ታውቋል። እነዚህን ልጆች ወደ ሮም የመሩት፣ በጀርመን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ፣ የወጣቶች ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ሊቀመንበር የሆኑት ብጹዕ አቡነ ስተፋን ኦስተር መሆናቸው ታውቋል። ከጀርመን ቀጥሎ በልጄም፣ ፈረንሳይ፣ ታላቋ ብሪታኒያ፣ ክሮዋሺያ፣ ሉሴምበርግ፣ ኦስትሪያ፣ ፖርቹጋል፣ ሮማኒያ፣ ሩሲያ፣ ስዊዘርላንድ፣ ሰርቢያ፣ ስሎቫኪያ፣ ቼክ ሪፓብሊክ፣ ዩክሬን፣ ሃንጋሪ እና ሰሜን አሜሪካ ተካፋይ ሲሆኑ አንቲጓ እና ባርቡዳ ሁለት ተወካዮቻቸውን መላካቸው ታውቋል።
ዓለም አቀፍ የመንበረ ታቦት አገልጋዮች ሕብረት ፕሬዚዳንት የሆኑት ብጹዕ አቡነ ላዲስላቭ ነመት፣ በጋዜጣዊ መግለጫቸው እንደገለጹት፣ ሕዝባዊነትን እና የብሔራዊነት መንፈስ በመላበስ፣ ሁሉን አሰባስቦ አንድ ላይ ለማድረግ በመንቀሳቀስ ላይ ያለ ዓለማችን የሚያስተጋባውን የሰላም ጥሪ በመቀበል እኛም ወጣቶቻችንን በማሰባሰብ፣ ምንም ዓይነት ድንበር ሳያግደን የበኩላችንን ድርሻ ለማበርከት ተነስተናል ብለዋል።
እስከ ዓርብ ሐምሌ 27 ቀን 2010 ዓ. ም. በሚቆየው በዚህ ዓለም ዓቀፍ መንፈሳዊ ስብሰባ ወቅት ወጣቶችን የሚያሳትፉ የተለያዩ ዝግጅቶች መኖራቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ከተለያዩ አገሮች የመጡ ወጣቶች እርስ በርስ የሚገኛኙበት መድረክ፣ ከየአገሮቻቸው ጳጳስ ጋር ቁጭ ብለው የሚወያዩበት፣ መስዋዕተ ቅዳሴን እና የጉባኤ ጸሎትን በጋራ የሚካፈሉበት፣ ኑዛዜ የሚገቡበት እና ምክሮችን የሚቀበሉበት፣ በሮም ውስጥ የተለያዩ ታሪካዊ ቦታዎችን መጎብኘት እና ከሬስቶራንት ውጭ የተዘጋጀ የምሳ ፕሮግራም እና እነዚህ የተለያዩ ዕቅዶች ተግባራዊ የሚሆኑባቸው እና እንግዶች የሚስተናገዱባቸ 300 ቦታዎች በሮም ከተማ ውስጥ መዘጋጀታቸው ታውቋል። ከሁሉም በላይ በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር የሚደረገው ግንኙነት ትልቅ ስፍራ የተሰጠው ሲሆን፣ የዘንድሮ በዓል በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የኢየሱሳዊያን ማህበር መሥራች የሆነው የሎዮላው ቅዱስ ኢግናሲዮስ በሚታሰብበት ዕለት በመሆኑ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም የዚህ ማህበር አባል በመሆናቸው፣ ዘንድሮ የተደረገውን የወጣቶች መንፈሳዊ ጉዞ የበለጠ አስደሳች ያደርገዋል ተብሏል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ወጣቶችን የሚመለከቱ ሁለት ዓበይት ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች እነርሱም በሮም በወጣቶች ጉዳይ ላይ በስፋት የሚመክር የመላው ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ እና መካከለኛዋ አሜሪካ አገር በሆነችው በፓናማ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን በዓል ከፊታችን እንደሆነ ታውቋል። ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ በሚደረገው ግንኙነት ወቅት ከወጣቶች የሚቀርቡ ምስክርነት፣ ወጣቶችን የሚያሳትፉ መዝሙሮች፣ ከዩክሬን፣ ከሰሜን አሜርካ እና ከጀርመን በመጡ ወጣቶች በኩል ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሚቀርቡ ስጦታዎች ከእነዚህም መካከል ዕለቱን የሚያስታውሱ ምስሎች ወይም ምልክቶች፣ በነጭ ቀለም የተሳለ እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን በግል የሚመለከት የወጣቶቹ ዓለም አቀፍ ማህበር አርማ ያለበት ስጦታም እንደሚቀርብ ታውቋል።
በጀርመን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ፣ የወጣቶች ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚዳንት የሆኑት ብጹዕ አቡነ ስተፋን ኦስተር፣ ዘንድሮም መንፈሳዊ ጉዞ ወጣቶች እምነታቸው እንዲገነዘቡና በዚህም ማንነታቸውን እንዲያውቁ እና የአገልግሎታቸውን ዓለም አቀፋዊነት እንዲረዱ ያደርጋል ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ በእነዚህ ቀናት ውስጥ በሚከናወኑ ዝግጅቶች፣ በመስዋዕተ ቅዳሴና በጸሎት ዝግጅቶች መሳተፍ፣ ከዓለም ዙሪያ ከመጡት እና በተመሳሳይ አገልግሎት ከተሰማሩት የቤተ ክርስቲያን ልጆች ጋር መገናኘት፣ እምነታቸውን በተግባር እንዲኖሩ እና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንደሚያሳድግላቸው ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። ብጹዕ አቡነ ስተፋን ኦስተር በማከልም ይህ ዓለም አቀፍ የወጣቶች መንፈሳዊ ጉዞ፣ ወጣቶች በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት ከማሳደግ በተጨማሪ ከመላው የዓለም ወጣቶች ጋር መልካም ግንኙነትን ለመገንባት ይጠቅማል ብለዋል። ወጣቶቹ ከዚህ ዓለም አቀፍ መንፈሳዊ ጉዞ የሚቀስሙትን መልካም ልምድ ወደ አገሮቻቸው በመውሰድ፣ ሰላምንና ደስታን በመጨመር ከሚኖሩበት ሕብረተ ሰብ ጋር ተስማምተው የሚኖሩበትን መንገድ ይፈጥራል ብለዋል።
የዚህ መንፈሳዊ ጉዞ ተካፋይ ለሚሆኑ ወጣቶች፣ “ጎ ሮም” ወይም “ወደ ሮም ሂዱ” የሚል የኢንተር ኔት ፕሮግራም የተመቻቸ ስለ ሆነ ይህን ኣፕሊኬሽን በመጠቀም በሮም በሚያሳልፏቸው ሦስት ቀናት ወስጥ የሚከናወኑትን ዝግጅቶች እንዲከታተሉ፣ ሃሳቦቻቸውን እንዲጋሩ፣ በሮም ሊካሄድ በታቀደው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖድ ላይ ያላቸውን አስተያየትና ጥያቄ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንዲያቀርቡ የሚያስችል መንገድ መዘጋጀቱ ታውቋል።