ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተባበሩ አረብ ኤምረቶችን እንዲጎበኙ መጋበዛቸው ተነገረ።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተባበሩት አረብ ኤምረትን እንዲጎበኙ በማለት የተባበሩት አረብ ኤምረት ሼክ መሐመድ ቢን አል ናያን ግብዣ ማቅረባቸው ታውቋል። ከሼክ መሐመድ ቢን አል ናያን ግብዣ በተጨማሪ በተባበሩት አረብ ኤምረቶች ከምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንም ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ግብዣ መድረሳቸው ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የአረብ ኤምረቶችን የሚጎበኙት ከጥር 26 እስከ ጥር 28 ቀን 2011 ዓ. ም. እንደሆነ ታውቋል። ቅዱስነታቸው በአረብ ኤምረቶች በሚያደርጉት ቆይታ “የሰው ልጆች ወንድማማችነት” በሚል ርዕስ፣ በአቡ ዳቢ ከተማ የሚካሄደውን የዓለም ሐይማኖቶች መሪዎች ስብሰባ ላይም እንደሚገኙ የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ተጠሪ የሆኑት አቶ ግረግ ቡርኬ ገልጸዋል።
የሰላምህ መሣሪያ አድረገኝ፣
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሐዋርያዊ እረኝነት አገልግሎት ከጀመጀመራቸው አስቀድመው፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ እንደጻፈው በምዕ 5 ቁጥር 9 ላይ “ሰላምን የሚያወርዱ ብጹዓን ናቸው፣ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ይጠራሉና” የሚለውን በተግባር በገለጸው በቅዱስ ፍራንችስኮስ ስም ለመጠራት መፈለጋቸው ይታወቃል። ከእግዚአብሔር የሚገኝ እውነተኛ ሰላም በሰው ልጆች መካከል የሚታየውን ጥላቻ እንደሚያስወግድ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ባወጀው መልካም ዜና አማካይነት መላው ዓለም በአንድ እግዚአብሔር ስም እርቅንና ሰላምን እንዲያገኝ መደረጉ ይታመናል። በተባበሩት አረብ ኤምረቶች፣ አቡ ዳቢ ከተማ የሚካሄደው የዓለም ሐይማኖቶች መሪዎች ጉባኤ የመወያያ ርዕስም፣ ቅዱስ ፍራንችስኮስ ለሰላም ካቀረበው ጸሎት የመነጨ በመሆኑ፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ተባበሩት አረብ ኤምረቶች የሚያደርጉት ጉብኝት ከእግዚአብሔር የተሰጠንን ሰላም ለማጠናከር እገዛ እንዳለው፣ በዚህ ታሪካዊ ጉባኤ አማካይነት በጎ ፈቃድ ባላቸው ሰዎች ልብ ውስጥ የእግዚአብሔር ሰላም እንደሚመጣ ተስፋ ተደርጎበታል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጉብኝት አስመልክቶ የተዘጋጀ አርማ፣
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ተባበሩት አረብ ኤምረቶች የሚያደርጉትን ጉብኝት ምክንያት በማድረግ ልዩ አርማ መዘጋጀቱም ታውቋል። በአርማው የተገለጸው ምስል እንደሚያመለከተው፣ የወይራን ቅጠል ያነገበች፣ በነጭና በቢጫ ቀለማት የተሳለች እርግብ ስትሆን፣ እነዚህ ሁለቱ ቀለማትም የቫቲካንን ባንዲራ የሚያመለክቱ መሆናቸው ታውቋል። የተባበሩት አረብ ኤምረቶች ባንዲራ ቀለማትም እርግቧ ከተሳለችባቸው ቀለማት ውስጥ እንደሚገኙ ሲታወቅ፣ የአርማው ዋና መልዕክት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ተባበሩት አረብ ኤምረቶች የሚያደርጉት ጉብኝት የሰላም መልእክተኛ መሆናቸውን የሚያመለክት እንደሆነ ታውቋል።