የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አጭር ታሪክ።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ልዑል ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ ኣል ናያን በቀረበላቸው ግብዣ መሠረት ከእሑድ ጥር 26 – 28፣ 2011 ዓ. ም. ድረስ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ለማድረግ ወደዚያች አገር እንደሚሄዱ ታውቋል። ከሼክ መሐመድ ቢን አል ናያን ግብዣ በተጨማሪ ቅዱስነታቸ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንም ግብዣ ማድረጋቸው ታውቋል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ የፋርስ ባሕረ ሰላጤ ደቡባዊውን ጠረፍ ይዞ፣ በሰሜን ምዕራብ የኦማን ባሕረ ሰላጤ አከባቢዎችን የሚያጠቃልልና በፌደራል ግዛት አወቃቀር የተመሠረት መንግሥት ያለው፣ በሰሜን ከካታር፣ በምዕራብ ከሳውድ አረቢያ፣ በደቡብ ከኦማን ጋር የሚዋሰን አገር ነው። የሕዝቡ ብዛት 9,229,000 እንደሆነ ይነገራል። የአገሩ ብሔራዊ ቋንቋ አረብኛ ሲሆን እንግሊዝኛም በስፋት ይወራል። ከሕዝቡ መካከል 12 ከመቶ የኤምሬት አገሮች ተወላጆች፣ 59 ከመቶ የደቡብ እሲያ ተወላጆች፣ 10 ከመቶ ግብጾች፣ 14 ከመቶ የሌሎች አግሮች ተወላጆች እንደሚኖሩበት ይነገራል። በአገሩ የእምነት ተከታዮችን በተመለከተ 76 ከመቶ የእስልምና እምነት ተከታዮች፣ 10 ከመቶ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች እና 14 ከመቶ የሌሎች እምነቶች ተከታዮች የሚገኙበት አገር ነው። ዋና ከተማ አቡ ዳቢ ሲሆን የነዋሪዎቿ ብዛት 1 ሚሊዮን 452 ሺህ 57 እንደሆኑ ይነገራል። በአረብኛ ቋንቋ አቡ ዳቢ ማለት የሜዳ ፍየል የሚገኝበት መሬት ማለት ነው። አቡ ዳቢ በአረብ አገሮች መካከል ከዱባይ ቀጥሎ ሁለተኛ ዘመናዊ ከተማ እንደሆነ ይነገራል። የሚገኘውም በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ከሚገኙት ደሴቶች መካአክል በአንዱ ነው። የአቡ ዳቢ ደሴት ከዋናው መሬት ጋር የተገናኘው በድልድይ አማካይነት እንደሆነ ይታወቃል። የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ በብዛት በማምረት ከሚታወቁ ቀዳሚ አገሮች መካከል የሚመደብ ሲሆን ከዓለም የነዳጅ ምርት መጠን 9 ከመቶ እና ከተፈጥሮ ጋዝ ምርት መጠንም 5 ከመቶ ለዓለም ገበያ እንደሚያቀር ታውቋል። በዚህ የተነሳ የአገሩ ነዋሪ ሕዝብ የኑሮ ደረጃ የተደላደለ እና የዓመት ገቢውም ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል። አቡ ዳቢ በ1950 ዓ. ም. የምድር ውስጥ የተፈጥሮ ሐብት ክምጭት ከማግኝቱ አስቀድሞ በ18ኛው ክፍለ ዘመን የተቆረቆረ፣ ዓሳን በማጥመድ እና የቴምር ፍሬን ለገበያ በማቅረብ የሚተዳደሩ የባኑ ያስ ጎሳዎች የሚኖሩበት አነስተኛ ከተማ እንደነበር የከተማዋ ታሪክ ያስረዳል። የአቡ ዳቢ ከተማ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አሁን ወደ ደረሱበት የኤኮኖሚ እድገት ትልቅ አስተዋጽዖን ያበረከቱት እና አገሪቱን እስከ 1996 ዓ. ም. ሲመሩ ቆይተው ያረፉት ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ ኣል ናያን መሆናቸው ይታወቃል። ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ ኣል ናያን አገሪቱ በተፈጥሮ ሐብት ምርት እንድትበለጽግ፣ ትምህርት እንዲስፋፋ፣ ውጤታማ የሆኑ ማሕበርዊ ተቋማትን በማደራጀት፣ በሐይማኖቶች መካከል መቻቻል እንዲኖር ትልቅ አስተዋጽዖን እንዳበረከቱ ይነገርላቸዋል። ከእርሳቸው ቀጥለው ስልጣንን የተረከቡት ልኡል ሼክ ካሊፋ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናያን፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ቀዳሚ የኤኮኖሚ ዋልታ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ከሚሆን ትራንስፖርት፣ ጤና፣ ባሕል እና ቱሪዝም በማለት በእነዚህ የአገልግሎት መስጫ ዘርፎች ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ እንዲውል አድርገዋል። በአገሪቱ ከሚጠቀሱ ታላላቅ ፕሮጀክቶች መካከል በስነ ሕንጻ አርት ትልቅ ዝናን እና ዓለም አቀፍ እውቅናን ያገኙ፣ በዣን ኑቨል የተነደፉ ለምሳሌ የሉቭር ሕንጻ፣ በኖርማን ፎስተር የተነደፈው እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዋና መስራች እና አባት እንደሆኑ ለሚታወቁ ለሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ ኣል ናያን መታሰቢያ የሆነው የዛይድ ብሔራዊ ሙዚየም እና በፍራንክ ጄሪ የተነደፈው የጉጀኔም ዘመናዊ ሥነ ጥበብ ሙዜም ይገኙባቸዋል። ባሁኑ ጊዜ ከአቡ ዳቢ 15 ኪሎ ሜትር ወጣ ብሎ በመቆርቆር ላይ የሚገኝ የማስዳር ከተማ የሚጠቀስ ሲሆን ይህ ከተማ ሙሉ በሙሉ ከጸሐይ ብቻ በሚገኝ ታዳሽ ሃይል የሚታገዝ የመጀመሪያ ከተማ እንደሚሆን ይነገራል። በአቡ ዳቢ ከተማ ውስጥ ከታነጹት የአምልኮ ስፍራዎች መካከል አንዱ የሆነው የሼክ ዛይድ መስጊድ የሚጠቀስ ሲሆን ሌሎችም በ18ኛው ክፍለ ዘመን የታነጹ እና እድሳት እየተደረገላቸው የሚገኙ ጥንታዊ ሕንጻዎች መኖራቸው ታውቋል። አቡ ዳቢ የቱሪስት ከተማ እየሆነ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በከተማው ውስጥ ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቁ ረጃጅም ሆቴሎች፣ ንጹሕ የባሕር ዳር መዝናኛ ስፍራዎች፣ ታዋቂው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ቤተ መንግሥት የሚገኝበት ከተማ ነው።