ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “መንግሥትህ ትምጣ" ማለት አንተ "በእኛ መካከል ሁን! ማለት ነው።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው የጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሻ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የሀገር ጎብኝዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በዚህ መሰረት በኅዳር 26/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው የጳውሎስ 6ኛ የስብሰባ አዳራሽ ያደርጉት የጠቅላላ የተምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ዙሪያ ላይ መሰረቱን ያደርገ የክፍል አንድ አስተምህሮ እንደ ነበረ መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን “ኢየሱስ ጸሎት መጸለይ እንዲይስተምረን ልንጠይቀው ይገባል” ማለታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በታኅሳስ 03/2011 ዓ.ም አሁንም “አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ዙርያ ላይ ባደርጉት የክፍል ሁለት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “አባታችን ሆይ” የሚለውን ጸሎት “በእግዚኣብሔር በመተማመን ልንጸልየው የሚገባን ጸሎት ነው” ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን በታኅሳስ 24/2011 ዓ.ም አሁንም “አባታችን ሆይ!” በሚለው ጸሎት ዙርያ ላይ ባደርጉት የክፍል ሦስት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “ሳትለምነው  በፊት ምን እንደ ሚያስፈልግህ  በሚያውቀው አባትህ ፊት ሆነህ ጸልይ” (ማቴ. 6፡6) የእኛ አምላክ የሆነው እግዚኣብሔር እርሱ ከእኛ ምንም ነገር አይፈልግም፣ ነገር ግን እርሱ ከእኛ የሚፈልገው አንድ ነገር ቢኖር የእርሱ በጣም ተወዳጅ ልጆቹ የሆንን እኛ፣ በጸሎት ሁልጊዜ ከእርሱ ጋር ለመገናኘት የሚያስችለንን የመገናኛ መስመር ሁልጊዜ ክፍት እንድናደርግ ብቻ ነው የሚጠይቀን” ማለታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

በጥር 1/2011 ዓ.ም አሁንም “አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ዙርያ ባደርጉት የክፍል አራት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት “ማነኛውም ዓይነት ጸሎት ወደ እግዚ/ር ዘንድ ሳይደርስ እንዲሁ በከንቱ አይቀርም!  እርሱ እግዚኣብሔር አባት በመሆኑ የተነሳ በመከራ ውስጥ ሆነው እርሱን የሚለምኑትን ልጆቹን በፍጹም አይረሳም” ማለታቸውን የሚታወስ ሲሆን በጥር 08/2011 ዓ.ም “አባታችን ሆይ!” በሚለው ጸሎት ዙሪያ ባደረጉት የክፍል አምስት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ደግሞ አባ" ማለት እግዚአብሔርን "አባት" ብሎ ከመጥራት የበለጠ ልብ የሚነካ ስሜት እንደ ሌለ ያሳየናል”  ማለታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

ቅዱስነታቸው ከዚያም በመቀጠል በየካቲት 06/2011 ዓ.ም አሁንም በዚሁ “አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ዙርያ ላይ ባደርጉት የክፍል ስድስት የጠቅላላ አስተምህሮ እንደ ገለጹት “እውነተኛ ጸሎት ተጨባጭ የሆነና በርኅራኄ መንፈስ የተሞላ ጸሎት ሊሆን የገባዋል!” ማለታቸውንም መዘገባችን ይታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በየካቲት 13/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ አሁንም “አባታችን ሆይ!” በሚለው ጸሎት ዙሪያ ባደርጉት የክፍል ሰባት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “በሰማይ የምትኖር አባታችን ሆይ!” በሚለው ጭብጥ ዙሪያ ላያ ያተኮረ እንደ ነበረ መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን “ማንም ሰው ሊወደን በማይችል መልኩ እግ/ሔር አባታችን ይወደናል”  ማለታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

በየካቲት 20/2011 ዓ.ም አሁንም “አባታችን ሆይ!” በሚለው ጸሎት ዙሪያ ላይ ቅዱስነታቸው ያደርጉት የክፍል ስምንት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “ስምህ ይቀደስ” በሚለው የመጀመሪያው የመማጸኛ ጸሎት ሐረግ ዙሪያ ላይ ያተኮረ እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን “የኢየሱስ ስም ቅዱስ እና ኃያል በመሆኑ የተነሳ ክፉ መንፈስ ተሸንፏል!” ማለታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

በየካቲት 27/2011 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ያደረጉት የክፍል ዘጠኝ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አሁንም “አባታችን ሆይ!  በሚለው ጸሎት ውስጥ ባለው  “መንግሥትህ ትምጣ” በሚለው ሁለተኛው የመማጸኛ ጸሎት ሐረግ ላይ መሰረቱን ያደርገ እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን “የጌታ የሆነቺው ቤተ ክርስቲያን “ጌታ ሆይ በቶሎ ና!”፣ ጌታ ሆይ መንግሥትህ ይምጣ” ብላ መጸለይ ይገባታል”፣ “መንግሥትህ ትምጣ" ማለት አንተ "በእኛ መካከል ሁን! ማለት ነው” ማለታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ- ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራነስኮስ ዛሬ የካቲት 27/2011 ዓ.ም “አባታችን ሆይ!” በሚለው ጸሎት ዙሪያ ላይ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አሰትምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተናዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

 "አባታችን ሆይ!" የሚለውን ጸሎት በምንጸልይበት ወቅት በሁለተኛ ደረጃ የምናገኘው የመማጸኛ ጸሎት “መንግሥትህ ትምጣ” (ማቴ 6፡10) የሚለውን ነው። አማኙ በቅድሚያ “ስምህ ይቀደስ” የሚለውን የመማጸኛ ጸሎት ከጸለየ በኋላ የእርሱ መንግሥት መምጣት እንዲፋጠን እንደሚፈልግ ያለውን ፍላጎት ይገልጻል። ይህ ምኞት የመነጨው ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልብ ውስጥ ሲሆን እርሱም የተሰጠውን ተልዕኮ በይፋ በገሊላ ክፍለ አገር በመጀመረበት ወቅት “ዘመኑ ተፈጸመ ፣የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ፣ በወንጌልም እመኑ” (ማር. 1፡15) በማለት ዩሐንስ ስለእርሱ ከተናገረው ቃል ጋር ይመሳሰላል። እነዚህ ቃላት የማሰፈራሪያ ቃላት አይደሉም፣ በተቃራኒው ግን አስደሳች የሆኑ የደስታ መልዕክቶች ናቸው። ኢየሱስ እግዚአብሔር የሚሰጠውን ፍርድ በተመለከተ ፍርሐትን በመዝራት ወይም ለተፈጸመው ክፉ ተግባር የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማቸው በማድረግ ፍርሃትን በመዝራት ሰዎች መንፈሳዊ ለውጥ እንዲያመጡ አላስገደደም ወይም አላደርገም። ኢየሱስ ሰዎች በግዳጅ መንፈሳዊ የሆነ ለውጥ እንዲያመጡ አያስገድድም፣ በቀላሉ እርሱ ሰዎች መንፈሳዊ ለውጥ እንዲያመጡ ይመክራቸዋል። በተቃራኒው እርሱ የደህንነት ምንጭ የሆነውን መልካም የሆነ ዜና ያመጣልናል፣ እናም ከእዚያ መልካም ዜና በመነሳት መንፈሳዊ ለውጥ እንድናመጣ ይጋብዘናል። እያንዳንዳችን በቅዱስ ወንጌል እንድናምን ተጠርተናል፣ የእግዚኣብሔር ሕልውና ለልጆቹ ቅርብ ይሆናል። ቅዱስ ወንጌል ማለት እግዚኣብሔር ለልጆቹ ቅርብ ሆነ ማለት ነው። እናም ኢየሱስ ይህንን አስደናቂ ነገር፣ ይህንን ጸጋ አውጇል፣ እግዚአብሔር አብ ይወደናል፣ ቅርባችን ነው፣ እናም በቅድስና መንገድ እንድንሄድ ያስተምረናል።

የዚህ መንግሥት የመምጣት ምልክቶች በርካታ እና ሁሉም አዎንታዊ የሆነ ገጽታ አላቸው። ኢየሱስ በማኅበረሰቡ የተገለሉ ሰዎችን እና የአካልና የመንፈስ በሽታ ያላቸውን ሰዎች በመርዳት ነበር ምድራዊ አገልግሎቱን የጀመረው፣ ለምሳሌም ለምጻሞችን፣ በኃጢያታቸው ምክንያት በሁሉም ሰዎች የተናቁትን ወይም የተወገዙትን፣ ምንም እንኳን ከእነርሱ በላይ ከፍተኛ የሆነ ኃጢያት የሰሩ ሰዎች ቢኖሩም ግብዞች ራሳቸውን በከንቱ በማመጻደቃቸው የተነሳ ከእነርሱ የባሰ ኃጢአት ያለስሩ ሰዎችን እንደ ጥፋተኛ ፈርጀው ያገለሉዋቸውን ሰዎች ለማዳን መጣ። እነዚህን የመሳሰሉ ሰዎችን ኢየሱስ "እናንተ ግብዞች!” በማለት ይጠራቸዋል። ኢየሱስ ራሱ “ዕውሮች ያያሉ፣ አንካሶችም ይሄዳሉ፥ ለምጻሞችም ይነጻሉ፣ ደንቆሮችም ይሰማሉ፥ ሙታንም ይነሣሉ” (ማቴ. 11፡5) ብሎ በመናገር እነዚህ ምልክቶች የእግዚአብሔርን መንግሥት ምልክቶች መሆናቸውን ያመለክታል።

ለዚህም ነው ታዲያ አንድ ክርስቲያን “አባታችን ሆይ” የሚለውን ጸሎት በሚጸልይበት ወቅት “መንግሥትህ ትምጣ!" በማለት አጥብቆ የሚማጸነው በዚሁ ምክንያት ነው። ኢየሱስ ወደ ዓለም መጥቱዋል፣ ነገር ግን ዓለም አሁንም በበርካታ ኃጢያቶች ውስጥ ይገኛል፣ በጣም ብዙ ሰዎች በስቃይ ውስጥ የገኛሉ፣ እርስ በእርሳቸው ይቅር የማይባባሉ እና የማይዋደዱ ሰዎች አሁንም አሉ፣ ዓለም አሁንም ቢሆን በጦርነቶች እና በብዙ ዓይነት የብዝበዛ ዘዴዎች ምክንያት እየተሰቃየች ትገኛለች፣ ለምሳሌ በሕጻናት ላይ የሚፈጸሙትን በደሎች ማንሳት ይቻላል። እነዚህ ሁሉ እውነታዎች የክርስቶስ ድል አድራጊነት ገና ሙሉ በሙሉ አለመረጋገጡን ያሳያሉ፣ አሁንም ቢሆን በጣም የብዙ ወንዶች እና ሴቶች ልብ አሁንም እንደ ተዘጋ ያሳየናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ "አባታችን ሆይ" በሚለው ጸሎት ውስጥ የሚገኘውን “መንግሥትህ ትምጣ” የሚለውን ሁለተኛው የመማጸኛ ጸሎት ክርስቲያኖች ሁልጊዜ የሚደግሙት በዚህ ምክንያት ነው። ይህም ማለት ደግሞ "አባት ሆይ አንተ ታስፈልገናለህ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ አንተን እንሻለን፡ ከእኛ ጋር በየተኛውም ቦታ እና ለዘላለም እንድትሆኑ እንፈልጋለን!” ማለት ነው። "መንግሥትህ ትምጣ" ማለት አንተ "በእኛ መካከል ሁን!" ማለት።

አንዳንድ ጊዜ እራሳችንን እንዲህ ብለን እንጠይቃለን: ይህ መንግሥት ቀስ ብሎ እየተከሰተ ያለው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ምሳሌዎችን በመጠቀም እርሱ ስለተቀናጀው ድል መናገር ይወዳል። ለምሳሌ ያህል የእግዚኣብሔር  መንግሥት በአንድ ማሳ ላይ እንደ ተዘራ እና አብረው እንዲያድጉ የተደርጉትን በጥሩ ስንዴና በእንክርዳድ ይመሰላል በማለት ይናገራል፣ ከሁሉም የከፋው ስህተታችን ደግሞ እኛ እንክርዳድ የሚመስሉ ነገሮችን በሙሉ ከዓለም ላይ ለማጥፋት መሞከር ማሰባችን ሊሆን ይችላል። እግዚኣብሔር እንደኛ አይደለም፣ እግዚኣብሔር ታማኝ ነው። መንግሥቱ ን በዓለም ውስጥ የሚመሰርተው በነውጥ አማካይነት አይደለም; እርሱ ምንግሥቱን በዓለም ውስጥ የሚያስፋፋው በየዋህነት መንፈስ ነው።

በርግጥ የእግዚአብሔር መንግሥት ትልቅ የሆነ ኃይል ነው፣ ከሁሉም በላይ ትልቅ ነው፣ ነገር ግን በዓለም መመዘኛዎች አይለካም፣ ለዚህም ነው ከሁሉም በላይ የሆነ ታላቅ ኃይል ያለው የማይመስለው በዚሁ ምክንያት ነው። ይህም ሊጥ እንዲቦካ የሚያደርገውን ትንሽዬ እርሾ ይመስላል፣ በዓይናችን የምናየው ነገር ባይሆንም ነገር ግን ሊጡ እንዲቦካ ግን በደንብ ያደርጋል (ማቴ. 13፡33) ወይም ደግሞ በሰናፊጭ ዘር አምሳያ ይመሰላል፣ የሰናፊጭ ዘር በዓይን እንኳን ለማየት የምታዳግት በጣም ትንሽ የሆነች ዘር ስትሆን ነገር ግን የተፈጥሮ ኃይልን  በማንጸባረቅ  አንድ ጊዜ ካደገች ግን በእርሻው ስፍራ ካሉ ዛፎች ሁሉ በላይ ትሆናለች (ማቴ 13፡31-32)።

በዚህ የእግዚአብሔር መንግሥት ዕጣ ፈንታ እና የኢየሱስን ሕይወት መገመት እንችላለን- እርሱ ደግሞ በሁኑ ጊዜ ባሉ የታሪክ ጸሐፊዎች ዘንድ ብዙ የማይታወቅ ክስተት ነው። “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የስንዴ ቅንጣት በምድር ላይ ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች” (ዮሐንስ 12፡24) በማለት እርሱ ራሱ ስለራሱ ተናግሮ ነበር። የዘሪው ምሳሌ አንደበተ ርቱዕ ነው፣ አንድ ቀን ዘሪው ዘሩን በአፈር ውስጥ ይቀብረዋል (ከቀብር ሥነ-ስረዓት ጋር ይመሳሰላል) ከዚያም በኋላ “እርሱም ሌሊትና ቀን ይተኛል፣ ይነሣልም እንዴት እንደሚሆን ሳያውቅ ዘሩ ይበቅላል ያድግማል” (ማር. 4፡26-27)። የተዘራውን ዘር ከዘሪው ይልቅ ዘሩ እንዲበቅል የሚያደርገው እግዚኣብሔር ነው። እግዚአብሔር ሁል ጊዜ ይቀድመናል፣ እግዚአብሔር ሁልጊዜ ያስነሳናል። ከስቅለተ ዐርብ ሌሊት በኋላ ለእሱ ምስጋና ይግባውና የትንሣኤ ጀንበር ለመላው ዓለም ሙሉ ተስፋ እንዲሰጥ ማድረግ ይቻላል።

“መንግሥትህ ትምጣ!” ይህንን ቃል በኃጢአቶቻችን እና በውድቀቶቻን መካከል መዝራት ይኖርብናል። በሕይወት ጫና ምክንይታ ተስፋ የቆረጡ ሰዎችን እና የሕይወት ጫና በከፍተኛ ሁኔታ ያጎበጣቸው፣ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻ የጎዳቸውን፣ ለምን እንደ ሚኖር እንኳን ሳይገባው ትርጉም የለሽ የሆነ ሕይወት በመኖር ላይ የሚገኙ ሰዎችን እንዲደሰቱ ማደርግ ይኖርብናል። ለፍትህ መስፈን ለሚታገሉ ሰዎች፣ በታሪክ ሂደት ውስጥ መስዋዕት ለሆኑ ሰዎች፣ ሕይወቱን በከንቱ ውጊያ ውስጥ እንዳላሳለፉ ለሚቆጥሩ ሰዎች እና በዚህ ምድር ውስጥ የሚገኙትን ክፉ ነገሮችን ሁልጊዜ ለማሸነፍ ለሚሞክሩ ሰዎች ይህንን ተስፋ እንስጣቸው። ከዚያም "አባታችን ሆይ" የሚለው ጸሎት ምን ማለት እንደ ሆነ በትክክል ይገባናል። በተስፋ ቃላቶቹ ላይ መንፈስ ቅዱስ በሁሉም የቅዱሳን መጽሐፍት ውስጥ በማኅተም አትሞ ያስቀመጠውን እነዚህን የተስፋ ቃሎች “መንግሥትህ በቶሎ ይምጣ” የሚለውን ጸሎት በእየለቱ መድገም ያስፈልጋል፣ እርሱም “ቶሎ እመጣለሁ” ብሎ ይመልስልናል። የጌታ የሆነቺው ቤተ ክርስቲያን “ጌታ ሆይ በቶሎ ና!”፣ ጌታ ሆይ መንግሥትህ ይምጣ” ብላ መጸለይ ይገባታል። ኢየሱስም “በቶሎ እመጣለሁ!” ብሎ ይመልስልናል። ኢየሱስ እርሱ በፈቀደው መልኩ በእየለቱ ይመጣል። በዚህ መተማመን ሊኖረን ይገባል። አባታችን ሆይ የሚለውን ጸሎት በምንጸልይበት ወቅት “ምንግሥትህ ትምጣ”  የሚለውን ቃል ከልባችን መጸለይ ይኖርብናል፣ እርሱም “አዎን መጣሁኝ ቶሎ እመጣለሁኝ” ብሎ የሚመልስልንን ቃል በልባችን ውስጥ ለማዳመጥ እንችላለን።

 

 

06 March 2019, 14:14