“ቤተክርስቲያን የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች መገናኘት ይችሉ ዘንድ ድልድይ መገንባት ይኖርባታል”
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው የጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሻ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የሀገር ጎብኝዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዛሬው እለት ማለትም መጋቢት 25/2011 ዓ.ም ዘወትር ረቡዕ ዕለት በሚያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ፈንታ በቅርቡ ከመጋቢት 21-22/2011 ዓ.ም ድረስ “የእግዚኣብሔር አገልጋዮች አገልጋይ” በሚል መሪ ቃል በሞሮኮ ዋና ከተማ በራባት አድርገውት የነበረውን 28ኛው ሐዋርያዊ ጉብኝት አስመልክተው መልእክት ማስተላለፋቸው የተገለጸ ሲሆን “ቤተ ክርስቲያን የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች መገናኘት ይችሉ ዘንድ አገናኝ የሆነ ድልድይ መገንባት ይኖርባታል” ማለታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዛሬው እለት ማለትም በመጋቢት 25/2011 ዓ.ም በቅርቡ ከመጋቢት 21-22/2011 ዓ.ም ድረስ በሞሮክ አድረገውት የነበረውን 28ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት አስመልክተው ያደረጉትን ንግግር ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!
ባለፈው ቅዳሜ እና እሁድ እለት (መጋቢት 21-22/2011 ዓ.ም) የሞሮኮ ንጉሥ የሆኑት የተከበሩ ሞሃመድ 6ኛ ባቀረቡልኝ ግብዣ መሰረት በሞሮኮ ሐዋርያዊ ጉብኝት አድርጌ ነበር። እርሳቸው እና ለሌሎች የሞሮኮ ባለሥልጣናት ላደረጉልኝ ሞቅ ያለ አቀባበል እና ትብብር ምስጋናዬን ለማቅረብ እወዳለሁ።
በተለይም ደግሞ “የጌታ አገልጋዮች አገልጋይ” በሚል መሪ ቃል ያደረኩት ይህ ሐዋርያዊ ጉዞ ከወንድሞቼ እና ከእህቶቼ የእስልምና እምነት ተከታዮች ጋር አዲስ የውይይት መድረክ በመክፈት ቀጣይ የሆነ ውይይት ማድረግ እንችል ዘንድ የፈቀደውን ጌታን አመስግናለሁ። የእኔ ሐዋርያዊ ጉዞ የሁለት ቅዱሳንን ፈለግ ተከትሎ የተደረገ ጉዞ ነው፡ እነዚህም የአዚዚው ቅዱስ ፍራንቸስኮስ እና ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ ናቸው። ከ800 ዓመታት በፊት የአዚዚው ቅዱስ ፍራንቸስኮስ የሰላም እና የወንድማማችነት መልዕክት ለሱልጣን አል-ማሊክ አል-ካምል አመጣ፡ ከዚያም በመቀጠል ደግሞ በወቅቱ የእስልምና አገራት መሪዎች ከነበሩት ሰዎች መካከል በቀዳሚነት ቫቲካንን ከጎበኙ የአገር መሪዎች መካከል የመጀምሪያው የነበሩት ንጉሥ ሀሰን ሁለተኛ ቫቲካንን ከጎበኙ በኋላ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ዮሐንስ ጳውሎስ እ.አ.አ 1985 ዓ.ም እርሳቸው በሞሮኮ ያደርጉት ጉብኝት ይጠቀሳል።
አሁን እኛ ባለንበት ዘመን ውስጥ ተስፋን ማራመድ ማለት በሰብዓዊ ስልጣኔ መካከል አገናኝ የሆነ ድልድይ መገንባት ማለት ነው። ይህንን ተስፋ ይዤ በዚህች ታላቅ አገር በሆነችው በሞሮኮ መገኘቴ ለእኔ ታላቅ ደስታ እና ክብር ነው። በቅርብ ዓመታት በዚያ ሀገር ውስጥ የተደረጉትን ጠቃሚ ዓለም አቀፍ ጉባዔዎች በማስታወስ ከንጉሥ ሞሐመድ ስድስኛ ጋር ተገናኝተን በተወያየንበት ወቅት ሰብአዊ ክብርን ለማስጠበቅ ይቻል ዘንድ መሰረታዊ የሆኑትን የሐይማኖት ነጻነት፣ ሰላምን ማረጋገጥ፣ ፍትህን ማስፈን፣ ለተፈጥሮ ጥበቃ ማድረግ እና የጋራ መኖሪያ ቤታችን የሆነችውን ምድራችንን መንከባከብ እንደ ሚገባ ተነጋግረናል። ከዚህ አንጻር ሲታይ በተጨማሪም ቅድስቲቷን ከተማ ኢየሩስአሌምን በተመለከተ የሰብአዊ ማኅበረሰቡ ርስት እና የሰላም ስፍራ እንድትሆን፣ በተለይም ለሶስቱ በአንድ አምላክ ለሚያምኑ የሐይማኖት ተከታዮች በጋራ የሚኖሩባት ከተማ እንደ ሆነች የሚያመልክት መልእክት ይፋ አድርገናል።
ሞሃመድ 5ኛ እና ሀሰን ሁለተኛ የተቀበሩበትን ስፍራ ጎብኝቼ የነበረ ሲሆን ከዚያም በመቀጠል ደግሞ ለእነርሱ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ የተቋቋመውን ኢማሞች የሌሎች የሐይምኖት ተቋማትን ማክበር እንደ ሚገባ እና ማነኛውንም ግጭት ማስወገድ እንደ ሚገባ ስልጠና የሚወስዱበትን ሥፍራ ጎብኝቻለሁ።
በተለይም ደግሞ የስደተኞችን ጥያቄ በተመለከተ በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥቼ ከአገሪቷ ባለስልጣናት ጋር እና እንዲሁም ከስደተኞች ጋር በተገናኘውበት ወቅት ይህ ጉዳይ ከፍተኛ የሆነ ትኩረት ይሰጠው ዘንድ የበኩሌን ጥረት አድርጊያለሁ። ከእነሱ መካከል አንዳንዶቹ የስደተኞች ሕይወት ሊቀየር የሚችለው እና ሕይወታቸው ሰብዓዊ ክብሩን ጠብቆ ሊጓዝ የሚችለው ማኅበርሰቡ እነርሱን እንደ ሰው አድርጎ ሲቀበላቸው ብቻ እንደ ሆነ ገልጸውልኝ ነበር። ይህ መሰረታዊ የሆነ ነገር ነው። ባለፈው ታኅሣሥ ወር በሞሮኮ በምትገኘው በማራካሽ በተደረገው ስብሰባ ላይ “የስደተኞችን ፍልሰት ሥርዓት ባለው መልኩ ለማስተናገድ የሚረዳ ዓለም አቀፍ የመግባቢያ ሰንድ ይፋ መሆኑ ይታወሳል። ይህም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በዚህ ጉዳይ ላይ ኃላፊነት እንዲወስድ የሚያደርግ አስፈላጊ እና የመጀመሪያው እርምጃ ነበር። እንደ ቅዱስት መንበር እኛም ለዚህ ቀደም ሲል ተካሂዶ ለነበረው ጉባሄ የበኩላችንን አስተዋጾ በማድረግ አራት ግሶችን በመጠቀም መቀበል፣ መንከባከብ፣ ማራመድ እና ማዋሃድ የሚሉትን ጽንስ ሐሳቦችን ከግምት ያስገባ መልእክት አስተላልፈናል። ከላይ የተጠቀሱትን የበጎ አድራጎት መርሃግብሮችን መቀነስ አይደለም፣ ነገር ግን በአራቱም ድርጊቶች ላይ የተቀናጀ ጉዞ ማድረግ፣ የየራሳቸውን ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ማንነቶች ጠብቆ ማቆየት እና ለሰብአዊነት እና ለወንድማማችነት መንፈስ እንዴት ዋጋ መስጠት እንደሚችሉ ለማወቅ ያስችላቸዋል። በሞሮኮ የሚገኘው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ረገድ ከፍተኛ የሆነ አስተዋጾ በማድረግ ለስደተኞች ያላትን ቅረበት በመግለጽ ክርስቶስን በቃሉ “ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛል” ያለውን ቃሉን በተግባር ላይ እያዋለች ትገኛለች።
እሁድ እለት ደግሞ ለክርስቲያን ማኅበርሰቡ ትኩረት የተሰጠበት እለት ነበር። በቅድሚያ የፍቅር ሥራ ልጆች ማኅበር አባላት ደናግላን በገጠራማ ሥፋር እያከናወኑት የሚገኘውን የማኅበራዊ የበጎ ሥራ ተግባር ጎብኝቻለሁ፣ በዚህም ማኅበራዊ የበጎ ሥራ ተገባራቸው ከብዙ የበጎ ሥራ የነጻ አገልግሎት ከሚሰጡ ሰዎች ጋር በተቀናጀ መልኩ እያከናወኑ የሚገኙትን ማኅበራዊ አገልግሎት ጎብኝቻለሁ።
በራባት በሚገኘው ካቴድራል ውስጥ በዚያ በሞሮኮ ከሚኖሩ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ካህናት፣ ገዳማዊያን ገዳማዊያት እና እንዲሁም ለሐይማኖት ሕብረት ከሚሰራው ተቋም ተወካዮች ጋር ተገናኝቻለሁ። በሞሮኮ የምትገኘው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በሞሮኮ ውስጥ እንደ አንድ ትንሽዬ መንጋ የምትቆጠር ስትሆን ለዚህም ነው በቅዱስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሰውን የጨው፣ የብርሃንና የእርሾ ምሳሌን ተጠቅሜ የተናግርኩት በዚሁ ምክንያት ነው። ዋናው እና አስፈላጊው ነገር ብዛት አይደለም፣ ነገር ግን የጨው ጣዕም፣ የሚያበራ ብርሃን፣ እና ለመላው ማኅበረሰብ ጥንካሬን የሚሰጥ እርሾው መሆን ነው የሚገባው። ይህ ደግሞ የሚመጣው ከእኛ ሳይሆን ከእግዚኣብሔር እና ከመንፈስ ቅዱስ ሲሆን ይህም የክርስቶስ መስካሪዎች እንድንሆን እኛን በማብቃት በመውይይት እና በጓደኝነት መንፈስ እንድንኖር እና በተለይም ይህንን መንፈስ በእኛ በክርስትያኖች ውስጥ በማጽናት እየሱስ በወንጌሉ እንደ ተናገረው “እርስ በርሳችሁ ብትዋደዱ፣ ሰዎች ሁሉ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።” (ዮሐንስ 13፡35) ያለውን ቃል በተግባር ላይ ማዋል ይኖርብናል።
የቤተ ክርስቲያን ሕብረት የደስታ ምንጭ የሆነው በቅዱስ ቁርባን አማካይነት ከሚገኘው መሰረታዊ እና አስፈላጊ ጸጋ ሲሆን ይህም በእለተ ሰንበት በሚደረግ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ የምንቋደሰው መሰረታዊ ነገር ነው። በራባት ባሳረኩት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ከስልሳ በላይ የተለያዩ አገራት ዜጎች ተገኝተዋል። እስላማዊ በሆነ ሀገር ውስጥ የተከናወነው የእግዚአብሔር ህላዌ መገለጫ ነው። በወቅቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ የነበረው የርኅሩ አባት ምሳሌ በመካከላችን ውስጥ የእግዚአብሄር ንድፍ ሐሳብ ውበት አድርጎ የገለጸ ሲሆን ይህም ልጆቹ በሙሉ የእርሱን ምሕረት፣ እርቅ እና የመታደስ በዓል በደስታ እንዲካፈሉ እንደ ሚፈልግ ይገልጻል። በዚህ ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰው ድግስ ላይ የአባት ምህረት እንዴት እንደሚያስፈልጋቸው እና አንድ ወንድምና እህት ወደ አገራቸው ተመልሰው ሲገናኙ የሚከሰተውን ከፍተኛ ደስታ ያሳያል። ወንድሞቻችን የእስልማን እመንት ተከታዮችም ሳይቀሩ መሐሪ የሆነ አባታቸውን በእየለቱ የሚለምኑት እና የሚማጸኑትም በዚሁ ምክንያት ነው። በዚህም ምክንያት ዳግመኛ የሚወለዱና በአባታቸው እቅፍ ውስጥ መኖር የሚጀምሩ ሰዎች ሁሉ በዓለም ላይ በተስፋ የተሞሉ የእርሱ አገልጋዮች ለመሆን ይችላሉ።