ፈልግ

“የዐብይ ጾም ወቅት እግዚአብሔር በፍቅር እንዲመለከተን የምናደርግበት፣ ሕይወታችንን የምንቀይርበት የጸጋ ወቅት ነው!”

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር መሰረት የላቲን ስርዓተ አምልኮ በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በየካቲት 18/2012 ዓ.ም የዐብይ ጾም ወቅት መጀመሩ ይታወቃል። ይህ የዐብይ ጾም ወቅት የተጀመረው የሰው ልጆች ሁሉ ያለእግዚኣብሔር ድጋፍ እና ምሕረት ከንቱ መሆናችንን እንድናስታውስ እና ብሎም በዚህ በዐብይ ጾም ወቅት በሰራናቸው ኃጢአቶቻችን መጸጸታችንን በመግለጸ የፋሲካን በዓል መንፈሳዊ ለውጥ በማምጣት ተገቢ በሆነ መልኩ ለማክበር መንፈሳዊ ዝግጅት የምናደርግበት ወቅት መሆኑን በይፋ በመግለጸ በይፋ መጀመሩ ይታወቃል። በጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር መሰረት የላቲን ስርዓተ አምልኮ በምትከተለው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የዐብይ ጾም ወቅት በየካቲት 18/2012 ዓ.ም በተጀመረበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራነቸስኮስ በሮም ከተማ በሚገኘው ሳንታ ሳቢና ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ባደሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስበከት ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት “የዐብይ ጾም ወቅት እግዚአብሔር በፍቅር እንዲመለከተን የምናደርግበት እና ሕይወታችንን የምንቀይርበት የጸጋ ወቅት ነው” ማለታቸውን ከደረሰን መረጃ ለመረዳት ተችሉዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በትላንታንው እለት ማለትም በየካቲት 18/2012 ዓ.ም የዐብይ ጾም በተጀመረበት ወቅት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ያሰሙትን ስብከት ሙሉ ይዘት እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

ይህንን የዐብይ ጾም ወቅት የምንጀምረው “ዐፈር ነህና ወደ አፈርም ትመለሳለህ (ዘፍ 3፡ 19) በማለት የዐመድ መቀባት ስነ-ስረዓት በመፈጸም ነው። ራሳችን ላይ የሚነሰነሰው ዐመድ ወደ ምድር ይመልሰናል፣ አፈር እንደሆንንና ወደ አፈርም እንደምንመለስ ያስታውሰናል። እኛ ደካሞች፣ ተሰባሪዎች እና ሟች ነን። ምዕተ ዓመታት እና ሺህ ዓመታት ያልፋሉ እኛም እንመጣለን እንሄዳለንም አዕላፍ ከሆኑ ብዙ ከዋክብት እና ሕዋዕ ጋር ስንነጻጸር ግን እኛ እሚንት ነን። እኛ በአጽናፈ ሰማይ ውስጥ የምንገኝ አፈር ነን። ነገር ግን እኛ በእግዚአብሔር የተወደድን አፈር ነን። ጌታ ያንን አፈር በእጆቹ በመሰብሰብ በእርሱ ውስጥ የሕይወትን እስትንፋስ መዝራት ደስ ያሰኘዋል (ዘፍ 2: 7)። ስለሆነም እኛ ውድ የሆንን ሕይወት፣ ለዘለአለም ህይወት የታጨን አፈር ነን። እኛ እግዚአብሔር ሰማይን የመሰረተበት ሕልሞቹን የያዝን አፈር ነን። እኛ የእግዚአብሔር ተስፋ ፣ ሀብቱ እና ክብሩ ነን።

ስለዚህ አመድ የሕይወታችን አቅጣጫ ማሳሰቢያ ነው፣ ከአፈር ወደ ሕይወት የሚያልፍ መተላለፊያ ነው። እኛ አፈር፣ አፈር እና ሸክላ የሆንን ሰዎች ስንሆን ነገር ግን እግዚአብሔር በእጁ እንዲቀርጸን ከፈቀድንለት ደግሞ አስደናቂ የሆነ ነገር እንሆናለን። ብዙውን ጊዜ በተለይ በችግር እና በብቸኝነት ጊዜያት አፈር መሆናችንን ብቻ እናያለን! ነገር ግን ጌታ ያበረታታናል - በእርሱ ፊት ጥቃቅን ብንሆንም ነገር ግን ከፍተኛ ዋጋ አለን። ስለዚህ አይዞዋችሁ፣ እኛ የተወለድነው ለመወደድ ነው፣ የእግዚአብሔር ልጆች ሆነን የተወለድን በእዚህ ምክንያት ነው።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች ፣ ይህንን የዐብይ ጾም ወቅት ስንጀምር ይህንን በአእምሮአችን እናስታውስ። የዐብይ ጾም ወቅት ዋጋ ቢስ የሆኑ ስነ-ስረዓቶችን የመፈጸሚያ ጊዜ ሳይሆን ነገር ግን በእግዚኣብሔር የተወደድን አፈር መሆናችን የምንገነዘብበት ወቅት ነው። ይህ ወቅት እግዚአብሔር በፍቅር እንዲመለከተን የምናደርግበት እና በዚህ መንገድ ሕይወታችንን የምንቀይርበት የጸጋ ወቅት ነው። በእዚህ ምድር ውስጥ የተፈጠርነው ከአፈርነት ወደ ሕይወት እንድንሻገር ነው። ስለዚህ ተስፋችንን እና የእግዚአብሔርን ሕልም ወደ ዱቄትነት እና አመድነት አንቀይረው! እንዲህ ብለን ልንጠይቅ እንችላለን “እንዴት ልተማመን እችላለሁ? ዓለም ፈርሷል፣ ፍርሃት እየጨመረ ነው፣ በዙሪያችን ሁሉ ብዙ ክፋቶች አሉ፣ ክርስቲያን የሆነው ሕብረተሰብ በቁጥር እየቀነስ ነው” በማለት ጥያቄ ልናነሳ እንችል ይሆናል። እግዚኣብሔር አፈርችንን ወደ ክብር ይለውጣል ብለህ ታምናለህ ወይ?

በግንባራችን ላይ በዐመድ የተቀባነው ምልክት በአዕምሮአችን ውስጥ የሚያልፉትን ሀሳቦች ይነካል። ይህ ስነ-ስረዓት የእግዚአብሔር ልጆች እንደ መሆናችን መጠን ህይወታችንን አፈር እያባከንን ማሳለፍ እንደማንችል ያስታውሱናል። ከእዚህ ጀምሮ አንድ ጥያቄ ወደ ልባችን ውስጥ ሊገባ ይችላል-“የምኖረው ለኔ ነው?” የእዚህች ዓለም ነባራዊ እውነታዎች የሚያመለከቱት እግዚአብሔር በሕይወቴ ያደረገውን ነገር የማንቀበል ከሆንን አመድ እና አፈር ነበርን ወደ እዚያው እንደ ምንመለስ ያመለክቱናል። የምኖረው ገንዘብ ለማግኘት ፣ ጥሩ ጊዜ ለማሳለፍ ፣ በስራዬ ውስጥ ትንሽ ክብር ወይም ከፍ ያለ ቦታ ለማግኘት ብቻ ከሆነ ለአፈርነት እኖራለሁ። በቂ አክብሮት ካላገኘው ወይም እኔ የሚገባኝን ነገር ካላገኘው በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ ደስተኛ ካልሆንኩኝ እኔ እንደ አፈር ነኝ ማለት ነው።

በዚህ ዓለም ውስጥ እንድንፈጠር የተደረገው ለዚህ አይደለም። እኛ ከእዚህ በላይ ዋጋ ያለን ሰዎች ነን። እኛ የእግዚአብሄርን ህልም እና ፍቅር እውን ለማድረግ የተፈጠረን በመሆናችን የተነሳ ከእዚህ የተሻለ መኖር ይጠበቅብናል። የፍቅር እሳት በልባችን ውስጥ እንዲነድድ አመድ በራሳችን ላይ ይረጫል። እኛ የሰማይ ዜጎች ነን ፣ እናም ለእግዚአብሄር እና ለጎረቤታችን ያለን ፍቅር ወደ ሰማይ የሚወስደን ፓስፖርታችን ነው።  ምድራዊ ንብረታችን ምንም ጥቅም እንደሌለው አፈር የሚበላሽ ይሆናል፣ ነገር ግን በቤተሰቦቻችን፣ በስራችን ፣ በቤተክርስቲያን እና በዓለም ውስጥ ከሚኖሩ ሰዎች ጋር የምንካፈለው ፍቅር ለዘላለም ያድነናል።

በግንባራችን ላይ የምንቀባው አመድ ስለ ሁለተኛው እና ተቃራኒ ስለሆነው ነገር ያስታውሰናል-ከሕይወት ወደ አፈር። በዙሪያችን ያለው የሞትን አፈር እናያለን። ሕይወት ወደ አመድነት ሲቀየር እንመለከታለን። አመጽ፣ ጥፋት ፣ ጦርነት። የንፁህ ሰዎች ሕይወት፣ የተገለሉ እና ድሃ የሆኑ ሰዎች ሕይወት፣ የተዘነጉ ሰዎች ሕይወት። እራሳችንን ማጥፋታችንን እንቀጥላለን ፣ ወደ አመድ እና ወደ አፈርነት እንመለሳለን። በግንኙነቶቻችን ውስጥ ምን ያህል አፈር አለ! ቤቶቻችንን እና ቤተሰባችንን ተመልከቱ- አለመግባባቶች፣ ግጭቶችን መፍታት አለመቻላችን፣ ይቅርታ ለመጠየቅ ፈቃደኛ አለመሆን፣ ይቅር አለማድረግ፣ ግጭትን በአዲስ መልክ መጀመር፣ በተመሳሳይ ጊዜ ለራሳችን ነፃነት እና መብቶቻችን አጥብቀን እንከራከራለን! ፍቅራችንን የሚያደፈርስ እና ህይወታችንን የሚያበላሸው ይህ አፈር ነው። በቤተክርስቲያን ውስጥ በእግዚአብሔር ቤት እንኳን ሳይቀር ብዙ የተሰበሰበ አፈር፣ የዓለም አፈር ይገኛል።

ወደ ልባችን ወደ ውስጣችን እንመልከት- ስንት ጊዜ ነው የእግዚአብሄርን እሳት በግብዝነት አመድ የምናጠፍው! ግብዝነት እኛ ልናስወግደው የሚገባን ነገር ሲሆን በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ ኢየሱስ የነገረን ርኩሰት ነው። በእርግጥ ጌታ የበጎ አድራጎት ስራዎችን እንድንፈጽም፣ እንድንፀልይ እና እንድንጾም ብቻ ሳይሆን የሚጠይቀን ነገር ግን እነዚህን ነገሮች ያለቅድመ ሁኔታ፣ ብዥታ እና ግብዝነት እንድንፈጽም ነግሮናል (ማቴ 6፡2.5.26)። ነገር ግን ምን ያህል ጊዜ ነው ነገሮችን ለመታወቅ ብለን፣ ጥሩ ለመምሰል እና የራስ ወዳድነት ፍላጎታችንን ለማርካት የምንፈጽመው! ብዙን ጊዜ ክርስቲያን ነን እንላለን ነገር ግን በልባችን ውስጥ ባሪያዎች ሊያደርገን የተዘጋጀውን ምኞት እንከተላለን! ምን ያህል ጊዜ ነው የሰበክነውን በተግባር ላይ ያዋልነው! በውስጣችን ቂም እየያዝን በውጭ ጥሩ ሰዎች እንደ ሆንን አድርገን እናሳያለን! በልባችን ውስጥ ምን ያህል ድግግሞሽ አለን… እነዚህ ሁሉ በፍቅር ላይ ያለውን እሳት የሚያጠፋ አመዶች ናቸው።

ልባችንን የሸፈነውን አፈር ሁሉ መንጻት አለብን። እንዴት? በዛሬው በሁለተኛው ንባብ ውስጥ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ አስቸኳይ ጥሪ ማድረጉ እኛን ሊረዳን ይችላል። ጳውሎስ “ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ” በማለት ተናግሯል። እሱ እንዲያው በቀላሉ ከእርሱ ጋር እንድንታረቅ ብቻ ሳይሆን የሚጠይቀን ነገር ግን እርሱ “ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን በክርስቶስ እንለምናችኋለን” (2ቆሮ 5፡20) ብሎ በመማጸን ጭምር ነው። እኛ “ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ!” ብለን ልንናገር እንችል ይሆናል። ነገር ግን ሐዋርያው ጳውሎስ የተጠቀመው የቃላት አገላለጽ ከእርሱ ጋር ታረቁ! የሚለው ነው። ቅድስና በእኛ ጥረት አይገኝም ፣ ምክንያቱም ጸጋ ነው! በራሳችን ልባችንን የሚያደናቅፈውን አፈር ማስወገድ አንችልም። ልባችንን የሚያውቅ እና የሚወደው ኢየሱስ ብቻ ነው ሊፈውሰው የሚችለው ፡፡ የዐብይ ጾም ወቅት የመፈወሻ ወቅት ነው።

ታዲያ ምን ማድረግ አለብን? ወደ ፋሲካ ለመጓዝ ሁለት እርምጃዎችን ማድረግ እንችላለን - በመጀመሪያ ከአፈር ወደ ሕይወት፣ ከደካማው ሰብአዊነታችን ሰብአዊነታችንን ወደ ሚፈውሰው ኢየሱስ መጓዝ ይኖርብናል።  በተሰቀለው ጌታ መስቀል ፊት ቆም ብለን “ኢየሱስ ሆይ ወደኸኛል፣ ቀይረኸኛል …” በማለት ደጋግመን ልንናገር ይገባል። እናም አንዴ ፍቅሩን ከተቀበልን በኋላ ሕይወታችን ዳግም ወደ አፈር ውስጥ ገብታ እንዳትወድቅ ቁርጥ ፈቃድ በማደረግ እና ያንን የኢየሱስን ፍቅር በማሰብ ወደ ሁለተኛው ደረጃ እንሻገራለን። በምስጢረ ንስሐ አማካይነት የእግዚአብሔርን ይቅርታ ማግኘት እንችላለን ምክንያቱም እዚያ የእግዚአብሔር ፍቅር እሳት የኃጢያታችንን አመድ ይበላልና። በምስጢረ ንስሐ አማካይነት በእግዝኣብሔር እቅፍ ውስጥ መግባት ልባችንን ያነጻል። ከእግዚኣብሔር ጋር ለመታረቅ ፈቃደኞች እንሁን፣ በእዚህ መልኩ የእርሱ ተወዳጅ ልጆቹ ሆነን ለመኖር እንችላለን፣ ኃጢአቶቻችን ይሰተሰረያሉ፣ ከእርሱም ጋር ታርቀን ለመኖር እንችላለን።

እኛም በምላሹ ፍቅርን መስጠት እንድንችል እንድንወደው ፈቃደኛ እንሁን። ተነስተን ወደ ፋሲካ በዓል መንገድ መጓዝ እንችል ዘንድ ራሳችንን እናዘጋጅ። ያኔ እግዚአብሔር ከአመድ ላይ እንዴት እንደ ሚያነሳን  በማወቅ ደስታ እንገኛለን።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

 

26 February 2020, 15:54