“ጨለማን የሚያስወግድ ሐዋርያዊ የቅዱስ ቁርባን ቡራኬ እና ሥርየተ ኃጢአት ጸሎት”
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የዓለማችን ስጋት የሆነው ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንዲቆም በማለት ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ጥልቅ ጸሎት በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። ለሰው ልጅ ከባድ ፈተና የሆነውን ይህን ወቅት ምዕመናን በጠንካራ እምነት እና ተስፋ እንዲኖሩ አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው፣ ዓርብ መጋቢት 18/2012 ዓ. ም. በኢትዮጵያ የሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 2:00 ላይ ለሮም ከተማ ሕዝብ እና ለዓለም ሕዝብ በሙሉ በሚያቀርቡት የቅዱስ ቁርባን ቡራኬ ጸሎት እና የጠቅላላ ሥርየተ ኃጢአት ሥነ ሥርዓት ላይ መላው ካቶሊካዊ ምዕመናን በመንፈስ እንዲተባበሯቸው አደራ ብለዋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን ከሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሮም ከተማ እና ለመላው ዓለም ሕዝብ በሚያቀርቡት ሐዋርያዊ ቡራኬ እና የቅዱስ ቁርባን ጸሎት ላይ ካቶሊካዊ ምዕመናን በመንፈስ በመካፈል የምሕረት ጸጋን የሚቀበሉ መሆኑ ታውቋል። ይህ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት በተለያዩ ማኅበራዊ መገናኛዎች በኩል ከቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በቀጥታ የሚተላለፍ መሆኑ ታውቋል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን እያዳረሰ ባለበት በዚህ ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሚያቀርቡት ጸሎት እና ሐዋርያዊ ቡራኬ በስቃይ እና በጭንቀት ውስጥ የሚገኝ ሕዝብ በእምነቱ እንዲጸና እና ተስፋንም እንዲያደረግ የማበረታታ መሆኑ ታውቋል። ወደ ቅዱስ ቁርባን ከሚደረግ ጸሎት በመቀጠል የሚደረግ ሐዋርያዊ ቡራኬ ሥነ ሥርዓት በጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር 1100 ዓ. ም. መጨረሻ እና በ1200 መጀመሪያ በቤልጄም አገር የተጀመረ መሆኑ ይታወሳል። ይህ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት በመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ዘንድ እንዲፈጸም በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ኡርባኖስ አራተኛ፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ1264 ዓ. ም. መደንገጋቸው ይታወሳል። ከር. ሊ. ጳጳሳት ኡርባኖስ አራተኛ ውሳኔ አንድ ዓመት አስቀድሞ በመካከለኛው ምሥራቅ ጣሊያን፣ ቦልሰና በተባለ አካባቢ የቅዱስ ቁርባን ተዓምር መታየቱ ይታወሳል። ቀጥሎም በአብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ በኩል ተቀባይነትን አግኝቶ እንዲበረታታ መደረጉ ሲታወስ፣ እስከ ዛሬ ድረስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የሮም ከተማን እና የዓለም ምዕመናንን በቅዱስ ቁርባን የሚባርኩት ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ለማስተዳደር ሐዋርያዊ ስልጣን በተቀበሉበት ዕለት፣ የሮም ሀገረ ስብከት እና የመላዋ ካቶሊካዊ ቤተክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በመሆናቸው፣ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ትንሳኤው ክብረ በዓል እና በብርሃነ ልደቱ ክብረ በዓል ዕለት መሆኑን የሥርዓተ አምልኮ ሊቅ የሆኑት ክቡር አባ አርቱሮ ኤልቤርቲ ገልጸው ይህ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ ቡራኬ ከምስጢረ ንስሐ ፍሬዎች ጋር በጥብቅ የተያያዘ በመሆኑ የምሕረት ጸጋን የሚያስገኝ መሆኑን አስረድተዋል።
“ሥርየተ ኃጢአት፣ በደሉ ይቅር የተባለለት ኃጢአት የሚያስከትለው ጊዜያዊ ቅጣት በእግዚአብሔር ፊት መደምሰስ ሲሆን ሸክሙ የወረደለት ምዕመን በውል በታወቁ ሁኔታዎች የመዳን አገልጋይ በመሆኗ የክርስቶስ እና የቅዱሳን ካሣ መዝገብ ሰጭ እና እነርሱንም የመፈጸም ሥልጣን ያላት ቤተክርስቲያን በምትከነውነው ድርጊት አማካይነት የሚያገኘው ምሕረት ነው” በማለት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ያስረዳል። ቤተክርስቲያን ይቅርታን ለማድረግ ስልጣን ያላት መሆኑን ያስረዱት፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቅ ክቡር አባ ፍራንችስኮ ቮልታጆ፣ ኃጢአት በራሳችን እና በሌሎች ሰዎች ሕይወት የሚፈጥረው ቁስል መኖሩን ገልጸው በሌላ ወገን ኃጢአትን በሙሉ የሚያስወግ የኢየሱስ ክርስቶስ የምሕረት ጸጋ በቅዱሳን አንድነት የሚያሳትፍ መሆኑን አስረድተዋል። በመሆኑም በአንዳንድ ልዩ አጋጣሚዎች የቤተክርስቲያን አባቶች እነዚህን የምሕረት ጸጋዎችን በመጠቀም ለግል እና ለሙታን ጠቅላላ ሥርየተ ኃጢአትን ለማስገኘት በጸሎት ያቀርቡታል።
ጠቅላላ ሥርየተ ኃጢአት የተባለበት ምክንያት ኃጢአትን እና ኃጢአት ያስከተላቸውን መዘዞች የሚያስወግድ በመሆኑ፣ በተለይም ምዕመናን ምስጢረ ንስሐን መቀበል በማይችሉበት እና አንዱ ከሌላው ተነጥሎ እንዲቀመጥ በሚደረግበት የጭንቀት ወቅት፣ የምሕረት ጸጋን በመንፈስ ቅዱስ አንድነት በኩል መስጠት እንዲቻል በቅርቡ የተጠቀሰው ሐዋርያዊ ድንጋጌ ማዘዙ ይታወሳል። በዚህ መልክ የሚሰጥ ሥርየተ ኃጢአት በኮሮና ቫይረስ ለተጠቁ ምዕመናን እና ረዳቶቻቸው፣ ከሁሉም በፊት ለወላጅ ቤተሰብ እና የሕክምና ባለሞያዎች፣ በጸሎታቸው ሕሙማንን ለሚያስታውሱ ምዕመናን መሆኑን ሐዋርያዊ ድንጋጌው ያስረዳል። ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ በሰዎች ሕመም፣ ጭንቀት እና ድካም መካከል ርህራሄውን የሚገልጽበት፣ የቅርብ ረዳት እና አጽናኝ መሆኑ የሚያሳይበት መንገድ መሆኑን የሕገ ቀኖና ሊቅ፣ ክቡር አባ አንጦንዮስ ኢንተርጓሊየልሚ አስረድተዋል።
ሕዝቦች በመከራ እና ጭንቀት ውስጥ በሚገኙበት ጊዜ ቤተክርስቲያን መጽናናትን እና ብርታትን ለመስጠት ዝግጁ መሆኗን የገለጹት ክቡር አባ አንጦንዮስ ኢንተርጓሊየልሚ ከጸጋዎች ሁሉ በላይ የሆነውን ልዩ የምሕረት ጸጋ በጦርነቶችና በተለይም በመቅሰፍቶች ጊዜ የምትሰጥ መሆኑን አስረድተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዓርብ መጋቢት 18/2012 ዓ. ም. በኢትዮጵያ የሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 2:00 ላይ በሚያቀርቡት የጸሎት እና የሐዋርያዊ ቡራኬ ሥነ ሥርዓት ላይ የሮም ከተማ የፈውስ እናት የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ምስል እና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ መስቀል የሚገኝ መሆኑ ታውቋል። እነዚህ ሁለቱ ቅዱሳት ምስሎች የሮም ከተማ በወረርሽኝ በተጠቃበት ጊዜ ነዋሪው ሕዝብ በመንፈስ በመተባበር በእምነት ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ጸሎታቸው በማቅረብ ምሕረትን የለመኑባቸው ምስሎች መሆኑ ታውቋል።