ር.ሊ.ጳ ፍራንችስኮስ “የጋራ የመኖሪያ ቤታችን የሆነችውን ምድር እንከባከብ” አሉ።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሚያዝያ 14/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ ሕንጻ ውስጥ ከሚገኘው ቤተ-መጽሐፍት ውስጥ ሁነው ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትኩረቱን አድርጎ የነበረው በሚያዝያ 14/2012 ዓ.ም በአለም አቀፍ ደረጃ ለ50ኛ ጊዜ በተከበረው የምድር ቀን ላይ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን ለፍጥረታት በሙሉ ጥበቃ ማደረግ እንደ ሚገባ ገልጸዋል።
የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን
የጋራ መኖሪያ ቤታችን የሆነችውን ምድራችንን ለመንከባከብ ይቻል ዘንድ ያለንን ግንዛቤ ከማሳደግ ይልቅ ምድራችንን እየበከልን እና አያዘበራረቅን እንገኛለን በማለት አስተምህሮዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ከታች አንስቶ እስከ ላይ ድረስ ለምድራችን እንክብካቤ ማድረግ የሚያስችል ግንዛቤ ሊፈጠር ይገባል ብለዋል።
በእርግጥ በአሁኑ ወቅት አሳዛኝ በሆነ ሁኔታ እየተከሰተ የሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በእውነቱ አንድ ላይ በመሆን በጣም አቅመ ደካማ የሆኑትን የማኅበረሰብ ክፍል በመርዳት “ዓለም አቀፍ የሆኑ ፈተናዎችን ማሸነፍ እንደምንችል” ያሳየን አጋጣሚ ነው ብለዋል። ስለሆነም በምድራችን ላይ እየተከሰተ የሚገኘውን ውድመት ለማስቀረት፣ ሌሎች ፍጥረታትን ለመንከባከብ እና ለሌሎች ያለንን ፍቅር እና ርህራሄ ለማሳደግ “ሥነ-ምህዳርን የተመለከተ ውይይት” እና “የጋራ ዕቅድ” ያስፈልጋል ብለዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ከእዚህ ቀደም በተራራው ላይ ኢየሱስ ያደረገው ስብከት ላይ ተመርኩዘው በተከታታይ ሲያደርጉት የነበረውን አስተምህሮ ለአፍታ ያህል አቁመው በዕለቱ በሚያዝያ 14/2012 ዓ.ም ለሃምሳኛ ጊዜ በአለም አቀፍ ደረጃ በተከበረው የዓለም የመሬት ቀን መታሰቢያ በዓል ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ ሲሆን ይህ አለም አቀፍ የመሬት ቀን የተከበረው እርሳቸው የዛሬ አምስት አመት ገደማ በላቲን ቋንቋ “Laudato si’” በአማርኛው “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚል አርዕስት ያፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ መልዕክት ጭብጥ ለሁሉም ይዳረስ እና ግንዛቤ ይፈጠር ዘንድ በእየ አመቱ በተመሳሳይ ቀን በጣሊያን የሚከበር ሲሆን ዘንድሮ ግን በኮሮና ቫይረስ ወረርሽ ምክንያት ሳይከበር መቀረቱ ተገልጿል።
ምድር በእውነቱ “የሀብት ማከማቻ” አይደለም ፣ ነገር ግን “ለእኛ አማኞች ተፈጥሮአዊው ዓለም ‘የፍጥረት ወንጌል’ ነው በማለት በአጽኖት የገለጹት ቅዱስነታቸው ይህ ደግሞ ፍጥረታትን ለመመልከት የሚያስችለን “አዲስ መንገድ” ነው ብለዋል። እኛ በእርግጥ እርስ በእርሳችን የተሳሰርን፣ አንዱ ያለሌላው ሊኖር የማይችል የአንድ ቤተሰብ አባል ነን ያሉት ቅዱስነታቸው ከምድር በተወሰደ አፈር የተሰራን እና ከእግዚአብሄር እስትንፋስ የተቀበልን በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠርን የአንድ ቤተሰብ አካል ነን ብለዋል።
ምድራችንን መንከባከብ ሲገባን ነገር ግን በራስ ወዳድነት መንፈስ ምክንያት “ባለጠጎች” ለመሆን በምናደርገው እሽቅድድም ምክንያት ምድራችንን የመንከባከብ ኃላፊነት ዘንግተናል፣ በእዚህም ተግባራችን በቅድሚያ የምንጎዳው እኛ ራሳችን ነው ብለዋል። ስለሆነም አሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “ሕሊናችን ከወሰደው እንቅልፍ እንዲነቃ” ለማድረግ የሚያስችሉ በአሁኑ ወቅት በመካሄድ ላይ ለሚገኙት “ልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ እና አካባቢያዊ እንቅስቃሴዎች” ልባዊ አድናቆታቸውን ገልጸዋል። “ልጆቻችን ይህንን ለማስተማር ወደ ጎዳና መውጣታቸው አሁንም አስፈላጊ ነው” ያሉ ሲሆን “ግልፅ ነው ይህንን ማደረግ ካልቻልን ደግሞ እኛ የወደፊት ሕይወት አይኖረንም ማለት ነው” ብለዋል። ስለሆነም እያንዳንዳችን ይብዛም ይነስም የራሳችንን አስተዋጾ ለማደረግ ቁርጠኛ መሆን ይጠበቅብናል ብለዋል።
“በተቀናጀ መልኩ በብሔራዊም ሆነ በአከባቢ ደረጃ እየተደረጉ የሚገኙትን ቁርጠኛ እንቅስቃሴዎች ለማበረታታት እፈልጋለሁ፣ እያንዳንዱን ማሕበራዊ አደረጃጀት በአንድ ላይ አሰባስቦ ከተቻ እሰከ ላይ ደረስ የተቀናጀ እንቅስቃሴ በማደረግ ምድራችንን መንከባከብ ያስፈልጋል” ብለዋል።
ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ፣ ከጎረቤታችን ፣ ከድሆች ጋር እና ከምድር ጋር “ግንኙነትን” የመፍጠር ጥያቄም ነው ያሉት ቅዱስነታቸው ስምምነትን የሚፈጥር መንፈስ ቅዱስ ነው ብለዋል።
ዛሬ የዓለም የምድር ቀንን በማክበር ላይ በምንገኝበት ወቅት የእኛ መኖሪያ ቤት ብቻ ሳትሆን የእግዚአብሔር ቤትም ጭምር የሆነችውን ምድራችንን ቅዱስ የሆነ አክብሮት እንድናጸባርቅ ተጠርተናል ያሉት ቅዱስነታቸው ከዚህ በመነሳት በተቀደሰች ምድር ላይ እየኖርን እንደ ሆንን የሚገልጽ ግንዛቤ ላይ ለመድረስ አንችለን ብለዋል።
እግዚአብሔር ምድርን እና በምድር ላይ የሚኖሩትን በሙሉ ከፈጠረ በኋላ እጅግ በጣም መልካም መሆኑን እንደ ተመለከተ ያስትወሱት ቅዱስነታቸው ነገር ግን “አሁን እየተከሰቱ የሚገኙት የተፈጥሮ አደጋዎች” እኛ ለምድር የሰጠነው ምላሽ ነጸብራቅ ናቸው ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “እኛ ነን እንጂ ምድራችንን ያበላሸናት ጌታ ሲፈጥራት ግን መልካም ነበረች” ብለዋል።
ስለሆነም አሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “እግዚአብሔር ሁል ጊዜ ይቅር ይለናል ፣ ይቅር ባይም ነው” ያሉ ሲሆን እኛ ሰዎች ግን አንዳንዴ ይቅር እንላለን፣ አንዳንዴ ደግሞ ይቅርታ አናደርግም፣ ምድራችን ግን በጭራሽ ይቅር አትለንም ብለዋል። እኛ ምድራችንን ካበላሸናት ምላሹ እጅግ መጥፎ እና አደገኛ ይሆናል ያሉት ቅዱስነታቸው ከምድር ጋር የተሳሰረ ሕይወት፣ ከምድራችን ጋር ተሳማሚ የሆነ ሕይወት፣ ከምድራችን ጋር ጠንካራ የሆነ ግንኙነት በመፍጠር መኖር ይኖርብናል ብለዋል።
የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ መልዕክት ምድራችንን በመንከባከብ ሂደት ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ተሳታፊ ሊሆኑ ለሚገባቸው የመንግሥት ባለስልጣናት እና ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጭምር የተደረገ ጥሪ ሲሆን የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ትብብር መፍጠር እንደ ሚገባውም ጥሪ አድርገዋል።፡ በመጨረሻም ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በዚህ የፋሲካ በዓል ወቅት የምድርን አስደናቂ ስጦታ እንድናደንቅ እና ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን መንከባከባችንን መቀጠል ይኖርብናል ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው አስተምህሯቸውን አጠናቀዋል።