ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “የክርስቲያን ጸሎት በቅርበት በመተማመንና በእምነት የሚደረግ ጸሎት ነው” አሉ!
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደምያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በእዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በግንቦት 05/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ ቤት ውስጥ ከሚገኘው ቤተ መጸሐፍት ውስጥ ያደረጉት ሳምንታዊ አስተምህሮ በተለያዩ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች መተላለፉ ተገልጹዋል። በወቅቱ ቅዱስነታቸው ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከእዚህ ቀደም ባለፈው ሳምንት በጸሎት ዙሪያ ላይ ጀምረውት የነበረው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ቀጣይ ሁለተኛ ክፍል እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን በእዚሁ “የክርስቲያን ጸሎት” በሚል አርዕስት ቅዱስነታቸው ባደረጉት አስተምህሮ “እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አምላኬ ነህ፤ አንተን ከልብ እሻለሁ፤ ውሃ በሌለበት፣ በደረቅና በተራቈተ ምድር፣ ነፍሴ አንተን ተጠማች፤ ሥጋዬም አንተን ናፈቀች” (መዝሙር 63፡ 1 5. 9) እግዚአብሔርን መፈለግ በሚለው ጭብጥ ዙሪያ ላይ ትክረቱን ያደርገ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን “የክርስቲያን ጸሎት በቅርበት፣ በመተማመን እና በእምነት የሚደረግ ጸሎት ነው” ማለታቸው ተገልጿል።
በዕለቱ የተነበበው የመጸሐፍ ቅዱስ ቃል
“እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አምላኬ ነህ፤ አንተን ከልብ እሻለሁ፤ ውሃ በሌለበት፣ በደረቅና በተራቈተ ምድር፣ ነፍሴ አንተን ተጠማች፤ ሥጋዬም አንተን ናፈቀች። ስለዚህ በመቅደስ ውስጥ አየሁህ፤ ኀይልህንና ክብርህንም ተመለከትሁ። ምሕረትህ ከሕይወት በልጣልና፤ ከንፈሮቼ ያመሰግኑሃል። እንግዲህ፣ በሕይወቴ ዘመን አመሰግንሃለሁ፤ በአንተም ስም እጆቼን አነሣለሁ። ነፍሴ አንተን የሙጥኝ አለች፤ቀኝ እጅህም ደግፋ ይዛኛለች” (መዝሙር 63፡ 1 5. 9) ።
የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።
ውድ ወንድሞች እና እህቶች እንደምን አረፈዳችሁ!
ባለፈው ሳምንት በጸሎት ዙሪያ ላይ የጀመርነውን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሁለተኛ ክፍል ዛሬ እንቀጥላለን። ጸሎት ለሁሉም የተሰጠ ነው ፣ ለሁሉም የሐይማኖት ተቋማት ተከታይ ሰዎች እና ምናልባትም ‘ምንም ዓይነት ሐይማኖት የለኝም’ በማለት ለሚናገሩ ሰዎች ሳይቀር ጸሎት አስፈላጊ ነው። ጸሎት በራሳችን ምስጢር ውስጥ ይወለዳል፣ መንፈሳዊ ጸሐፍት ብዙውን ጊዜ “ልብ” ብለው እንደ ሚጠሩት ጸሎት ከዚህያ ይወለዳል (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ 2562-2563)። ስለዚህ መጸለይ በውስጣችን ያለ ገለልተኛ የሆነ ነገር ወይም ጉዳይ አይደለም፣ እሱ በእኛ ውስጥ የሚገኝ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጥ ነገር አይደለም ፣ ነገር ግን ለእኛ በጣም ቅርብ የሆነ ምስጢር ነው። ይህ ምስጢር ነው የሚጸልየው። ስሜቶች ይፀልያሉ፣ ነገር ግን ጸሎት ስሜታዊ ብቻ ነው ሊባል አይችልም። እውቀት ይፀልያል ፣ ነገር ግን መጸለይ አዕምሯዊ ተግባር ብቻ አይደለም። ሰውነት ይጸልያል ፣ ነገር ግን አንድ በጣም ከባድ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ዋጋ ቢስ እንደ ሆነ ሆኖ ቢሰማውም እንኳን እግዚአብሔርን ማናገር ይችላል። ስለሆነም ሰው የሚጸልየው ጸሎት ሁሉ የሚወጣው “ከልብ” ነው።
ጸሎት ከራሳችን በላይ የሆነ እና በጉልህ ተነሳሽነት የሚደረግ ልመና ነው፣ በሰውነታችን ጥልቀት ውስጥ የተወለደ እና የሚደርስ አንድ ነገር ነው፣ ምክንያቱም አንድ የጥማት ስሜት ስለሚሰማን ነው። ያ ከችግር እና ከፍላጎት በላይ የሆነ ከፍተኛ ናፍቆት በራሱ አንድ የጸሎት መንገድ ነው። ጸሎት “እኔ” ከሚለው ፍላጎት የሚመነጭ ድምጽ ሲሆን “አንተ” ወደ ሚለው ድምፅ ይሄዳል። በ "እኔ" እና በ "አንተ" መካከል ያለው ግንኙነት የሒሳብ ቀመሮችን ተጠቅመን ማስላት አንችልም፤ እሱ የሰዎች ግንኙነትን የሚያመለክት ሲሆን “አንተን” የሚፈልገውን “እኔ” ለማግኘት ብዙ ጊዜ ወይም አንድ ጊዜ ብቅ ይላል።
ይልቁኑ የክርስቲያን ጸሎት ከመገለጥ ይመነጫል፣ “አንተ” የሚለው በስውር አልተመረጠም ፣ ነገር ግን ከእኛ ጋር ወደ ወዳጅነት መንፈስ ገብተዋል። ክርስትና የእግዚአብሔርን “መገለጥ” በቀጣይነት የሚያከብር ሃይማኖት ነው ፣ ማለትም የእርሱን መገለጽ የሚያምን እምነት ነው። በአመቱ ሥረዓተ አምልኮ ውስጥ የመጀመሪያዎቹ በዓላት የሚጀምሩት ምስጢር ያልሆነውን፣ ነገር ግን ለሰዎች ራሱን እንደ ጓደኛ አድርጎ ያቀረበውን የእግዚአብሔር ልጅ መወለዱን የሚያመለክት በዓል በማክበር ነው። በቤተልሔም በበረት ውስጥ በድህነት ፣ በሰባ ሰገል አሰላሳይነት፣ በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ በጥምቀት፣ በቃና ዘገሊላ በተደረገው የጋብቻ ስነ ስረዓት ላይ በተፈጸመው ተአምር እግዚአብሔር ክብሩን ገልጿል። ይህንን በተመለከተ የዮሐንስ ወንጌል ያቀረበውን ትንታኔ የደመደመው “ከቶውንም እግዚአብሔርን ያየ ማንም የለም፤ ነገር ግን በአብ እቅፍ ያለው አንድያ ልጁ የሆነው አምላክ እርሱ ገለጠው” (ዮሐንስ፡1 18) በሚል ውዳሴ ነበር። እግዚአብሔርን የገለጠልን ኢየሱስ ነበር።
የክርስቲያን ጸሎት በሰዎች ሕይወት ውስጥ አንዳች ፍርሃት እንዳይኖር የሚፈልገው በጣም ርኅሩህ ወደ ሆነው እግዚአብሔር ላይ ባዘነበለ መልኩ የሚደረግ ግንኙት ነው። ይህ የክርስቲያን ጸሎት የመጀመሪያ ባሕርይ ነው።
ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ግንኙነት የአገልጋይ እና የጌታ ዓይነት ግንኙት አይደለም። ክርስቲያኖች አምላካቸውን የሚጠሩ አባት በማለት በመተማመን መንፈስ ነው።
ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ግንኙነት የፊውዳል (የጌታ) እና የአገልጋይ ዓይነት ግንኙነት አይደለም። በእምነታችን ውርስ ውስጥ“መገዛት”፣ “ባርነት” ወይም “መንበርከክ” እነዚህን የመሳሰሉ አገላለጾች የሉም፣ ነገር ግን እንደ “ቃልኪዳን” ፣ “ወዳጅነት” ፣ “ተስፋ” ፣ “ሕብረት” ፣ “ቅርበት” ያሉ ቃላት ናቸው የእመነት ውርሶቻችን። ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ ባደርገው ረዥም የስንብት ንግግር “ከእንግዲህ አገልጋዮች አልላችሁም፤ አገልጋይ ጌታው የሚሠራውን አያውቅምና፤ ነገር ግን ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ስለ ገለጽሁላችሁ ወዳጆች ብያችኋለሁ። እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም፤ እንድት ሄዱና ፍሬ እንድታፈሩ ፍሬያችሁም እንዲኖር ሾምኋችሁ። ስለዚህም አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል” (ዮሐ 15፡15-16) በማለት ተናግሮ ነበር። ነገር ግን ይህ ባዶ የሆነ ማረጋገጫ አይደለም፣ ምክንያቱም “በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አብ ይሰጣችኋል” በማለት ማረጋገጫ ሰጥቶናልና።
እግዚአብሄር ጓደኛ፣ አጋር እና ሙሽራ ነው። "አባታችን" በሚለው ጸሎት ውስጥ ኢየሱስ ተከታታይነትያላቸውን ጥያቄዎችን እንድንጠይቅ አስተምሮናል፣ ስለዚህ በመተማመን ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ከእርሱ ጋር መመስረት ይቻላል። ለእግዚአብሔር ሁሉንም ዓይነት ጥያቄዎች ማቅረብ እንችላለን፣ ሁሉንም ነገር ማቅረብ እንችላለን፣ ሁሉንም ነገር እግዚአብሔርን መጠየቅ እንችላለን። ሁሉንም ነገር ማብራራት፣ ሁሉንም ነገር መናገር እንችላለን። ከእግዚአብሄር ጋር በሚኖረን ግንኙነት ስህተት እንሠራለን ቢባል ምንም ችግር የለውም-እኛ የእግዚአብሔር ጥሩ የሚባል ዓይነት ጓደኞች አይደለንም፣ አመስጋኝ ልጆች አይደለንም፣ ታማኝ ሙሽሮች አይደለንም። እርሱ ግን እኛን መውደዱን ይቀጥላል። በመጨረሻው እራት ላይ ኢየሱስ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው ደሜ የሚመሠረት አዲስ ኪዳን ነው” (ሉቃ 22፡20) በማለት በግልጽ ተናግሯል። በእዚያ መልክ ኢየሱስ በላይኛው ክፍል ውስጥ ሆኖ የመስቀልን ምስጢር ይገልጻል። እግዚአብሔር ታማኝ አጋር ነው - ሰዎች እርሱን መውደዳቸውን ቢያቆሙ እንኳን የእርሱ ፍቅር ግን ወደ ቀራንዮ የሚመራው መሆኑን ቢያውቅም እንኳን እኛን መውደዱን ይቀጥላል። እግዚአብሔር ሁል ጊዜ በልባችን በር አጠገብ ይገኛል፣ ልባችንን እስከምንከፍት ድረስ ይጠብቃል። እናም አንዳንድ ጊዜ ልባችንን ያንኳኳል፣ ነገር ግን ጣልቃ የሚገባ አምላክ አይደለም፣ እስክንከፍትለት ድረስ ይጠብቃል። እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ትዕግስት አባት ለልጁ ያለው ትዕግስት ዓይነት ነው፣ እርሱ እጅግ በጣም የሚወደን አባት ነው። አንድ አባት እና አንድ እናት ያላቸው ዓይነት ትዕግስት ነው። ሁሌም ልባችን ቅርብ ነው፣ እናም እርሱ ልባችንን የሚያንኳኳው በርኅራኄ እና በብዙ ፍቅር ነው።
ሁላችንም ወደ ቃልኪዳኑ ምስጢር ለመግባት እንችል ዘንድ እንደዚህ ሁነን ለመጸለይ እንሞክር። እራሳችንን በእግዚአብሔር ምሕረት እጆች ውስጥ በጸሎት ውስጥ ለማስቀመጥ ፣ የቅድስት ሥላሴ ሕይወት በሆነው በዚያ የደስታ ምስጢር ውስጥ እንደ ገባን ሆኖ እንዲሰማን፣ የማይገባን አገልጋዮች እንደ ሆንን ሆነን እንዲሰማን ልንጸልይ ይገባል። በጸሎታችን ውስጥ አንተ ፍቅር እንጂ ጥላቻን በፍጹም አታውቅም ብለን በመገረም እና በመደነቅ ወደ እግዚአብሔር አባት እንጸልይ። እርሱ የሚያውቀው ፍቅር ብቻ ነው፣ ይህን ለመሰለ የፍቅር አምላክ ነው እንግዲህ ጸሎታችንን የምናቀርበው። ይህ የእያንዳንዱ ክርስቲያናዊ ጸሎት ዋና አካል ወይም ማዕከል ነው። የፍቅር አምላክ፣ የሚጠብቀን እና አብሮን የሚጓዝ አባታችን ነው።