ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ቤርተለሜዎስ የሰላምታ መልዕክት ላኩ።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ሰኔ 22/2012 ዓ. ም. በዕለቱ በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ንባብ ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ካቀረቡ በኋላ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከነበሩት ምዕመናን ጋር ሆነው የብስራተ ግብርኤል ጸሎትን አድርሰዋል። በኋላም በአደባባዩ ለነበሩት ምዕመና በተለይም ቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ ባልደረባቸው ለሆኗቸው ለሮም ከተማ ነዋሪዎች በሙሉ ልባዊ ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። በቅዱሳኑ አማላጅነት የሮም ከተማ ነዋሪዎች የተሟላ ሰብዓዊ ክብር እንዲኖራቸው፣ ደስታ የሚገኝበትን የቅዱስ ወንጌል ምስክሮችች እንዲሆኑ በማለት ጸሎታቸውን የሚያቀርቡ መሆኑን ገልጸዋል።
የቫቲካን ዜና፤
በቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ ለመገኘት የቁስጥንጥንያው ፓትሪያርክ የብጹዕ ወቅዱስ ቤርተለሜዎስ የክርስቲያኖች ውህደት እንቅስቃሴ ልኡካን ዘንድሮ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በክብረ በዓሉ ላይ ሊገኙ አለመቻላቸውን ያሳታወቁት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “መንፈሳዊ ወንድሜ” ላሏቸው ለብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ቤርተለሜዎስ ሰላምታቸውን ልከውላቸዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም ከወረርሽኙ በኋላ በሁለቱ የሐይማኖት መሪዎች መካከል የሚደረግ ሐዋርያዊ ጉብኝቶ እንደሚጀምሩ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
ሰኔ 22/2012 ዓ. ም. የቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ ዓመታዊ በዓል በተከበረበት ዕለት በሮም ከተማ በጭካኔ የተገደሉትን ሰማዕታት ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የሮም ከተማ የበርካታ ክርስቲያን ወንድሞቻችን ደም የፈሰሰበት ሥፍራ መሆኑንም አስታውሰው ቀጥሎ በሚውለው ቀን የእነዚህ ሰማዕታት ወንድሞቻች መታሰቢያ ዕለት መሆኑን ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን፣ ከቨነዙዌላ፣ ከካናዳ፣ ከኮሎምቢያ እና ከሌሎች አካባቢዎች ለመጡት መንፈሳዊ ነጋዲያን በሙሉ ሰላምታቸውን አቅርበው፣ ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ እና ቅዱስ ጳውሎስ መካነ መቃብር ያደረጉት መንፈሳዊ ንግደት እምነታቸውን በማሳደግ ታማኝ የቅዱስ ወንጌል መስክሮች እንዲያደርጋቸው ከተመኙላቸው በኋላ፣ ምዕመናኑ በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው ጠይቀው መልካም ቀንን በመመኘት የዕለቱ ስብከታቸውን አጠቃለዋል።