ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከድሆች ጋር ሆነው የቀረበላቸውን ምግብ ሲመገቡ፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከድሆች ጋር ሆነው የቀረበላቸውን ምግብ ሲመገቡ፣ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ቤተክርስቲያን የድሆችን ጩኸት አድምጣ ቶሎ እጆቿን እንድትዘረጋ አሳሰቡ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ 4ኛውን ዓለም አቀፍ የድሆችን ቀን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት ቤተክርስቲያን የድሆችን የስቃይ ጩሄት አድምጣ የዕርዳታ እጆቿን በቀዳሚነት እንድትዘረጋ አደራ ብለዋል።  በዓለማችን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለውን የጨንቀት ጊዜን ያስታስወሱት ቅዱስነታቸው፣ ወረርሽኙን ለመከላከል፣ ፍርሃት ለማስወገድ፣ የእርዳታ እጃቸውን በመዘርጋት እና በማጽናናት፣ በመልካም ስነምግባር ያታገዘ የሕይወት ትርጉምን ያሳዩ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን አስታውሰዋል።

የቫቲካን ዜና፤

ችግር ውስጥ ለሚገኙ የእርዳታ እጃቸውን በመዘርጋት ከችግራቸው ለማውጣት የተዘጋጁ፣ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት በደረሱበት ሁሉ ያዘኑትን በማጽናናት፣ በተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች ውስጥ የሚገኙትን ለመርዳት ጥረት የሚያደርጉ፣ ምድራዊ ችግሮችን በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ዘንድ የሚያቀርቡ ሰዎች፣ ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን ምክንያት በማድረግ፣ ቅዳሜ ሰኔ 6/2012 ዓ. ም. ይፋ ባደረጉት መልዕክታቸው ገልጸዋል። “እጅህን ለድሆች ዘርጋ"(ሲራ. 7:32) የሚለውን ጥቅስ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ባስከተለው ችግር ምክንያት የሚቀርብ የዕርዳታ ጥያቄ ጋር በማገናኘት መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የግሎባላይዜሽን ሥርዓት ያፈራው የብቸኝነት እና የራስ ወዳድነት ሕይወት ብዙ ሰዎችን ከቸርነት እና ከልግስና ሕይወት በማራቅ የእርዳታ እጃቸውን እንዳይዘረጉ እንቅፋት የፈጠረባቸው መሆኑን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህ ጋር በማያያዝ ቤተክርስቲያን በስቃይ ውስጥ የሚገኙትን ሰዎች ጩሄት በማድመጥ፣ ለምስክርነት እና ለቸርነት የተጠራውን የእግዚአብሔር ሕዝብ በማስተባበር፣ ለማኅበራዊ ጥቅም ሲባል በችግር ውስጥ ለሚገኝ ማኅበረሰብ የእርዳታ እጇን እንድትዘረጋ አደራ ብለዋል።

ጸሎትን እና እርዳታን ማቅረብ የማይለያዩ ናቸው፤

ድህነትን ጨምሮ የተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች በብሉይ ኪዳን፣ በመጽሐፈ ሲራቅ ውስጥ መጠቀሱን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ይህ መጽሐፍ የኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት የሚገኝበት መሆኑን አስረድተዋል። የችግር እና የመከራ ጊዜ መታመኛችን እግዚአብሔር ነው ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኑነት ማጠናከር የምንችለው በጸሎት እንደሆነ አስረድተዋል። ከእግዚአብሔር ጋር የማያስቋርጥ ግንኙነት ካለ ሁለት የማይለያዩ ነገሮችን፣ እነርሱም ጸሎታችንን ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ማቅረብን እና በስቃይ ውስጥ ለሚገኙ ድሆች የእርዳታ እጃችንን መዘርጋት ናቸው ብለው፣ የእግዚአብሔር ባርኮት በእኛ ላይ መውረድ የሚችለው ለተቸገሩት ሰዎች ያለንን ርህራሄ እና ፍቅር በተግባር ስንገልጽ ነው ብለዋል።

ድሃን መርዳት ፈጣን ምላሽን ይጠይቃል፤

ድሆችን ለመርዳት የሚደረግ ምርጫ ጥንቃቄን ይጠይቃል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ድሆችን ለመርዳት በሚወጠኑ ሐዋርያዊ እና ማኅበራዊ እቅዶች ውስጥ ጊዜን መስጠት፣ ስለ ራስ ማሰብ እና ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጥ የለብንም ብለው የእግዚአብሔርን የጸጋ ስጦታ በሰብዓዊ ዝንባሌዎች መለወጥ እንደማያስፈልግ አሳስበዋል። ድሆችን በቸርነት ልብ ስንመለከታቸው፣ ችግራቸውን ስንጋራቸው ሕይወት ወደ መልካምነት እንደሚቀየር የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ መልካም ተግባራችን በመለኮታዊ ቸርነት በሚመራበት ጊዜ ትክክለኛ የሰው ልጅ ማንነት ይገለጣል ብለዋል። የበርካታ ድሆች ጩሄት በእግዚአብሔር ሕዝብ ዘንድ ተደማጭነት ሊኖረው ይገባል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ በየዕለቱ ለሚያሰሙት የስቃይ ድምጽ ፈጣን ምላሽ ሊሰጥ ይገባል ብለው፣ በሚደረግላቸው እርዳታ በመታገዝ የተመቻቸ ማኅበራዊ ሕይወት ተካፋዮች እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ትርጉም ያለው ተግባር፣

ማኅበራዊ ጥቅምን ማስገኘት ለአንድ ክርስቲያን የሕይወት ተልዕኮ መሆኑን ያስረዱት ቅዱስነታቸው፣ ይህ ተግባር ከክርስቲያናዊ ምስክነት አልፎ ወደ ጋራ ሕይወት እንደሚመራ ገልጸው፣ ማንም ሰው ሊያገኝ ከሚገባው ሰብዓዊ እና መሠረታዊ ፍላጎታች መታገድ የለበትም ብለዋል። የሕይወት ትርጉም ያላቸው አንዳንድ ተግባራት እየዘነጉ ይገኛሉ ያሉት ቅዱስነታቸው፣ በስቃይ ውስጥ የሚገኙትን መመልከት የሚችሉ ዓይኖች የእግዚአብሔርን አለኝታ የሚገነዘቡ ናቸው ብለው፣ መልካም ሥራዎቻችን ተስፋን የሚሰጡ መሆን አለባቸው ብለዋል።

በኮሮና ቫይረስ ውጊያ ወቅት ለመልካም ሥራ የተዘረጉ እጆች አሉ፤

የዓለማችን ሕዝብ እየኖረ የሚገኘውን ወቅታዊ ሕይወት ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በአሁኑ ወቅት የዓለማችን ሕዝብ ኮሮና ቫይረስ ያመጣውን የሕመም፣ የሞት እና የስጋት ሕይወት እየኖረ መሆኑን አስታውሰው፣ መልካም ሥራን እየፈጸሙ ከሕዝቦቻቸው ጋር ሆነው የማይመች የስጋት ሕይወት የሚኖሩ የህክምና ባለሞያዎች፣ የጤና ረዳቶች፣ በጎ ፈቃደኞች እና ካህናት መኖራቸውን አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም የእርዳታ እጅን ከመዘርጋት በተጨማሪ ሌሎች በርካታ የቸርነት ሥራዎች መሰራታቸውን መመስከር ይቻላል ብለው፣ በኮሮና ቫይረስ ወቅት በመልካም ተግባር ላይ የተሰማሩት ሰዎች ለወረርሽኙ ራሳቸውን በማጋለጥ ሕዝባቸውን እየረዱ እና እያጽናኑ የሚገኙ መሆናቸውን አስረድረዋል።

ድሆችን ለመርዳት የተዘረጉ እጆች፣

ሳይታሰብ እና ዝግጅት ሳይደረግበት በዓለማችን ሕዝብ ላይ የተደቀነውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ቀውስ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ድሆችን እና የቫይረሱ ተጠቂዎችን ለመርዳት የተዘረጋው የብዙዎች እጅ እውነተኛ ምስክርነትን የምንገልጽበት መሆኑን አስረድተው፣ የምህረት ሥራ መፈጸም በዕለታዊ ሕይወት መካከል ልንማረው የሚገባን ክርስትያናዊ ተግባር፣ ዕርዳታን በመፈለግ የመጀመሪያዎች መሆናችንን እንድናውቅ የሚያደርግ ተግባር ነው ብለዋል።

እርግጠኛነታችንን ችግር ገጥሞታል፣

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አቅማችን ውስን መሆኑን፣ ነጻነታችንን እንድንገፈፍ፣ የምንወዳቸውን የቤተሰብ አባላት በሞት እንድናጣቸው፣ ከሥራ እንድንወገድ በማድረግ በከፍተኛ ፍርሃት እና ችግር ውስጥ እንድንገባ ማድረጉን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ዓይኖቻችን አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ላይ እንዲያተኩሩ በማድረግ አዲስ የወንድማማችነት ሕይወት መመስረት የሚያስፈልግ መሆኑን አስረድተዋል። በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በኤኮኖሚ እና ፖለቲካ ዘርፎች ላይ የደረሰው ከባድ ቀውስ ለወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ያለንን ፍቅር ሊቀንስ እንደማይገባ ቅዱስነታቸው አሳስበዋል።

ለዕርዳታ ያለተዘረጉ እጆች፤

ለእርዳታ የተዘረጉ እጆች የመኖራቸውን ያህል በራስ ወዳድነት እና በስግብግብነት የታሰሩ እጆች መኖራቸውን የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ ሌሎች በችግር፣ በስቃይ እና በሞት መከካል በሚገኙበት ባሁኑ ወቅት ኪሳቸውን የሚያደልቡ፣ አገርን በድህነት ውስጥ የሚከቱ፣ በጦር መሣሪያ ሽያጭ ሃብት የሚያካብቱ መኖራቸውን አስታውሰዋል። በሰዎች መካከል ልዩነትን በመፍጠር፣ አንዱን ከሌላው በማበላለጥ የራስ ወዳድነት ስሜት እንዲፈጠር የሚያደርግ የግሎባላይዜሽን ሥርዓት መዘርጋት ገልጸው፣ ከዚህ አስከፊ የኑሮ ሥርዓት የጸዱ እጆች ለመላው ዓለም የፍትህ እና የሰላም መሣሪያዎች መሆናቸውን አስረድተዋል።

“ደስታን ከድሆች ጋር መጋራት የፍቅር ምንጭ ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ፍቅርን መጋራት ደስታን የሚያጎናጽፍ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የሕይወት ዘይቤን እንድናማር የሚያደረግ ነው ብለዋል። ቅዱስነታቸው መልዕክታቸውን ሲያጠቃልሉ፣ የድሆች እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የፍቅር እና የቸርነት ሥራቸውን በማበርከት ላይ ያሉትን እንድታግዛቸው ጸሎታቸውን አቅርበው፣ እጆቻችን ለቸርነት አገልግሎት የተዘረጉ እንዲሆኑ፣ በሕዝቦች መካከል ወንድማማችነት እንዲያድግ በማለት ዓለም አቀፍ የድሆችን ቀን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።        

15 June 2020, 14:36