ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ የዓለም ማሕበረሰብ ከሊባኖስ ጎን እንዲቆም ጥሪ አቀረቡ!
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በነሐሴ 03/2012 ዓ.ም በእለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው አስተንትኖ ካደረጉ በኋላ እንደ ተለመደው እና ዘወትር እሁድ እለት እንደሚያደርጉት የእግዚአብሔር መልአክ ማርያምን ያበሰረበትን የብስራተ ግብርኤል ጸሎት ከደገሙ በኋላ ለዓለም ያስተላለፉት ሳማንታዊ መልእክት በቅርቡ በሊባኖስ ዋና ከተማ በቤሩት በሚገኘው በአንድ ወደብ አቅራቢያ በተከሰተው ፍንዳታ በርካታ ሰዎች መሞታቸው እና መቁሰላቸው፣ እንዲሁም በከተማይቷ ላይ ከፍተኛ የሆነ ውድመት መድረሱን አስታውሰው በሊባኖስ የምትገኘው ቤተክርስቲያን ለሕዝቡ ያላትን ቅርበት አጠናክራ እንድትቀጥል ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው ጥሪ አቅርበዋል።
“በእነዚህ ቀናት ውስጥ ሀሳቤ ብዙ ጊዜ በሊባኖስ ሕዝቦች ዙሪያ ላይ እያጠነጠነ ይገኛል” በማለት መናገራቸው የተገለጸ ሲሆን በተመሳሳይ መልኩ ይህ አደጋ ከተከሰተ በኋላ በማግስቱ ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት መልእክት ከሁሉም ማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ሃይማኖታዊ ተቋማት ጋር ስለጉዳዩ እንደ ሚነጋገሩ ገልጸው ለተጎጂዎች እና ለቤተሰቦቻቸው መጸለይ እንደ ሚቀጥሉ መናገራቸው ይታወሳል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ተጎጂዎችን እና ቤተሰቦቻቸውን በማስታወስ ጸሎት ያደርጉ ሲሆን ሊባኖስ ይህን ቀውስ ለማሸነፍ ትችል ዘንድ እንዲረዷት ለሁሉም ማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ሃይማኖታዊ ተቋማት ጥሪ አቅርበዋል።
ባልፈው ማክሰኞች በቤሩት በሚገኘው በአንድ ወደብ አቅራቢያ ከፍተኛ ፍንዳታዎች መከሰታቸው የሚታወስ ሲሆን በአደጋው ከመቶ በላይ የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን ከ4000 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል፣ በከተማይቷ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱም ተገልጿል። ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው ማጠቃለያ ላይ ለተጎጂዎቹ እና ለቤተሰቦቻቸው መጸልያቸውን እንደ ሚቀጥሉ አረጋግጠው በሁሉም ማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ሃይማኖታዊ ተቋማት የችግሩ ሰለባ የሆኑ ሰዎችን ለመርዳት ቁርጠኛ ተነሳሽነት እንዲያሳዩ የጠየቁ ሲሆን ይህንን አሳዛኝ እና አስቸጋሪ ወቅት ለመቋቋም እና ለመሻገር የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የራሱን ሚና ይጫወት ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል።