ፈልግ

የጌታ ፊቱ እንደ ፀሓይ አበራ፤ ልብሱም እንደ ብርሃን አንጸባረቀ የጌታ ፊቱ እንደ ፀሓይ አበራ፤ ልብሱም እንደ ብርሃን አንጸባረቀ 

የጌታ ምስክሮች መሆን የምንችለው በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ስንታገዝ ብቻ ነው።

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ዛሬ ሐምሌ 30/2012 ዓ.ም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መልክ ወደ አስደናቂ ብርሃን የተለወጠበት ቀን በዓል በመከበር ላይ የገኛል። “ከስድስት ቀን በኋላ ኢየሱስ፣ ጴጥሮስንና ያዕቆብን እንዲሁም የያዕቆብን ወንድም ዮሐንስን ወደ አንድ ከፍ ያለ ተራራ ብቻቸውን ይዞአቸው ወጣ። በዚያም በፊታቸው መልኩ ተቀየረ፤ ፊቱ እንደ ፀሓይ አበራ፤ ልብሱም እንደ ብርሃን አንጸባረቀ። ወዲያውም ሙሴና ኤልያስ ከኢየሱስ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው” ከማቴዎስ ወንጌል (17፡1-9)። የጌታ ምስክሮች መሆን የምንችለው በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ስንታገዝ ብቻ ነው።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ!

የዛሬው ቅዱስ ወንጌል የኢየሱስ መልክ በቅጽበት መቀየርን የሚገልጽ ነው (ማቴ 17፡1-9)። ኢየሱስ ከእርሱ ጋር ጴጥሮስን ፣ ያዕቆብን እና ዮሐንስን ይዞ እግዚአብሔር ቅርባችን እንደ ሆነ መገለጫ ወደ ሆነው ወደ አንድ ከፍ ያለ ተራራ ላይ የወጣ ሲሆን የእርሱን ስቃይ፣ ሞት እና ከሙታን መነሳት ምስጢር ደቀመዛሙርቱ ሙሉ በሙሉ መረዳት ይችሉ ዘንድ አስቦ ያደርገው ተግባር ነው። በእርግጥ ኢየሱስ እሱን ስለሚጠብቀው ስቃይ፣ ሞት እና ትንሣኤ ለእነርሱ ይነግራቸው ጀመር፣ ነገር ግን ያንን ተስፋ ሊቀበሉ አልቻሉም። በዚህም ምክንያት ወደ ተራራው አናት ላይ ሲደርስ በሦስቱ ደቀመዛሙርቶቹ ፊት በጸሎት መትጋት በጀመረበት ወቅት የዛሬው ቅዱስ ወንጌል እንደሚነግረን መልኩን ተለውጦ “ፊቱ እንደ ፀሐይ አበራ፣ ልብሱም እንደ ብርሃን አንጸባራቂ ሆነ” (ማቴ 17፡2)።

በእዚህ ተአምራዊ እና አስደናቂ የኢየሱስ ፊት የተቀየረበት ሁኔታ ሦስቱ ደቀመዛሙርት አንጸባራቂ ክብር ባለው በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያምኑ ተጠርተዋል። ስለሆነም የሰው ልጅ አጠቃላይ ሁኔታ ገጽታውን ተገቢ በሆነ መልኩ እንደማይገልፅ በመገንዘብ ስለጌታቸው ያላቸው እውቀት ለየት ባለ ሁኔታ በእነሱ ፊት የኢየሱስ ሕይወት እና መለኮታዊ ገጽታ ተገለጠ።  እናም “ከሰማይ የምወደው ልጄ ይህ ነው […] እሱን ስሙት”(ማቴ 17; 5) የሚል ድምጽ ተሰማ። በእዚህ ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ነበር ሰማያዊው አባቱ ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀበት ቀን ደቀመዛሙርቱ እርሱን እንዲያዳምጡ እና እንዲከተሉት ስለእርሱ የመሰከረው እና እነርሱን የጋበዘው በእዚህ መልኩ ነው።

ከአሥራ ሁለቱ ደቀመዛሙርት ውስጥ ኢየሱስ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን መርጦ ወደ ተራራ የወጣበት አጋጣሚ  ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ስለ ኢየሱስ ተአምራዊ የሆነው መልክ መለወጥ የመመሥከር ልዩ መብት ሰጣቸው። ነገር ግን ለምንድነው እነዚህን ሦስቱን ደቀመዛሙርት ብቻ የመረጠው? ለምንድነው እጅግ ቅዱስ ስለሆኑ ነው? በፍጹም! ጴጥሮስ ኢየሱስ ሞት በተፈረደበት ወቅት ይክደዋል፣ ሁለቱ ወንድማማቾች ያዕቆብ እና ዮሐንስ በመንግሥቱ የመጀመሪያ ስፍራ እንዲሰጣቸው ተተይቁዋል (ማቴ 20፡ 20-23)።  ሆኖም ኢየሱስ  እንደኛ መስፈርት አይደለም ምርጫውን የሚያካሂደው፣ ነገር ግን በእርሱ የፍቅር እቅድ መሰረት ነው። የኢየሱስ ፍቅር ምንም ልኬት የለውም ፣ ፍቅር ነው ፣ እናም በእዚያ ፍቅር እቅድ ይመርጣል። ነፃ ፣ ቅድመ-ሁኔታ የሌለው፣ በነፃ ተነሳሽነት፣ በምላሹ ምንም ነገር የማይጠይቅ መለኮታዊ ፍቅር ነው። እናም እነዚያን ሦስቱን ደቀመዛሙርት እንደጠራ ፣ በተመሳሳይም ዛሬ ስለእርሱ እንዲመሰክሩ የተወሰኑ ሰዎችን ወደ እርሱ ይጠራል። የኢየሱስ ምስክር መሆን የማይገባን ስጦታ ነው፣ እኛ ብቁ እንዳልሆንን ይሰማናል፣ ነገር ግን በእዚህ ስሜት ተገፋፍተን አቅም የለንም በሚል ሰበብ ወደ ኋላ መመለስ አይገባንም።

እኛ ወደ ታቦር ተራራ አልሄድንም፣ እንደ ፀሐይ የሚያብራውን የኢየሱስ ፊት በዐይናችን አላየንም። ሆኖም  የመዳን ቃል ለእኛም ተሰጥቷል ፣ እምነትም ተሰጥቶናል፣ እናም እኛ በተለያዩ መንገዶች ከኢየሱስ ጋር የመገናኘት ደስታ አግኝተናል። እኛንም ቢሆን ኢየሱስ “ተነሡ አትፍሩ” (ማቴ 17፡7) ይለናል። በራስ ወዳድነት እና በስግብግብነት በተሞላው በዚህ ዓለም ውስጥ የእግዚአብሔር ብርሃን በዕለት ተዕለት ጉዳዮች ይበልጡኑ ያበራል። እኛ ብዙውን ጊዜ - ለመጸለይ ጊዜ የለኝም ፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ አገልግሎት ለማከናወን ፣ ለሌሎች ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት አልችልም… እንላለን። ነገር ግን የተቀበልነው ጥምቀት እና ማረጋገጫ እኛ በተቻለን አቅም ምስክርነት መስጠት እንደ ሚገባን መርሳት የለብንም። ነገር ግን ይህንን የምናደርገው በመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ታግዘን ነው።

በእዚህ ወቅት ራሳችንን ተገዢ ለማደርግ እና በለውጥ ጎዳና ላይ ለመጓዝ እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆነውን የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ መቀበል እንችል ዘንድ በአማላጅነቷ እንድትረዳን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልንማጸናት ይገባል።

ምንጭ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በየካቲት 29/2012 ዓ.ም ካደረጉት አስተንትኖ የተወሰደ።

06 August 2020, 09:54