ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ በአርመኒያ እና አዘርባጃን መካከል ሰላም እንዲወርድ ጸሎት አቀረቡ።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሁድ ጥቅምት 1/2013 ዓ. ም ያቀረቡትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ከፈጸሙ በኋላ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተገኙት ምዕመናን ጋር የብስራተ ገብርኤል ጸሎት አድርሰዋል። ቅዱስነታቸው ከጸሎቱ በኋላ ባሰሙት ንግግር፣ በአርመኒያ እና አዘርባጃን መካከል በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት በከፍተኛ መከራ ውስጥ የሚገኙትን እና በላቲን አሜርካ አህጉር ውስጥ በተነሳው የሰደድ እሳት አደጋ ምክንያት ችግር ውስጥ የሚገኙትን አስታውሰዋል።
የቫቲካን ዜና፤
በአርመኒያ እና አዘርባጃን መካከል በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት በሰዎች እና በንብረት ላይ በደረሰው አደጋ እጅግ ያዘኑት ቅዱስነታቸው፣ ለአካባቢው ነዋሪዎች ሰብዓዊ እርዳታን ማድረስ ይቻል ዘንድ የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ዘላቂ እንዲሆን ተመኝተዋል። በሁለቱም አገሮች መካከል ሰላም እንደሚወርድ ያላቸውን ተስፋ የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ በአገሮቹ መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት አስተማማኝ ሊሆን ይገባል ብለው፣ እስካሁን በጠፋው የሰው ሕይወት እና በነዋሪዎች ላይ በደረሰው ስቃይ፣ በመኖሪያ ቤቶች እና በአምልኮ ስፍራዎች ላይ በደረሰው ውድመት ምክንያት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸው፣ በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡት እና በችግር ውስጥ ለሚገኙት በሙሉ እንደሚጸልዩላቸው ገልጸው፣ ምዕመናንም በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው አደራ ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ምዕመናን በቤተክስቲያን ውስጥ ያላቸው የአገልግሎት ድርሻ፣ በተለይም የሴቶች የሃላፊነት ሚኖ ማደግ እንዳለበት አሳስበዋል። የሴቶችን የአገልግሎት ሚና ለማሳደግ በሚቻል ከፍተኛ የሃላፊነት ቦታ ሆነው እንዲያገልገሉ ዕድል መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል። ምዕመናን በምስጢረ ጥምቀት በተቀበሉት ጸጋ በመታገዝ፣ በተለይም ሴቶች በመንፈሳዊ ተቋማት ውስጥ ከፍተኛ ሃላፊነት ተቀብለው ሚናቸውን እንዲወጡት፣ ለቤተክርስቲያን እድገት እንቅፋት የሚሆኑ አካሄዶችን በመቃወም፣ የቅድስት ቤተክርስቲያን ገጽታን ለማሳደግ የተጠሩ መሆናቸውን አስታውሰዋል።
በጣሊያን ውስጥ አሲዚ ከተማ ቅዳሜ መስከረም 30/2013 ዓ. ም. ብጽዕናው የታወጀለትን ካርሎ አኩቲስ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ይህ የ15 ዓመት ዕድሜ አዳጊ ወጣት በልቡ ውስጥ ለቅዱስ ቁርባን ከፍተኛ ፍቅር ያደረበት መሆኑን ገልጸው፣ የምቾት ሕይወትን በመተው፣ ድሆችን እና አቅመ ደካሞችን በመውደድ ኢየሱስ ክርስቶስ ለማግኘት እና ለማወቅ መቻሉን አስረድተዋል። በዘመናችን ለብጹዕነት የበቃው የወጣት ካርሎ አኩቲስ ምስክርነት፣ በሕይወት መካከል እግዚአብሔርን በማስቀደም፣ የደኸዩትን እና የተገለሉ ወንድሞችን በማገልገል የሚገኘውን እውነተኛ ደስታ ለሌሎች ልጆችም በመግለጽ ምሳሌ መሆኑን ገልጸዋል።
ችግር እና መከራ ውስጥ ለሚገኙ ቤተክርስቲያናት እገዛን በማድረግ የሚታወቅ ፋውንዴሽን፣ መጭው እሑድ ጥቅምት 8/2013 ዓ. ም. የአንድነት እና የሰላም ቀን እንዲሆን ማወጁን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ “አንድ ሚሊዮን ሕጻናት የመቁጠሪያ ጸሎት ያቀርባሉ” የሚለውን የበዓሉን መሪ ቃል ገልጸው፣ የመላው ዓለም ሕጻናት በዕለቱ በሚያቅርቡት ጸሎት በዓለማችን የተስፋፋው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባስከተለው ቀውስ ምክንያት በችግር ውስጥ የሚገኙትን ሰዎች የሚያስታውሷቸው መሆኑን አስረድተዋል።