ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ "ካቶሊካዊ ምዕመናን በዚህ አስፈሪ ጊዜ የመቁጠሪያ ጸሎት ሊደግሙ ይገባል"
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ዛሬ መስከረም 27/2013 ዓ. ም. በየሳምንቱ ርቡዕ የሚያቀርቡትን ሳምንታዊ ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ የመስብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ለተሰበሰቡት ምዕመናን አቅርበዋል። የላቲን ሥርዓተ አምልኮን በሚከተሉ ካቶሊካዊ ምዕመናን ዘንድ ዛሬ የተከበረውን የመቁጠሪያ እመቤታችን ማርያም ክብረ በዓል በማስታወስ፣ ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ በሚቀርቡ ጸሎቶች ያላቸውን ጠቃሚ ሃሳብ አካፍለዋል። የኮቪድ-19ን ወረርሽኝ የመሳሰሉ በሽታዎች ዓለምን ስጋት ውስጥ በከተተበት አስፈሪ ጊዜ ምዕመናን የመቁጠሪያ ጸሎት እንዲደግሙ በማለት ዛሬ በቅዱስ ጳውሎስ የመሰብሰቢያ አዳራሽና በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያ ለሚከታተሉት ምዕመናን አሳስበዋል።
የቫቲካን ዜና፤
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እመቤታችን ማርያም ለአንዳንድ ምዕመናን በተገለጸችባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ምዕመናን የመቁጠሪያ ጸሎትን እንዲያዘወትሩ፣ በተለይም ዓለማችን በፍርሃት ውስጥ በሚገኝባቸው ጊዜያት በሙሉ ምዕመናን የመቁጠሪያ ጸሎት እንዲያቀርቡ በማለት መምከሯን ከፖላንድ ለመጡት ነጋዲያን አስታውሰዋል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዓለማችንን እያስጨነቀ ባለበት ባሁኑ ጊዜም ቢሆን መቁጠሪያን በእጃችን በመያዝ ጸሎታችንን ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ማቅረብ ያስፈልጋል ብለዋል። በዚህ ጸሎት አማካይነት ለራሳችን እና ሌሎች ሰዎች በሙሉ ማስታወስ ያስፈልጋል ብለዋል። ወደ እመቤታችን ዘንድ በምናቀርበው ጸሎት በኩል የምህረት አምላክ የሆነው እግዚአብሔር በዚህ አስፈሪ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጊዜ ለወንድሞቻችን እና እህቶቻችን፣ በተለይም ብቸኝነት ለሚሰማቸው እና ከለላ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች የእርዳታ እጃችንን መዘርጋት እንድንችል ይርዳን በማለት ለስፓኒሽ ቋንቋ ተናጋሪ ነጋዲያን ባቀረቡት ሰላምታ አስታውሰዋል።
የድነት ምስጢር፤
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደዚሁም ለአረብኛ ቋንቋ ተናጋሪ ነጋዲያንም ባቀረቡት ሰላምታቸው፣ መቁጠሪያን በእጃቸው ካልሆነም በኪሳቸው ይዘው መጓዝ እንደሚያስፈልግ ተናግረው፣ የመቁጠሪያ ጸሎት ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ የምናቀርበው ድንቅ ጸሎት መሆኑን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም የመቁጠሪያ ጸሎት የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ እና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሕይወት በየደረጃው የምናስተነትንበት፣ ከአደጋ ሁሉ የሚጋርደን፣ ከክፉ ፈተናም የሚሰውረን መሣሪያ ነው ብለዋል። የመቁጠሪያ ጸሎት ጥልቅ ማሰላሰል ጸሎት የሚደረግበት መንገድ መሆኑን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ በመቁጠሪያ ጸሎት አማካይነት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራዎችን ላይ ማስተንተን እንችላለን ብለዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም በመቁጠሪያ ጸሎት በኩል በየጊዜው እየጨመረ የሚመጣውን የእግዚአብሔር ፍቅር በዘላቂነት ማሰብ እንችላለን ብለዋል።