ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ወንድማማችነት እና የፍጥረታት እንክብካቤ የዕድገት እና የሰላም መሠረት ናቸው"

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሁድ መስከረም 24/2013 ዓ. ም ያቀረቡትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ከፈጸሙ በኋላ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተገኙት ምዕመናን ጋር የብስራተ ገብርኤል ጸሎት አድርሰው፣ አጭር ንግግር አድርገዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ ንግግራቸው፣ ቅዳሜ መስከረም 23/2013 ዓ. ም በጣሊያን ውስጥ አሲዚ ወደተባለች የቅዱስ ፍራንችስኮስ የትውልድ ከተማ ሐዋርያዊ ጉብኝት በማድረግ በመስከረም 24 ቀን ለሚከበረው የቅዱስ ፍራንችስኮስ ዓመታዊ ክብረ በዓል በተዘጋጀው የዋዜማ ዕለት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ስርዓት መምራታቸውን ገልጸው፣ በዚሁ ዕለትም “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የተሰኘውን እና በሕዝቦች መካከል ፍቅር እና ማኅበራዊ ወዳጅነት እንዲያድግ በስፋት የሚገልጽ አዲስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸውን በፊርማቸው በማጽደቅ ይፋ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል። “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የተሰኘ ሁለተኛውን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸውንም ጭምር ለማቅረብ መሠረት በመሆን በረዳቸው በቅዱስ ፍራንችስኮስ መካነ መቃብር ስፍራ ተገኝተው አዲሱን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸውን ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

የቫቲካን ዜና፤

አሁን የምንገኝበት ጊዜ አስቸጋሪ መሆኑን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ጊዜው ወዳጅነትን በማሳደግ እና ለፍጥረታት አስፈላጊውን ጥበቃ እና እንክብካቤን በመስጠት ለሕዝቦች ማኅበራዊ ዕድገት እና ሰላም በርትቶ መሥራትን እንደሚጠይቅ የቀድሞ ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳትም፣ ቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ፣ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ እና ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ማሳሰባቸውን አስታውሰዋል።  “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የሚለው አዲስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው፣ በቅድስት መንበር ዕለታዊ ጋዜጣ፣ “ሎዘርቫቶሬ ሮማኖ” ታትሞ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚገኙ ምዕመናን እና ከአደባባዩ ውጭ ለሚገኙት በሙሉ እንዲታደል መደረጉን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም በእያንዳንዱ የሐይማኖት ተቋም እና ሕዝቦች መካከል  ወንድማማችነት እንዲያድግ፣ ቤተክርስቲያን በምትጓዝበት የወንድማማችነት ጉዞ የቅዱስ ፍራንችስኮስ እገዛ እንዲታከልበት በማለት በጸሎታቸው ጠይቀዋል።

መስከረም 24/2013 ዓ. ም፣ በቤተክርትስቲያን ስለ ፍጥረታት እንድናስብ የተመደበው የአንድ ወር ጊዜ መጠናቀቁን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ከሌሎች ወንድም አብያተክርስቲያናት ጋር በመሆን የጋራ መኖሪያ ምድራችን ኢዮቤልዩ በዓል መከበሩን አስታውሰዋል። በመሆኑም በዕለቱ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ የተገኙትን፣ ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ የአየር ንብረት ለውጥ እንቅስቃሴ አባላትን፣ በ ”ውዳሴ ላንተ ይሁን” እንቅስቃሴዎች ውስጥ የሚገኙ አባላትን እና ሥነ-ምህዳርን በሚመለከቱ ሥራዎች ተሰማርተው ለሚገኙት በሙሉ ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። ሥነ-ምህዳርን አስመልክቶ በበርካታ አገሮች ውስጥ በተግባር በመተርጎም ላይ በሚገኙት ዕቅዶች የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

ቅዱስነታቸው በማስከተል፣ በባሕር ላይ የሚኖሩ ሰዎች ማኅበራዊ እና መንፈሳዊ ሕይወት ለማገዝ በሚል ዓላማ፣ የዛሬ መቶ ዓመት፣ በስኮትላንድ አገር የተመሰረተውን የባሕር ላይ ዕርዳታ አቅራቢ ድርጅት መኖሩን አስታውሰው በዚህ ድርጅት ውስጥ ሆነው የቤተክርስቲያንን አለኝታነት በመመስከር ላይ የሚገኙ ሐዋርያዊ አገልጋዮችን፣ መርከበኞችን፣ ዓሣ አጥማጆችን እና ቤተሰቦቻቸውን በሙሉ ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።            

ቅዱስነታቸው በማስከተልም ከሮም እና አካባቢዋ ለመጡት ምዕመናን፣ ከተለያዩ አገራት ለመጡት ነጋድያን፣ የቁምስና ማኅበራት አባላት እና ግለሰቦች ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። በተለይም በአደባባዩ ለተገኙት፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጠባቂ ፖሊሶች ወላጆች እና ቤተሰቦች ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። በቅርቡ አዲስ ምልምል ፖሊሶች ወደ በቫቲካን ውስጥ መመደባቸውን የገለጹት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እነዚህ “Swiss Guards” በመባል የሚታወቁ እና ለሁለት፣ ለሦስት፣ ለአራት ዓመታት እና ከዚያም በላይ ቤተክርስቲያንን እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ለማገልገል ወደ ቫቲካን የሚመጡ ወጣቶች በአገልግሎታቸው የተመሰገኑ መሆናቸውን ተናግረው አድናቆታቸውን ገልጸውላቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የዕለቱን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ከማጠቃለላቸው በፊት በሥፍራው ለተገኙት ምዕመናን በሙሉ ሐዋርያዊ ቡራኬአቸውን ሰጥተዋል።    

05 October 2020, 11:34