ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ወንድማማችነት ቀን ላይ እንደ ሚሳተፉ ተገለጸ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባሄ በዓለም አቀፍ ደረጃ በእየ አመቱ  ጥር 27 ቀን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ቀን እንዲሆን መወሰኑን ተከትሎ በመጪው ሐሙስ ጥር 04/2013 ዓ.ም ላይ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ቀን ስብሰባ በአውታረ መረብ እንደ ሚካሄድ ተገልጿል፣ ቅዱስነታቸውም በእዚህ ስብሰባ ላይ እንደ ሚገኙም ተገልጿል። በእዚህ ስብሰባ ላይ የግብፁ አል-አዝሃር ታላቁ ኢማም አህመድ አህመድ-ታይየብ እንደ ሚካፈሉም ተዘግቧል። ዝግጅቱ ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ በተገኙበት በአቡ ዳቢ እንደ ሚሰተናገድም ተገልጿል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ዋና ከተማ አቡ ዳቢ ውስጥ በሼክ ሙሐመድ ቢን ዛይድ በአውታረ መረብ እንዲካሄድ ባዘጋጁት የመጀመርያው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ወንድማማቸነት ቀን ላይ  ሐሙስ ጥር 27/2013 ዓ.ም በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚከበረው የሰብዓዊ ወንድማማችነት ቀን ላይ እንደ ሚሳተፉ የተገለጸ ሲሆን ታላቁ የአል አዛር ኢማም አህመድ አህመድ -ታይየብ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ እና እንዲሁም ሌሎች ብዙ ተጋባዢ እንግዶች እንደ ሚሳተፉም ተገልጿል።

በዚሁ አጋጣሚ የሰብዓዊ ወንድማማችነት አስመልክቶ የተዘጋጀ ሰነድ ይፋ እንዲሆን ከፍተኛ ተሳትፎ ያደረጉ ሰዎች የዛይድ ሽልማት በመባል የተሰየመው ሽልማት እንደ ሚሸለሙ ተገልጿል። ስብሰባው እና የሽልማት ሥነ ሥርዓቱ በሮም የሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ በቀጥታ መስመር በበርካታ ቋንቋዎች እንደ ሚተላለፍ የተገለጸ ሲሆን በቫቲካን ኒውስ ፣ የቅድስት መንበር የመልቲሚዲያ የመረጃ አውታረ መረብ እና በቫቲካን ብዙኃን መገናኛዎች እንደ ሚተላለፍ ተገልጿል።

ከሌላው ጋር በሚደረገው ማነኛውም ግንኙነት አንዳችን ለሌላው የሰላም ስጦታ እንዲገነባ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሰው ልጆች ሁሉ ጥሪ ሲያቀርቡ እንደ ነበረ የሚታወቅ ሲሆን ይህ አለም አቀፍ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ቀን አከባበር ለእዚህ ጥሪ ምላሽ ይሰጣል ሲሉ የኃይማኖት እና የሃይማኖት ጉዳዮች የጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የሆኑት ካርዲናል ሚጉዌል አንጌል አይዩሶ ጉይኮት  እ.ኤ.አ. በጥቅምት 2020 ዓ.ም ላይ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በሚል አርዕስት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ይፋ ያደረጉት ሐዋርያዊ መልእክት ጋር ይህ ግብዣ ይበልጥ ግልፅ እንደ ሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። እነዚህ ስብሰባዎች ቅዱስ አባታችን እንደጠየቁን እውነተኛ ማህበራዊ ወዳጅነትን የምናገኝበት መንገድ ናቸው ብለዋል።

ቀኑ በአጋጣሚ የተሰየመ አይደለም።  እ.ኤ.አ. የካቲት 4/2019 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ወደ የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ በተጓዙበት ወቅት ከታላቁ የአል-አዛር የግብፅ ኢማም አህመድ አል-ታይየብ ጋር በመሆን ለዓለም ሰላም እና አብሮ ለመኖር የሚያስችል ሰብዓዊ ወንድማማችነትን ሊያዳብር የሚችል ሰነድ መፈራረማቸው ይታወሳል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት እና ታላቁ ኢማም ይህንን ሰብዓዊ ወንድማማችነትን የተመለከተ ሰነድ ከማወጃቸው በፊት ቢያንስ ለግማሽ አመት ያህል ሰነዱን ሲያዘጋጁ መቆየታቸው የሚታወስ ነው።

ከጥቂት ወራቶች በኋላ ወንድማማችነትን ፣ አብሮነትን ፣ መከባበርን እና የጋራ መግባባትን ለማጎልበት የሰባአዊ ወንድማማችነት ሰነድ ምኞትን ወደ ዘላቂ ተሳትፎ እና ተጨባጭ ድርጊቶች ለመተርጎም የተቋቋመው የከፍተኛ የሰብዓዊነት ኮሚቴ መቋቋሙ ይታወሳል። የከፍተኛ ኮሚቴው በአብዳቢ በሰዓድት ደሴት ላይ የምኩራብ ፣ ቤተ ክርስቲያን እና መስጊድ ያለው አብርሀማዊ የቤተሰባዊ ቤት ለመገንባት አቅዷል። የዛይድ ሽልማት ለሰብዓዊ  ወንድማማችነት ሽልማት ብቁ የሚሆኑ እጩዎችን ለመቀበል እና ሥራቸው ለሰብዓዊ ወንድማማችነት የዕድሜ ልክ ቁርጠኝነትን የሚያሳዩ አሸናፊዎችን እንዲመርጥ ገለልተኛ የሆኑ ዳኞች መዘጋጀታቸው ተገልጿል። እ.አ.አ የ 2021ዓ.ም ሽልማት እ.አ.አ በካቲት 4/2021 ዓ.ም እንደ ሚሰጥ ተገልጿል።

እ.ኤ.አ. ታህሳስ 21/2020 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ እ.አ.አ የካቲት 4 ቀን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ቀን ሆኖ እንዲከበር በሙሉ ድምፅ ማጽደቁ ይታወሳል። የህግ ባለሙያ የሆኑት አቶ  ሞሐመድ መሐሙድ አብደል "በዚህ ወሳኝ የሰው ልጅ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ እኛ መንታ መንገድ ላይ እንገኛለን፣በአንድ በኩል የሰው ልጅ በሚደሰትበት ዓለም አቀፋዊ የወንድማማችነት እና በሌላ በኩል ደግሞ የሰዎችን ስቃይ እና እጦትን የሚጨምር ከባድ ሰቆቃ" ውስጥ እንደ ምንገኝ የሰላም ወንድማማችነት ከፍተኛ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ  እ.ኤ.አ. በጥቅምት 4/2020 ዓ.ም መግለጻቸው ይታወሳል።

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የኃይማኖታዊ ውይይት ጳጳሳዊ ምክር ቤት መሪ በመሆን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ቀንን ለማክበር ቅድስት መንበር አበረታተዋል። ቅዱስ አባታችን ለጥር ወር ይሆን ዘንድ በቪዲዮ ባቀረቡት የጸሎት ሐሳብ ላይ “ለሰው ልጆች አገልግሎት በሚውልበት” መልኩ ሁሉም የሐይማኖት ተቋማት አስፈላጊ በሆነው ማለትም እግዚአብሔርን በማምለክ እና ለባልነጀሮቻችን ፍቅር ትኩረት መስጠትን አስፈላጊነት አጉልተው መናገራቸው ይታወሳል። ርዕሰ-ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት ላይ “ወንድማማችነት እራሳችንን የሁሉም አባት ለሆነው ፈጣሪ እንድንከፍት እና ከሌላው ወንድም ፣ እህት ጋር ህይወትን እንድንካፈል ወይም እርስ በእርስ እንድንደጋገፍ ፣ እንድንፋቀር ፣ እንድናውቅ ያደርገናል” ማለታቸው ይታወሳል።

በተለያዩ የሐማኖት ተቋማት መካከል የሚደረጉትን ውይይቶች የሚከታተለው ጳጳሳዊ ምክር ቤት

የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እና የሌሎች እምነት ተከታዮች መካከል በሚኖራቸው ግንኙነት እና ውይይት ላይ ዓላማ በማድረግ የሃይማኖታዊ ጉዳዮች ጳጳሳዊ ምክር ቤት እ.ኤ.አ. በ 1964 ዓ.ም የተቋቋመ ጳጳሳዊ መክር ቤት ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በካርዲናል ሚጌል አንገል አዩሶ ጉይኮት ሊቀመንበርነት የሚመራ ምክር ቤት ነው።

ከዋና ዋና ሥራዎቹ መካከል በሃይማኖቶች መካከል በሚደረጉ ውይይቶች ዙሪያ ከጳጳሳት እና ከኤፒስቆፖሳት ጋር የሚካሄዱ ጉባሄዎችን ማስተባበር ሲሆን ከሌሎች ሃይማኖቶች መሪዎች ጋር ስብሰባዎችን ፣ ጉብኝቶችን እና ጉባሄዎችን ያካሂዳል። እናም በተለያዩ እምነቶች መካከል የመግባባት መንፈስ እንዲስፋፋ የተለያዩ ጠቃሚ መረጃዎችን በማዘጋጀት እና ለህትመት በማብቃት ተደራሽ እንዲሆኑ ያደርጋል።

የሰብዓዊ ወንድማማችነት ከፍተኛ ኮሚቴ

የከፍተኛ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ኮሚቴ ከፍተኛ የሰብዓዊ ወንድማማቸንት ሰነድ ተነሳስተው የተለያዩ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገኙ የሃይማኖት አባቶችን ፣ ምሁራንን እና የባህል መሪዎችን ያቀፈ ኮሚቴ ሲሆን የጋራ መግባባት እና የሰላም መልዕክቱን ለማዳረስ የሚሰራ ኮሚቴ ነው።

ዋናው ሥራቸው በሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ ምኞት መሠረት በትክክል ተግባራዊ ማድረግ እና የጋራ መከባበር እና በሰላም አብሮ የመኖር እሴቶችን ማስፋፋት ነው። የሰብዓዊ ወንድማማችነት ከፍተኛ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ የህግ ባለሙያ የሆኑት መሐመድ መሐሙድ አብደል ሰላም ናቸው።

01 February 2021, 12:36