ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ባደረጉበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ባደረጉበት ወቅት  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ጸሎት የቅድስት ስላሴን ምስጢር እንድንረዳ የሚያደረገን መንገድ ነው አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በእዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በየካቲት 24/2013 ዓ.ም ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከእዚህ ቀድም በጸሎት ዙሪያ ላይ ጀምረውት ከነበረው አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን  ጸሎት የቅድስት ስላሴን ምስጢር እንድንረዳ የሚያደረገን መንገድ ነው ማለታቸው ተገልጿል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በእለቱ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ከእዚህ ቀደም በጸሎት ዙሪያ ላይ የጀመርነውን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በመቀጠል  ዛሬ እና በሚቀጥለው ሳምንት ለእየሱስ ክርስቶስ ምስጋና ይግባውና ጸሎት ለቅድስት ስላሴ እና እንደ ባሕር ጥልቅ ለሆነው ለእግዚአብሔር ፍቅር መንገዱን እንደ ሚከፍት እንመለከታለን። መንግስተ ሰማያትን የከፈተልን እና ከእግዚአብሄር ጋር እንድንሆን ያደረገን ኢየሱስ ነው። ሐዋርያው ​​ዮሐንስ በወንጌሉ መግቢያ ላይ ባስቀመጠው መደምደሚያ ላይ ይህንኑ ያረጋግጣል፣ እንዲህም ይላል “ከቶውንም እግዚአብሔርን ያየ ማንም የለም፤ ነገር ግን በአብ እቅፍ ያለው አንድያ ልጁ የሆነው አምላክ እርሱ ገለጠው” (ዮሐ 1፡18)። በእውነት እንዴት መጸለይ እንዳለብን አናውቅም ነበር - ለእግዚአብሄር ምን ዓይነት ቃላት ፣ ምን ዓይነት ስሜቶች እና ቋንቋዎች እንደ ሚመጥኑት አናውቅም። ደቀ መዛሙርቱ በእነዚህ ባደረግናቸው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሂደት ውስጥ ብዙ ጊዜ ለምናስታውሰው ለመምህሩ ባቀረቡት ጥያቄ “ጌታ ሆይ ፣ መጸለይ አስተምረን” (ሉቃስ 11፡1) በማለት ሁሉንም የሰው ልጆች መሰናክሎች ፣ ተደጋጋሚ ሙከራዎች ፣ ብዙውን ጊዜ ስኬታማ ያልሆኑ ሙከራዎቻችን እውን እንዲሆኑ አድርጓል።

ሁሉም ጸሎቶች እኩል አይደሉም ፣ ሁሉም ምቹ አይደሉም ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ውድቅ የተደረጉ ብዙ ጸሎቶችን አሉታዊ ውጤት ራሱ ይመሰክራል። ምናልባት እግዚአብሔር አንዳንድ ጊዜ በጸሎታችን አይረካም ይሆናል፣ እናም እኛ ይህንን እንኳን አናውቅም። እግዚአብሔር የሚጸልዩትን ሰዎች እጅ ይመለከታል፣ እጆቻችን ንፁህ እንዲሆኑ ለማድረግ እነሱን ማጠብ አስፈላጊ አይደለም ፣ አንድ ነገር ካለ ፣ አንድ ሰው ከክፉ ድርጊቶች መታቀብ አለበት። ቅዱስ ፍራንቸስኮስ ለየት ባለ መንገድ ጸለየ “ማንም ሰው ስምህን ሊጠራ የተገባ አይደለም” በማለት ይጸልያል።

ነገር ግን ምናልባት ለጸሎታችን ድህነት በጣም እውቅና የተሰጠው ከሮማዊው መቶ አለቃ አንደበት የመጣው እና አንድ ቀን ኢየሱስ የታመመውን አገልጋይ እንዲፈውስለት ከለመነው ሰው ነው (ማቴ 8፡5-13)። እሱ ሙሉ በሙሉ ብቁ እንዳልሆነ ተሰምቶት ነበር ፣ እሱ አይሁዳዊ አልነበረም ፣ እሱ በሰራዊቱ ውስጥ ብቁ የሆነ መኮንን ነበር። ነገር ግን ለአገልጋዩ በጣም ያስብ ስለነበረ “ጌታ ሆይ ወደ ቤቴ እንድትገባ የሚገባኝ አይደለሁም፤ ነገር ግን ከዚሁ ሆነህ አንዲት ቃል ብቻ ተናገር፤ አገልጋዬም ይፈወሳል”(ማቴዎስ 8፡8)። እሱ በሁሉም የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓቶች ውስጥ የምንደጋግመውም ሐረግ ነው። ከእግዚአብሄር ጋር መወያየት ፀጋ ነው - እኛ ለእርሱ ብቁ አይደለንም ፣ የመጠየቅ መብት የለንም ፣ በእያንዳንዱ ቃል እና ሀሳብ ሁሉ “አንካሶች” ነን... ነገር ግን ኢየሱስ የሚከፈት በር ነው።

የሰው ልጅ ለምን በእግዚአብሔር ይወደዳል? ምንም ግልጽ ምክንያቶች የሉም ፣ ለመወደዳቸው ምንም ድርሻ አላበረከቱም… ስለሆነም ብዙ አፈ ታሪኮች ስለ ሰብዓዊ ጉዳዮች የሚጨነቅ አምላክ ሊኖር እንደማይችል ፣ በተቃራኒው እነሱ እንደ አስጨናቂ እና አሰልቺ እንደሆኑ ተደርገው እንደ ሚወሰዱ እርሱን ሙሉ በሙሉ ችላ እንደ ሚሉት ይጠቁማሉ። ለአሪስቶትል እንኳን እግዚአብሔር ስለራሱ ብቻ የሚያስብ አምላክ ነው። አንዳች ነገር ካለ እኛ አምላክን ለማሳመን የምንሞክር እና በአይኖቹ ዘንድ ደስ የሚለን እኛ ሰዎች ነን። ስለሆነም “የሃይማኖት” ግዴታ እርሱ እንዲሰማን ሁደቶችን በተደጋጋሚ ግድየለሽ በሚመስለው እና ዝም ባለው አምላክ ፊት እራሳችንን ለማዋሃድ ደጋግመን መቅረብ ነው።

ሰውን የሚወድ አምላክ ኢየሱስን ባናውቀው ኖሮ በእርሱ ለማመን ድፍረቱ ባልነበረንም ነበር። መሃሪ የሆነው አባት ምሳሌ ወይም የጠፋውን በግ ፍለጋ በሄደ እረኛ ውስጥ ተጽፎ የምናገኛው ቃል ለእኛ ትልቅ ትምህርት ነው (ሉቃ 15)። ኢየሱስን ባናገኝ ኖሮ እንደዚህ ያሉ ታሪኮችን ለመፀነስ ወይም ለመረዳት እንኳን ባልቻልን ነበር። ለሰዎች ለመሞት የተዘጋጀ አምላክ ምን ዓይነት አምላክ ነው?  እንዲወዱት ሳይጠይቁ በምላሹ  ግን እርሱ እነርሱን የሚወድ አምላክ ምን ዓይነት ታጋሽ አምላክ ነው? ርስቱን አስቀድሞ የጠየቀ እና ሁሉንም የሚገባውን ነገር ይዞ ከቤቱ ለቆ የሄደው ልጅ በሰራው ስህተት ተጸጽቶ ሲመለስ የተቀበለው እግዚአብሄር ምን ዓይነት አምላክ ነው? (ሉቃ. 15፡12-13)።

ስለዚህ ኢየሱስ በሕይወቱ ውስጥ የእግዚአብሔር አባትነት ምን ያህል እንደሆነ ይነግረናል። እንደ እርሱ ያለ አባት ማንም የለም። የቅድስት ሥላሴ ፍቅር የተሞላበትና በአብ፣ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ መካከል ያለው የተሳሰረ ቸርነት ጥልቀት ከሩቅ መገመት ለእኛ ከባድ ነው። የምስራቃዊያን አብያተ ክርስቲያናት ምስሎች  የአጠቃላይ አጽናፈ ሰማይ መነሻ እና ደስታ የሆነውን የዚህን ምስጢር ፍንጭ ይሰጡናል።

ከሁሉም በላይ ይህ መለኮታዊ ፍቅር በሰዎች መዳረሻዎች ላይ በማረፉ ይስፋፋል ብለን ማመን ከእኛ በላይ የሚሆን ጉዳይ ሲሆን እኛ በምድር ላይ አቻ የሌለው ፍቅር ተቀባዮች ነን። የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ይህንን በተመለከተ ሲናገር “የተቀደሰው የኢየሱስ ስብእና መንፈስ ቅዱስ አባታችን ወደ ሆነው ወደ እግዚአብሔር እንድንጸልይ የሚያስተምርበት መንገድ ነው” (ቁጥር 2664) ይለናል። እምነታችን ጸጋ ነው። እኛ ከፍ ያለ ጥሪን በእውነት ተስፋ ማድረግ አንችልም ነበር - የኢየሱስ ሰብዓዊነት የቅድስት ሥላሴን ሕይወት ለእኛ አመጣልን።

03 March 2021, 10:54