ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከዩክሬይን ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ዴኒስ ሽማይል ጋር በቫቲካን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከዩክሬይን ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ዴኒስ ሽማይል ጋር በቫቲካን  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የዩክሬይን ጠቅላይ ሚኒስትርን በቫቲካን ተቀብለው አነጋገሩ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዩክሬይኑ ጠቅላይ ሚንስትር ክቡር አቶ ዴኒስ ሽማይል ጋር ተገናኝተው ባደረጉት ውይይት ሁለቱም አገሮች በምሥራቅ ዩክሬይን ያለው የፖለቲካ ቀውስ በሰላማዊ መንገድ እንደሚፈታ ተስፋ መኑሩን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐሙስ መጋቢት 16/2013 ዓ. ም. የዩክሬይን ጠቅላይ ሚንስትር ክቡር አቶ ዴኒስ ሽማይልን በቫቲካን ውስጥ በግል ተቀብለው ማነጋገራቸውን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ገልጿል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጥለውም ከቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ፣ ከብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ጋር እና በቅድስት መንበር የመንግሥታት ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ ከሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍሉ አክሎ ገልጿል።

የዩክሬይኑ ጠቅላይ ሚንስትር ክቡር አቶ ዴኒስ ከቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ከብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ጋር ባደረጉት ውይይት ሁለቱም አገሮች በመካከላቸው ተጠብቆ በቆየው መልካም የጋራ ግንኙነት ላይ በማትኮር የተወያዩ ሲሆን፣ በተለይም በዩክሬይን በምትገኝ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሕይወት እና እንቅስቃሴ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ጭብጦች ላይ ተወያይተዋል። ከዚህም በተጨማሪ በዩክሬይን ስለሚታይ የጤና ቀውስ እና በምሥራቃዊው የአገሪቱ ክፍል የተከሰተውን የሰላም ማጣት በማስመልከት ተወያይተው፣ በቅርቡ የተደረሰው የትኩስ አቁም ስምምነት የተከሰተውን አመጽ በማስቆም ሰላማዊ መፍትሄን ለማግኘት ዕድል እንደሚከፍት ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

27 March 2021, 20:22