ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ሦስቱ ሐይማኖቶች በኢራቅ የሰላም ጎዳናን እንዲከተሉ አሳሰቡ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የኢራቅ ክፍለ ሀገር በሆነችው በኡር ከሦስቱ የአብርሃም መሠረት ካላቸው ሐይማኖቶች፥ ከክርስትና፣ ከሙስሊም እና ከአይሁድ እምነቶች ተወካዮች ጋር ተገናኝተው ሐዋርያዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። በኡር ግዛት ለሦስቱ ሐይማኖቶች ተወካዮች ባስተላለፉት ሐዋርያዊ መልዕክት፣ እግዚአብሔር ለአብርሃም በገባው ቃል ኪዳን መሠረት ከከዋክብት በታች በኢራቅ ውስጥ የሰላም ጎዳናን እንዲከተሉ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በኢራቅ ለሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ሁለተኛ ቀን በሆነው ቅዳሜ የካቲት 27/2013 ዓ. ም. የሦስቱ ሐይማኖቶች ማለትም የክርስትና፣ የእስልምና እና የአይሁድ እምነቶች መሠረት እና የከለዳውያን ምድር ወደ ሆነው የኡር ግዛት መጓዛቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው ወደ ኡር ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት፣ በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በሚገኙ የእምነት ተቋማት መካከል እንዲያድግ ጥረት በማድረግ ላይ ላሉት የጋራ ውይይቶች እና ወንድማማችነት ዓላማ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ነው ተብሏል። “ይህ የተቀደሰ ስፍራ፣ የእግዚአብሔር ሥራ ወደ ሆነው የእምነታችን መሠረት ተመልሰን እንድንመጣ አድርጎናል” በማለት ቅዱስነታቸው ለሦስቱ ሐይማኖቶች ተወካዮች ተናግረዋል።

ጉዞ ወደ ቤታችን

“የአብርሃም የትውልድ ስፍራ ወደ ሆነው ኡር ግዛት ተመልሰን መምጣታችን ወደ ቤታችን እንደመጣን ይቆጠራል” ብለዋል። ሦስቱ ሐይማኖቶች የተገናኙበት ኡር በአገሩ ባሕል መሠረት የአብርሃም ቤት የሚገኝበት ስፍራ መሆኑ ታውቋል። ኡር አብርሃም ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥሪ የተቀበለው፣ ለጉዞ የተነነሳው እና ታሪክ የተቀየረበት ቦታ መሆኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው “እኛም የዚህ ጥሪ እና ጉዞ ፍሬዎች ነን” ብለዋል። እግዚአብሔር አብርሃምን ከዋከብትን እንዲቆጥር ማዘዙን የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ የእርሱ ተከታዮች እንደ ሰማዩ ከዋከብት ቁጥራቸው የበዛ እንደሚሆን ቃል መግባቱን አስታውሰው፣ ይህን በማድረጉ “እኛን ልጆችህን ተመልክቶናል” በአብርሃም ምድር የተሰበሰቡት የሦስቱ ሐይማኖቶች ተወካዮች በምድር ላይ ስንጓዝ ቀና ብለን ሰማይን መመልከት ይኖርብናል ብለዋል።

“ወደ ሰማይ እንመለከታለን”

ዛሬ በሰማይ ላይ የምናያቸው ከዋከብት አብርሃም በጊዜው የተመለከታቸው ከዋከብት መሆናቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ እነዚህ ከዋከብት በኅብረት በሚሆኑበት ጊዜ የሌሊት ጨለማን ማብራት የሚችሉ መሆኑን ካስረዱ በኋላ ሰማዩም የአንድነት ምልክት መሆኑን አስረድተው፣ ዓይናችንን የእኛን ዕርዳታ ከሚፈልጉ ጎረቤቶቻችን፣ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ላይ ማንሳት የለብንም ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም የልዩ ልዩ እምነት ተከታዮች በመካከላቸው ባለው ፍቅር በመታገዝ ወንድማማችነትን ማሳደግ እንደሚገባ እና ዓይናችንን ወደ ሰማይ በማቅናት አምልኮአችንን ወደ እግዚአብሔር ማቅረብ ያስፈልጋል ብለዋል። እግዚአብሔርን ማምለክ እና ባልንጀራን መውደድ እውነተኛ የእምነት ምልክት መሆኑን ያስረዱት ቅዱስነታቸው፣ የእግዚአብሔርን መልክ በተሳሳተ መንገድ በሚያሳየን ዓለማችን፣ አማንያን በሙሉ የእግዚአብሔርን መልካምነት እና አባትነት በመካከላቸው ወንድማማችነትን በማሳየት መመስከር ይገባል ብለዋል።

የሽብርተኝነት እና የጥላቻ ደመናዎች

“እግዚአብሔር መሐሪ ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በእግዚአብሔር ላይ የምንፈጽመው ትልቁ በደል “ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን በመጥላት ስሙን ማጥፋት ነው” ብለዋል። ቅዱስነታቸው በሐይማኖት ላይ የሽብር ጥቃት ሲደርስ ምዕመናን በዝምታ መመልከት እንደሌለባቸው ገልጸው፣ አመጽ እና አክራሪነት የሐይማኖት ፍሬዎች አይደሉም ብለዋል። ጥቁር ደመና እና አሸባሪነት፣ ጦርነት እና አመጽ የኢራቅ ሕዝብን ማስጨነቁ፣ ሁሉም ጎሳ እና የሐይማኖት ማኅበረሰቦች በስቃይ ላይ መሆናቸውን ያመለክታል ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም በኢራቅ ውስጥ ከያዚዲ ጎሳ አባላት መካከል ብዙዎቹ መገደላቸውን፣ በባርነት መሸጣቸውን እና እምነታቸውን እንዲለውጡ መገደዳቸውን አስታውሰዋል። በኢራቅ ውስጥ ለስደት እና ለምርኮ የተዳረጉት በሙሉ ወደ መኖሪያ ስፍራቸው በሰላም እንዲመለሱ በማለት ጸሎት አቅርበዋል። በሁሉም አካባቢዎች የሕሊና እና የሐይማኖት ነጻነት እንዲከበር መጸለይ ያስፈልጋል በማለት መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ቅዱስነታቸው፣ እነዚህ መሠረታዊ መብቶች በመሆናቸው የተፈጠርንለትን ሰማይ እንድናሰላስለው ነጻነትን ይሰጡናል ብለዋል።

በጨለማ ውስጥ የሚያበሩ ኮከቦች

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው የእስላማዊ መንግሥት ታጣቂዎች በሰሜናዊው ኢራቅ ከፍተኛ ውድመት መፈጸሙን አስታውሰዋል። ውድመት ቢደርስባቸውም አንዳንድ ከዋከብት ብርሃን መስጠትን ያላቋረጡ መሆኑን የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ በጦርነት የወደሙ የአምልኮ ሥፍራዎችን፣ አብያተ ክርስቲያናትን እና መስጊዶችን መልሶ ለመገንባት የተወሰደው የጋራ ጥረት መልካም ምሳሌ ነው ብለዋል። የአምልኮ ሥፍራዎች ተመልሰው አገልግሎት ሲጀምሩ ወደ ቅዱሳት ሥፍራዎች መንፈሳዊ ጉዞን ወይም ንግደት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አደራ ብለዋል። የእምነታችን አባት የሆነው አብርሃም በልዩ ልዩ ሥፍራዎች ለእግዚአብሔር መንበረ ታቦቶችን ሰርቶ ለጸሎት በማዘጋጀት የአምልኮ ሥፍራን ማዝውጋጀቱን አስታውሰው፣ ይህ የጸሎት ሥፍራ ሰዎች የሚገናኙበት የሰላም ሥፍራ መሆኑን አስረድተዋል።

በምድር ላይ አብሮ መጓዝ

አብርሃም በዚህ ምድር ላይ ሲጓዝ ዓይኑን ቀና አድርጎ ወደ ሰማይ መመልከቱን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ አብርሃም ወደ ሰማይ መመልከቱ ምድራዊ ጉዞን በመልካም ሁኔታ እንዲጓዝ የረዳው መሆኑን አስረድተው፣ በጎዳናው መጓዝ በእርሱ ዘሮች በኩል ወደ እያንዳንዱ ጊዜ እና ቦታ የሚያደርስ መሆኑን አስረድተዋል። የአብርሃም ጉዞ መስዋዕትነትን የሚያስከፍል ቢሆንም፣ አንዳችን የሌላው ድጋፍ የሚያስፈልገን መሆኑን ገልጸዋል። በጉዞአችን መካከል እንቅፋት የሚሆኑትን ነገሮች ወደ ጎን አድርገን የእግዚአብሔርን ፍቅር በመልበስ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን መመልከት ያስፈልጋል ብለዋል።

የሰላም ጎዳና

"ሰማይ ላይ ያሉትን ከዋከብትን መመልከት ወደ ሰላም ጎዳና ይመራናል" በማለት ያስረዱት ቅዱስነታቸው፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መዛመት፣ የሌሎችን በተለይም በጣም የደከሙ ሰዎች ሥቃይ ችላ ማለት እንደማንችል አሳይቶናል ብለዋል። አክለውም ሰላም፣ ልዩነትን በማሸነፍ ኅብረትን ለመፍጠር ስለሚያግዝ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል። እውነተኛ ጠላታችን ጥላቻ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው፣ በእግዚአብሔር የሚታመን ሁሉ አይሸንፈም ካሉ በኋላ፣ የልባችንን በር ዘወትር የሚያንኳኳው ብቸኛው ጠላታችን ጥላቻ ነው ብለዋል።

ወደ ወንድማማችነት የሚወስዱ እርምጃዎች

ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሦስቱ እምነቶች፥ ለክርስትና፣ ለእስልምና እና ለአይሁድ እምነቶች ተከታዮች ባስተላለፉት መልዕክታቸው የጋራ አባታችን በሆነው አብርሃም መነሻችንን ለማግኘት የጦር መሣሪያዎቻችንን ወደ ሰላም መሣሪያዎች መለወጥ ያስፈልጋል ብለዋል። የሰው ሕይወት ክቡርነት የሚለካው በማንነቱ እንጂ ምን እንዳለው አለ መሆኑን ለዓለም መመስከር ይጠበቅብናል ብለዋል። እኛ የሦስቱም እምነቶች ተከታዮች በጋራ ቤታችን ውስጥ እንገኛለን ብለው፣ ወደ ሰላም ለመድረስ በምናደርገው እርምጃ እና በወንድማማችነት መንፈስ አብሮ በመሥራት መልካም የሆነውን ነገር እናገኛለን ብለዋል።  

06 March 2021, 22:16