የጋራ የመኖሪያ ቤታችን የሆነችውን ምድራችንን እንከባከብ!
“laudato si” በአማረኛው “ውዳሴ ለአንተ ይሁን” በሚል አርዕስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እ.አ.አ በግንቦት 24/2015 ዓ.ም ለንባብ ያበቁ ጳጳሳዊ መልእክት ይፋ የሆነበት 6ኛው ዓመት በመጪው ግንቦት 16/2013 ዓ.ም ታስቦ እንደ ሚውል ይታወቃል። በዚህ ጳጳሳዊ መልእክታቸው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ “የጋራ መኖሪያ ቤታችን የሆነችውን ምድራችንን እንከባከብ” በሚል ጭብጥ ዙሪያ ላይ የዛሬ 6 አመት ገደማ ያፋ ያደርጉት ሐዋርያዊ መልእክት ሲሆን በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ በዓለማችን ላይ የሚታየው የአየር ንብረት ለውጥ መንስሄ ምድራችንን ያለ አግባቡ በመበዝበዛችን፣ ከባቢ አየርን ሊበክሉ የሚችሉ ንጥረ ነገሮችን፣ ጋዞችን ወደ አከባቢ በመልቀቃችን በመሳሰሉ ጉዳዮች የተከሰተ እና የጋራ የመኖርያ ቤታችንን አደጋ ላይ የጣለ ክስተት በመሆኑ ክስተቱን ለመግታት ባለድርሻ አካላት የራስቸውን ሚና መጫወት ይገባቸዋል የሚል ጭብጥ ያለው ጳጳሳዊ መልእክት እንደ ሆነ ይታወሳል።
የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን
ለጋራ የመኖሪያ ቤታችን እንራራላት
ከኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር በጋር በመሆን፣ እንዲሁም ከሌሎች የክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናት እና የክርስቲያን ማሕበረሰቦች አጋርነት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለተፈጥሮ እንክብካቤ ይደረግ ዘንድ ዓለማቀፍ የጸሎት ቀን ታከብራለች”። በእዚህ እለት አማኝ ግለሰቦች እና የማኅበረሰብ ክፍሎች እያንዳንዳቸው ተፈጥሮን የመንከባከብ ጥሪያቸውን በድጋሚ የሚያድሱበትን አጋጣሚ በመጠቀም፣ የእዚህን ድንቅ የሆነ ተፈጥሮ ፈጣሪና እንድንከባከበው በአደራ ያስረከበንን እግዚኣብሔርን እንድናመሰግነው እና በቀጣይነትም ይህንን ተፈጥሮ ለመንከባከብ እንድንችል ይረዳን ዘንድ፣ እንዲሁም በምንኖርባት ዓለም ላይ ላደረስነው ውድመት ይቅርታን እንድንለምነው አጋጣሚውን የሚፈጥርልን እለት ነው።
አብያት ክርስቲያናት እና የክርስቲያን ማኅበረሰብ እንዲሁም የሌላ እምነት ተከታዮች ለገጸ-ምድራችን የወደ ፊት እጣ ፋንታ መጠበብ መጀመራቸው አበረታች ነገር ነው። በእርግጥ ባለፉት አስርተ-ዓመታት የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች እና ልዩ ልዩ ተቋማት በምድራችን ላይ እየተከሰተ የሚገኘውን ኋላፊነት የጎደለው ብዝበዛ ለብዙኋኑ አጋልጠው እንደ ነበረ ይታወሳል። በእዚህም ረገድ የቁስጥንጥንያው ፓትሪያርክ በርተሌሜዎስ ከእርሳቸው ቀደም ብለው የነበሩትን የፓትሪያርክ ዲሚትሪን ፈለግ በመከተል በተፈጥሮ ላይ እየደረሰ የሚገኘውን ሐሳሳቢ ውድመት ኋጥያት መሆኑን እና ይህም በአከባቢ ላይ እየደረሰ የሚገኘው ውድመት ሞራላዊ እና መንፈሳዊ ሥር መሰረቶችን እንደ ምያቃውስ መግለጻቸው ይታወቃል። ከተፈጥሮ ጋር ያለን ውህደት እዲጨምር እንዲሁም የአደጋው አሳሳቢነትን ለማጉላት በማሰብ በእዚህም ሳቢያ በዓለማችን በእዚሁ ጉዳይ ዙሪያ የተለያዩ ሥራዎች እንዲከናወኑ መንስሄ ከመሆኑም ባሻገር ፍታዊ የሆነ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም እዲኖር፣ ለድሆች ትኩረት እንዲሰጥ፣ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ኋላፊነት ተሰምቶት በተለይም ደግሞ የተለያዩ ሐይማኖት ተቋማት ተከታይ የሆነው የወጣቱ ትወልድ በአንድነት በእዚህ ጉዳይ ላይ እንዲረባረብ ጥሪ ያቀርባል። ክርስቲያኖች ይሁኑ ክርስቲያን ያልሆኑ በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎችም ጭምር የጋራ መጠልያ ቤታችን ለሆነችው ምድራችን ርኅራኄን እንዲያሳዩ እና የጋራ መኖሪያ ቤታችን የሆነችውን ምድራችንን መንከባከም ይኖርብናል።
1. ምድራችን በልቅሶ ላይ ናት
በእዚህ ምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ በመከራ ውስጥ የሚገኙ ድሆችን እና በአከባቢ ላይ እየደረሰ የሚገኘውን ውድመት በድጋሚ ማስታወስ እፈልጋለሁኝ። እግዚኣብሔር የተትረፈረፈ የአትክልት ሥፍራን ሰጠን ነገር ግን እኛ ወደ ባድማነት እና የትርኪምርኪ መጣያ፣ ወደ ተበከለ የቆሻሻ መጣያ ሥፍራነት ቀየርናት። በምድራችን ስነ-ምዕዳር እና የተመጋጋቢነት ሂደት ላይ ኋላፊነት በጎደለው መልኩ እና በእራስ ወዳድነት መንፈስ እየደረሰ የሚገኘውን ውድመት በግድየለሽነት ስሜት ወይም በዝምታ መመልከት አይኖርብንም። ምክንያቱም በሺዎች የሚቆጠሩ ዝርያዎች እየጠፉ በሚመጡበት ወቅት በመኖራቸው ምክንያት እነርሱን በማየት ለፈጣሪ የምንሰጠው ምስጋና እየቀነሰ ስለ ሚመጣ እና ይህንን የማድረግ መብትም ስለሌለን ጭምር ነው።
የሰው ልጆች በምያደርጉት እንቅስቃሴ ምክንያት የአለም ሙቀት መጨመሩ ይቀጥላል፣ ባሳለፍነው 2015 የነበረው የዓለማችን ሙቀት እስካሁን ከተመዘገቡት ሁሉ በጣም የላቀ ሲሆን በ2016ም ይህ ነገር በቀጣይነት እንደ ተከሰተ እሙን ነው። ይህ ጉዳይ በዓለማችን ድርቅ፣ ጎርፍ፣ እሳት እና ያልተለመደ የአየር ንብረት ለውጥ እዲኖር እያደረገ ይገኛል። የአለም የአየር ንብረት ለውጥ ለስደተኞች ፍሰት ቀውስ ከፍተኛ የሆነ ድርሻ አበርክቷል። በዓለም ውስጥ የሚኖሩ ድሆች ኋላፊነት በማይሰማቸው ሰዎች ምክንያት ድህነት ከደቀንባቸው መከራ ባሻገር በአለም የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከድጥ ወደ ማጡ እየወረዱ ይገኛሉ።
የተመጣጠን የስነ-ምዕዳር ሂደት እንደ ምያሳየው የሰው ልጆ ከተፈጥሮ ጋር ጥብቅ የሆነ ግንኙነት እንዳለው ነው። ስለእዚህም ተፈጥሮን መበደል ማለት የሰው ልጆችን መበደል ማለት ነው። በተመሳሳይ መልኩ እያንዳንዱ ፍጥረት የራሱ የሆነ ተፈጥሯዊ እሴቶች አሉት ይህም ሊከበር ይገባዋል። “ምድራችን እና ድሆች እያሰሙ የሚገኙትን ለቅሶ ችላ አንበል” ተገቢ እና ወቅታዊ ምላሽ እንዲገኝ የተቻለንን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል።
2. . . .እኛ ኋጥያትን ስለ ሠራን
እግዚአብሔር ለእኛ ምድርን የሰጠን ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ “እንድናለማት እና እንድንከባከባት ነው” (ዘፍ 2,15)። ከመጠን በላይ መጠቀም እና በጣም አንሰተኛ በሚባል መልኩ መንከባከብ ኋጥያት ነው።
አሁን በጋራ የመኖሪያ ቤታችን ላይ እየተከሰተ ካለው እውነታ በመነሳት እና በተለይም ደግሞ በምስጢረ ንስኋ አማካይነት “ውስጣዊ የሆነ ለውጥ ማምጣት ይኖርባናል። በእዚህ በተፈጥሮ ላይ ያደረስነውን ጥፋት ተገንዝበን ይቅርታን የምንጠይቅበት ሊሆን ይገባል። እንዲሁም ይህንን ሁኔታ ለመለወጥ ተጨባጭ እርምጃዎችን መውሰድ እንድያስችለን እስቲ ራሳችንን እንመልከት ምክንያቱም ለስነ-ምዕዳር የምናደርገው አስተዋጾን በግልጽ በማወቅ ለራሳችን፣ ለጎረቤቶቻችን፣ ለተፈጥሮ እና ለፈጣሪ ማሳየት የሚገባንን ኃላፊነት ማወቅ ያስፈልጋል።
3. ሕሊናችንን መመርመር እና መጸጸት
ለእዚህ ችግር ቀዳሚ የሆነ መፍትሄን ለማምጣት እንዲያስችለን በቅድሚያ “ማመስገን እንድንችል፣ ዓለማችን የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑዋን መረዳት እንድንችል እንዲሁም በጽሞና የእርሱን መልካምነትን በመላበስ በመልካም ሥራችን እራሳችንን መስዋዕት ማድረግ እንድንችል፣ በቅድሚያ እራስን መመርመር ያስፈልጋል። ጠንከር ያለ የሕሊና ምርመራ ካደረግን በኋላ በፈጣሪ፣ በፍጥረት፣ እንዲሁም በወንድም እና ሕህቶቻችን ላይ ባደረስነው ጥፋት ተጸጽተን ንስኋ መግባት ያስፈልጋል። “ንስኋን አስመልክቶ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እንዳስቀመጠው እውነት ነጻ ያወጣችኋል” “እግዚአብሔር ከኋጥያታችን በላይ ነው” ስለሆነም በተፈጥሮ ላይ ላደረስነው በደል ይቅር ይለናል”።
4. አካሄዳችንን ማስተካከል
ሕሊናን መመርመር፣መጸጸት እንዲሁም ኃጥያታችን በምሕረት ለተሞላው እግዚአብሔር መናዘዝ ወደ አንድ መሻሻል ማምጣት ወደ ምያስችለን አንድ ዓላማ ይመራናል። ይህም ዓላማ ተፈጥሮን ማክበር ወደ ምያስችለን ተጨባጭ ሐሳብ እና ተግባር ሊተረጎም ይገባል። ለምሳሌም “ፕላሲቲክ ነክ የሆኑ ነገሮችን መጠቀም አቁመን በምትኩም ወረቀት ነክ ነገሮችን መጠቀም፣ የውሃ አጠቃቀማችንን በቁጠባ ማድረግ፣ ህይወት ያላቸው ፍጥረቶች ሁሉ እንክብካቤ ማሳየት፣ በካይነት የሌላቸውን የመጓጓዣ አገልግሎቶችን መጠቀም፣ ዛፎችን መትከል. . . ወዘተ የመሳሰሉትን ተግባራት መፈጸም ያስፈጋል።
5. አዲስ የምሕረት ተግባር
“የምሕረትን ተግባር ከማከናወን በተሻለ ሁኔታ ከእግዚአብሔር ጋር የምያዋህደን የተሻለ ነገር የለም፣ ምክንያቱም እግዚአብሔር ኃጥያታችንን ይቅር የሚለን እና ፀጋውን የሚሰጠን እኛም ይህንን የምሕረት ተግባር በስሙ ማከናወን እንድንችል ነው”።
የክርስቲያን ሕይወት ባህል ሰባት አካላዊ እና መንፈሳዊ የምሕረት ተግባራትን መፈጸም እንዳለብን ያስተምረናል። “ብዙን ጊዜ የምሕረት ተግባራት ከግለሰቦች ጋር በተያያዘ ሁኔታ የሚፈጸሙ ለምሳሌ ለታመሙት ሆስፒታል፣ ለተራቡት ምግብ ቤት፣ ቤት ለሌላቸው መኖሪያ ቤት፣ ለተማሪዎች ትምህርት ቤት. . . ወዘተ ብቻ መስሎን ሊታይን ይችላል። ነገር ግን የምሕረት ተግባራትን በጥቅሉ ብንመለከት የምሕረት ተግባራት ዋናው ትኩረት የሰው ነፍስ እና ሰውን ያማከሉ ነገሮች ብቻ እንደ ሆኑ ያመለክታል።
ያለምንም ጥርጥር “የሰው ልጅ ሕይወት እና ይህንንም ያማከሉ ነገሮች ሁሉ” የጋራ መኖሪያችን የሆነውን ቤታችን እንድንከባከብ አደራ ይሉናል ማለት ነው። ስለ የጋራ መኖሪያ ቤታችን መንከባከብ የእዚህ የምሕረት ተግባራ አንደኛው አካል ነው።
6. በመጨረሻም እንጸልይ
ምንም እንኳን ኋጥያተኞች ብንሆንም እና በብዙ መከራዎች ውስጥ እያለፍን ቢሆንም ቅሉ ተስፋ መቁረጥ አይገባንም ምክንያቱም ፈጣሪያችን መቼም ቢሆን ብቻችንን አይተወንምና ነው። መቼም ቢሆን ፈጣሪያችን መሆኑን አያቆምም ምክንያቱም እርሱ ከምድራችን ጋር የተዋኋደ እና የእርሱ ፍቅር ሁል ጊዜም ቢሆን ወደ ፊት እንድንጓዝ የሚደግፈን በመሆኑ ጭምር ነው።
እንዲህ ብለን ልንጸልይ ይገባናል. . . “የድሆች አምላክ የሆንክ እግዚአብሔር ሆይ የተረሳችሁን እና የተጣለችሁን በአንተ ፊት ግን በጣም ውድ የሆነችውን ምድራችንን መታደግ እንድንችል እርዳን። የፍቅር አምላክ ሆይ በእዚህ ምድር ላይ ለሚገኙ ፍጥረቶች ሁሉ ያንተን ፍቅር ማሳየት የምንችልበትን ቦታ እና ምንገዱን አሳየን። የምሕረት አምላክ ሆይ ያንተን ምሕረት የተጎናጸፍነውን ምሕረት የጋራ የመኖሪያ ቤታችን በሆነችው ምድራችን ውስጥ መተግበር እንድንችል እርዳን። የእግዚአብሔር ሥም የተመሰገን ይሆን።