ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ኢየሱስን ማግኘት ማለት የልብ ሰላም ማግኘት መሆኑን ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ቅዱስነታቸው በዚህ ጸሎት ወቅት እንደተናገሩት፣ ከብርሃነ ትንሳኤው እሑድ ቀጥሎ የሚውለው ሰኞ ዕለት፣ የመልአክ ዕለት ተብሎ የሚጠራ መሆኑን ገልጸው፣ ይህ ዕለት የእግዚአብሔር መልአክ ወደ መቃብሩ ከመጡት ከሴቶች ጋር መገናኘቱን ያስታውሰናል ብለዋል። “እናንተስ አትፍሩ፤ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንደምትፈልጉ አውቃለሁ፣ እርሱ ከሞት እነሳለሁ ብሎ እንደተናገረው ተነስቶአልና በዚህ የለም” በማለት መልአኩ ለሴቶች መናገሩን አስታውሰው፣ “እርሱ ከሞት ተነስቶአልና በዚህ የለም” የሚለው መልዕክት ሰው ልያከናውን የማይችለው ነገር መከናወኑን ይገልጻል ብለዋል። ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብርብር የደረሱት ሴቶች ያገኙት ባዶ መቃብር፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሳኤ ሊያረጋግጥ እንደማይችል ገልጸው፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሳኤ ማረጋገጥ የሚቻለው፣ “እነሆ ትጸንሻለሽ፣ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፣ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ፤ እርሱ ታላቅ ይሆናል፣ የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል” በማለት ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያበሰራት፣ ቅዱስ መልአክ ብቻ ማረጋገጡን አስረድተዋል።
የእግዚአብሔር ጣልቃ ገብነት
ወንጌላዊው ማቴዎስ በብርሃነ ትንሳኤው ዕለት ጠዋት በማለዳ “ታላቅ የምድር መናወጥ መሆኑን እና የጌታ መልአክ ከሰማይ ወርዶ ድንጋዩን በማንከባለል በላዩ እንደተቀመጠ መናገሩን አስታውሰው፣ “የክፉ መንፈስ እና የሞት ምልክት የሆነው ትልቅ ድንጋይ ተንከባልሎ በመውደቅ የጌታ መልአክ የእግሩ መርገጫ እንዳደረገው ቅዱስነታቸው ገልጸው፣ በዚህም የጠላት ዕቅድ መክሸፉን አስረድተዋል። አክለውም ከመቃብሩ ፊት ለፊት በድንጋይ ላይ የተቀመጠው የመልአኩ ምስል የእግዚአብሔርን ድል አድራጊነት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የዚህ ዓለም አለቃ በነበረው ሰይጣን ላይ ድል መቀዳጀቱን እና ብርሃንም ጨለማን ማሸነፉን የሚገልጽ ግልጽ ማረጋገጫ ነው ብለዋል። የኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር ሊከፈት የቻለው በግዙፍ አካላዊ ኃይል ሳይሆን በእግዚአብሔር ኃይል መሆኑን አስረድተው፣ እንደ መብረቅ የበራው የመልአኩ ፊት፣ እንደ በረዶ የተነጣው የመልአኩ ልብስም ይህን እውነት ያረጋግጣል ብለው፣ እነዚህ የታሪክ ዝርዝሮች የመጨረሻው ዘመን ባለቤት የሆነውን የእግዚአብሔርን ጣልቃ ገብነት የሚያረጋግጡ ምልክቶች ናቸው በማለት አስረድተዋል።
ባለ ሁለት እጥፍ ምላሽ
“የእግዚአብሔርን ጣልቃ ገብነት በሁለት መንገዶች መመልከት እንችላለን” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የመጀመሪያው “በመሬት መንቀጥቀጥ በመናወጥ እንደ ሞተ ሰው በመውደቅ የእግዚአብሔርን ኃይል መጋፈጥ የማይችሉ የመቃብሩ ጠባቂዎች የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ በሞት ላይ ድል መቀዳጀቱን ያረጋገጡ መሆናቸው፣ ሁለተኛው መንገድ ደግሞ ኢየሱስን በመቃብር ውስጥ እንዳይፈልጉ የጌታ መልአክ የነገራቸው ሴቶች የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ማረጋገጫ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ከመላእክት የሚገኝ ትምህርት
“ከመልአኩ ቃላት ጠቃሚ እና ውድ ትምህርቶችን መማር እንችላለን” ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የተትረፈረፈ ሕይወትን የሚሰጥ እና ከሞት የተነሳውን ኢየሱስ መፈለግ ፈጽሞ ሊሰለቸን እንደማይገባ ገልጸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስን በሕይወታችን ማግኘት ማለት የልብ ዕረፍት እና ሰላም የሚሰጥ መሆኑን አስረድተዋል። ቅዱስ ማቴዎስ በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ላይ እንደጻፈው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር ፈጥነው የሄዱት ሴቶች የመቃብሩ ባዶ መሆን ሲመለከቱ እጅግ ያስደነገጣቸው ቢሆንም ጌታን በሕይወት በማግኘታቸው ታላቅ ደስታ የተሰማቸው መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስታውሰዋል። አክለውም፣ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ መታሰቢያ ወቅት ተመሳሳይ መንፈሳዊ ተሞክሮ እንዲኖረን የትንሳኤውን መልካም ዜና በልባችን ፣ በቤታችን እና በቤተሰቦቻችን ውስጥ መቀበል ያስፈልጋል በማለት ምኞታቸውን ገልጸዋል። በመጨረሻም፣ በብርሃነ ትንሳኤው ወቅት እንድንጸልይ የሚያነሳሳን ይህ እርግጠኝነት ስላለ ነው” ብለው፣ በሉቃ. ምዕ. 1፡28 ላይ እንደተጻፈው፣ ወደ ማርያም ዘንድ የተላከው ቅዱስ ገብርኤል “አንቺ ጸጋን የተመላሽ” በማለት የማርያምን ደስታ ሙሉ እንዳደረገው ሁሉ፣ ኢየሱስ ክርስቶስም የጠላትን ኃይል በፍቅር በማሸነፍ ያመጣው ደስታ የሁላችን ደስታ ሊሆን ይገባል በማለት ስብከታቸውን ደምድመዋል