ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የቫቲካን ሚዲያዎች አገልግሎታቸውን የበለጠ እንዲያሳድጉ አሳሰቡ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ግንቦት 16/2013 ዓ. ም ከቅድስት መንበር ብዙሃን መገናኛ ክፍሎች መካከል “ሎዘርቫቶሬ ሮማኖ” የተባለ ዕለታዊ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልን፣ የቫቲካን ሬዲዮን እና የቫቲካን ዜና ዝግጅት ክፍሎችን መጎብኘታቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በእነዚህ ክፍሎች ተሰማርተው ለሚሰሩ ጋዜጠኞች ባስተላለፉት መልዕክት፣ የቫቲካን ሚዲያዎች አገልግሎታቸውን የበለጠ በማሳደግ በመላው ዓለም የሚገኙ በርካታ አድማጮችን እና አንባቢያንን መድረስ እንደሚገባ አሳስበዋል። ከቅድስት መንበር ብዙሃን መገናኛዎች መካከል “ሎዘርቫቶሬ ሮማኖ” የተባለ የቅድስት መንበር ዕለታዊ ጋዜጣ የተመቋቋመበትን 160ኛ ዓመት ዘንድሮ እያከበረ ሲገኝ የቫቲካን ሬዲዮ አገልግሎትም የተቋቋመበትን 90ኛ ዓመቱን እያከበረ መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ፒዮስ 10ኛ ስም በሚጠራው ሕንጻ ውስጥ እና በሌሎች የቅድስት መንበር ማኅበራዊ መገናኛ ክፍሎች ለሚሰሩት የመገናኛ ባለሞያዎች ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት መልዕክት የቅድስት መንበር ብዙሃን መገናኛ አገልግሎቶች ተገልጋዩን ሕዝብ በስፋት እንዲደርስ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ ተቋሙ አገልግሎቱን በብቃት እና በነጻነት እንዲያቀርብ አደራ ብለዋል።

“ሎዘርቫቶሬ ሮማኖ” ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ስብሰባን መካፈላቸው

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማዕከሉ ውስጥ ባደረጉት የአንድ ሰዓት ጉብኝታቸው፣ የቅድስት መንበር ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ስብሰባን ለአጭር ቆይታ ከተካፈሉ በኋላ በማዕከሉ ውስጥ በሚገኝ በብሥራተ ገብርኤል ጸሎት ቤት በመገኘት ጸሎታቸውን አቅርበዋል። ቀጥለውም የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ ከሆኑት ከክቡር አቶ ፓውሎ ሩፊኒ እና በቫቲካን ሬዲዮ ውስጥ ከልዩ ልዩ ቋንቋዎች አገልግሎት ተጠሪዎች እና ከዜና ዝግጅት ክፍሉ ጋዜጠኞች ጋር ተገናኝተዋል።

ቅዱስነታቸው “ሎዘርቫቶሬ ሮማኖ” ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ሲጎበኙ
ቅዱስነታቸው “ሎዘርቫቶሬ ሮማኖ” ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ሲጎበኙ

እ. አ. አ ታኅሳስ 17/1936 ዓ. ም የታተመ ጋዜጣ

በቅድስት መንበር ጋዜጣ ክፍል እ. አ. አ ከ1978 ዓ. ም ጀምሮ የዝግጅት ክፍሉ ሃላፊ የሆኑት ክቡር አቶ ፔትሮ ዲ ዶሜኒካንቶኒዮ ለመጀመሪያ ጊዜ እ. አ. አ በ1861 ዓ. ም የታተመ የቅድስት መንበር ጋዜጣ ቅጂን ለዕይታ ካቀረቡላቸው በኋላ እ. አ. አ ታኅሳስ 17/1936 ዓ. ም ጋዜጣ ዕትም የመጀመሪያ ገጽ ቅጂን በስጦታ መልክ አቅርበውላቸዋል።  

ቅዱስነታቸው በብሥራተ ገብርኤል ጸሎት ቤት ውስጥ ጸሎት ማቅረባቸው

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሃያ ከሚሆኑ የዝግጅት ክፍል ሰራተኞች ጋር በመሆን በሕንጻው ውስጥ በሚገኝ ብሥራተ ገብርኤል ጸሎት ቤት በመገኘት ዘንድሮ በግንቦት ወር ለ55ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የማኅበራዊ መገናኛ ቀንን በማሰብ ጸሎታቸውን አቅርበዋል። በዮሐ. 1: 43 – 46 በተጻፈው ላይ ፊሊጶስ ናትናኤልን “መጥተህ እይ” ያለውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ማሕበራዊ ግንኙነት የሚፈጸመው ሰዎች እርስ በእርስ ሲገናኙ መሆኑን ገልጸው የማኅበራዊ መገናኛ ባለሞያዎች እግዚአብሔር እውነትን መናገር እንዲያስተምራቸው መለመን እንደሚገባ እና ለሌሎችም ያዩትን እና የሰሙትን እውነት መመስከር እንደሚገባ አሳስበዋል።

ቅዱስነታቸው በማዕከሉ በሚገኝ ብሥራተ ገብርኤል ጸሎት ቤት ጸሎታቸውን ሲያቀርቡ
ቅዱስነታቸው በማዕከሉ በሚገኝ ብሥራተ ገብርኤል ጸሎት ቤት ጸሎታቸውን ሲያቀርቡ

ከቫቲካን ሬዲዮ ሃላፊ ጋር መገናኘታቸው

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ በቫቲካን ሬዲዮ ዝግጅት ክፍል ተገኝተው በጣሊያንኛ ቋንቋ አገልግሎት በቀጥታ ስርጭት በኩል ባስተላለፉት መልዕክት፣ የቅድስት መንበር ማኅበራዊ መገናኛዎች ዋና ዓላማ የቫቲካን ሚዲያዎች አገልግሎታቸውን የበለጠ በማሳደግ በመላው ዓለም የሚገኙ በርካታ አድማጮችን እና አንባቢያንን መድረስ እንደሚገባ አሳስበዋል። ከዚህ ዓላማ ወደ ኋላ የሚያስቀር እንቅፋት እንዳይኖር አሳስበው፣ የኢየሱስ ክርስቶስን መልካም ዜና ወደ ዓለም ሁሉ ማድረስ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

የዘመናዊ የመገናኛ መሣሪያዎች ክፍል

ቅዱስነታቸው በሕንጻው ውስጥ በሚገኝ በቅዱስ ፍራንችስኮ ሳቬሪዮ ድምጽ መቅረጫ ክፍል የሚገኙ ዘመናዊ የመገናኛ መሣሪያዎችን እና የክፍሉ ሰራተኞችን ከጎበኟቸው በኋላ የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ ከሆኑት ክቡር አቶ ፓውሎ ሩፊኒ እና የዝግጅት ክፍሎች አስተባባሪ ከሆኑት ከክቡር አንድሬያ ቶርኔሊ ጋር ተገናኝተዋል። ክቡር አቶ ፓውሎ ሩፊኒ፣ በማርኮኒ አዳራሽ ከነበሩት ወደ 50 የሚጠጉ የልዩ ልዩ ቋንቋዎች ዝግጅቶት ክፍል ጋዜጠኞችን ከቅዱስነታቸው ጋር አስተዋውቀዋል።  

ለሚዲያ ባለሞያዎች ያቀረቡት መልዕክት

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በጉብኝታቸው ማጠቃለያ በቫቲካን ከቅድስት መንበር ማኅበራዊ መገናኛ ውስጥ በ “ሎዘርቫቶሬ ሮማኖ” ዕለታዊ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል፣ በቫቲካን ሬዲዮ እና በቫቲካን ዜና ዝግጅት ክፍሎች መካከል በሚታየው ኅብረት እና የሥራ ቅንጅት መደሰታቸውን ገልጸው፣ የሠራተኞቹ አንድነት እና የሥራ ጥራት የበለጠ እንዲያድግ እና መልካም ውጤት የሚገኝበት እንዲሆን አሳስበዋል።

ለቫቲካን ሚዲያ ባለሞያዎችን ብርታትን ሲስጡ
ለቫቲካን ሚዲያ ባለሞያዎችን ብርታትን ሲስጡ

በሥራ ውጤታማ መሆን የበለጠ ለማደግ ያግዛል

የሥራ ቦታ እጅግ ዘመናዊ ቢሆንም ፍሬው የሚለካው አገልግሎቱ በሚያመጣው ውጤት መሆኑን ያስረዱት ቅዱስነታቸው፣ ሥራው እና አገልግሎቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ መልካም ውጤት የሚያስመዘግብ ከሆነ የበለጠ ለማደግ ያግዛል ብለዋል። “ሥራችሁም ቀጣይነት ያለው ፈጠራ የታከለበት መሆን አለበት” በማለት በልዩ ልዩ የቅድስት መንበር ማኅበራዊ መገናኛ ክፍሎች ተሰማርተው ለሚሰሩ ጋዜጠኞች በሙሉ ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።              

25 May 2021, 16:13