ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ዕርዳታ ተማጽነዋል   ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ዕርዳታ ተማጽነዋል  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሁሉም ሰው የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ማግኘት እንዲችል ጸሎት አቀረቡ

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከምድራችን እንዲወገድ በቫቲካን ውስጥ የመቁጸሪያ ጸሎት መቅረቡ ተገልጿል። ቅዱስነታቸው በዚህ ሥነ-ሥርዓት ላይ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ባቀረቡት ጸሎት፣ በሰዎች መካከል የሚታየው ራስ ወዳድነት፣ ልዩነት፣ ጦርነት እና አመጽ እንዲወገድ እመቤታችን ታግዘን በማለት ለምነዋል። ከቅዱስነታቸው ጋር በመሆን ሕጻናት፣ ወላጅ ቤተሰብ እና ካህናት ጸሎታቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ በጸሎታቸውም ሕሙማንን፣ ሥራ አጦችን እና ሳይንሳዊ ምርምር የሚያካሂዱትን አስታውሰው በማኅበራዊ ሕይወትም መረጋጋት እንዲመጣ የእመቤታችንን እርዳታ ጠይቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቫቲካን የአትክልት ሥፍራ ባቀረቡት ጸሎት፣ እግዚአብሔር ዓለምን ከጥፋት እንዲጠብቅ፣ ሰዎች በመካከላቸው ልዩነት ሳይፈጥሩ ሁሉም ሰው ከወረርሽኙ የሚተርፍበት የመከላከያ መድኃኒቶች ቶሎ የሚገኝበት መንገድ እንዲመቻች የእግዚአብሔርን እና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዕርዳታ ለምነዋል። እንዲሁም በምድራችን ውስጥ ራስ ወዳድነት፣ ልዩነት፣ ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ችግሮች፣ አመጽ እና ጦርነት መኖሩን አስታውሰው፣ እነዚህ ችግሮች በሙሉ እንዲወገድ የእመቤታችንን ዕርዳታ ተማጽነዋል።

ዓለም አቀፍ የጸሎት መርሃ ግብሩ ተጠናቅቋል

በቫቲካን የአትክልት ሥፍራ የተካሄደው የመቁጸሪያ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት በግንቦት ወር ሲካሄድ የቆየው ጸሎት ማጠቃለያ መሆኑ ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የዓለማችን ካቶሊካዊ ምዕመናንን የሚያሳትፍ የጸሎት መርሃ ግብር ማስጀመራቸው ይታወሳል። በዚህ የጸሎት መርሃ ግብር በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚገኙ ምዕመናን በአካባቢያቸው በሚገኙ ትላልቅ ባዚሊካዎች ተገኝተው በጸሎት ሲተባበሩ መቆየታቸው ታውቋል። ከናይጄሪያ እስከ አርጄንቲና፣ ከፊሊፒን እስከ ቤልጄም፣ ከአውስትራሊያ እስከ ቦስኒያ ባሉት ባዚሊካዎች በተካሄደው የመቁጠሪያ ጸሎት ላይ በርካታ ምዕመናን የተካፈሉ ሲሆን፣ በጸሎታቸውም የጤና ባለሞያዎችን፣ ከሥራቸው የተገለሉትን፣ በሞት የተለዩ ቤተሰቦችን፣ ወዳጅ ዘመድን እና በሕክምና ላይ የሚገኙትን፣ በጦርነት ውስጥ የሚገኙ አገራትን፣ ለታመሙት መንፈሳዊ እና ቁሳዊ ዕርዳታን በማቅረብ ላይ የሚገኙ ገዳማዊያን፣ ገዳማዊያት እና ካኅናትን፣ ወጣቱን ትውልድ እና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተያዙትን በሙሉ አስታውሰዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመቁጠሪያ ጸሎት ላይ
ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመቁጠሪያ ጸሎት ላይ

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ መልዕክት

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በንግግራቸው፣ በያዝነው የግንቦት ወር ከበርካታ ምዕመናን ጋር በጸሎት መተባበራቸውን አስታውሰው፣ ወደ እመቤታችን ባቀረቡት ጸሎታቸው፣ በዓለማችን ውስጥ የሰውን ልጅ እያሰቃየ የሚገኝ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተወግዶ አስተማማኝ እና የተረጋጋ ማኅበራዊ ሕይወት እንዲመጣ ለምነዋል። በቫቲካን ውስጥ በተካሄደው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት የመላዋ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ድምጻቸውን በማስተባበር ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር፣ በሰው ልጅ ጫንቃ ላይ የወደቀው አስጨናቂው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንዲወገድ ጸሎታቸውን አቅርበዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ ኅዳር 27/2020 ዓ. ም ሰዎች ባልተገኙበት እና ጸጥታ በሰፈነበት ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ፣ ዓለማችን ውስጥ የገባው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንዲወገድ በማለት ጸሎት ማቅረባቸው ይታወሳል።

መላው ዓለም ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር ይጸልያል

በቫቲካን ውስጥ በሚገኝ የአትክልት ሥፍራ በተዘጋጀው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር ሕጻናት፣  ወላጅ ቤተሰቦች፣ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ክቡራን ካኅናት፣ ወጣቶች እና አዛውንት በጸሎት መተባበራቸው ታውቋል። በተጨማሪም በማኅበራዊ ሚዲያዎች በኩል በቀጥታ በተላለፈው ስርጭት አማካይነት የዓለም ምዕመናን መሳተፋቸው ታውቋል።

የእመቤታችን ማርያም ዕርዳታ

በቫቲካን ውስጥ በተካሄደው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ መንፈሳዊ ኡደትም የተደረገ ሲሆን፣ ኡደቱንም የመሩት በጀርመን የአውስቡርግ ጳጳስ፣ ብጹዕ አቡነ ቤርትራም ዮሐንስ ሜዬር መሆናቸው ታውቋል። ብጹዕ አቡነ ቤርትራም ዮሐንስ ከሀገረ ስብከታቸው ይዘው የመጡትን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መንፈሳዊ ምስል በጸሎቱ ወቅት በክብር ቦታ ላይ አስቀምጠውታል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመቁጠሪያ ጸሎት ላይ
ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመቁጠሪያ ጸሎት ላይ

ለ 30 የዓለም መቅደሶች ምስጋና ቀርቦላቸዋል           

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመቁጠሪያ ጸሎት ማጠቃለያ ላይ፣ ሥነ-ሥርዓቱን ያዘጋጁትን፣ በቅድስት መንበር የአዲስ ስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ምክር ቤት አስተባባሪ ለሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። ቅዱስነታቸው በተጨማሪም በግንቦት ወር በየአካባቢያቸው የተካሄደውን የመቁጠሪያ ጸሎትን ላስተባበሩት ለ30 የዓለም ካቶሊካዊ መቅደሶች ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። በእነዚህ መቅደሶች ውስጥ በቀረበው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ምዕመናን ድምጻቸውን በማስተባበር ጸሎታቸውን ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናት፣ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ማቅረባቸውን አስታውሰው፣ በሰዎች መካከል የሚታየው ራስ ወዳድነት፣ ልዩነት፣ ጦርነት እና አመጽ እንዲወገድ፣ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ እግዚአብሔር ዓለምን እንዲታደጋት፣ ሁሉም ሰው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባትን እንዲያገኝ በማለት የእግዚአብሔርን እና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ዕርዳታ ተማጽነዋል።    

01 June 2021, 16:00