ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለተደረገላቸው ጸሎት እና መልካም ምኞት ምስጋናቸውን አቀረቡ።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የሕክምና ዕርዳታን ለማግኘት ሆስፒታል በገቡበት ወቅት ሙሉ ጤናን ለተመኙላቸው የሃይማኖት ተቋማት እና የሀገር መሪዎች፣ ለከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት እና ምዕመናን በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በሆስፒታል በቆዩባቸው ጥቂት ቀናት ውስጥ የተቀበሏቸውን በርካታ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክቶችን አስታውሰው መልካምን ለተመኙላቸው በሙሉ ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ለቅዱስነታቸው የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን ከላኩት መካከል የአርመኒያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ካሬኪን ዳግማዊ ይገኙባቸዋል። ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ካሬኪን ዳግማዊ “በክርስቶስ የተወደድክ ወንድሜ” ባሉት መዕክታቸው በሐዋርያዊ የቤተክርስቲያን አገልግሎት ወቅት የእግዚአብሔርን ጥበቃ እና ምሕረት፣ ፍሬያማ ሐዋርያዊ አገልግሎትን የሚያቀርቡበት ረጅም ዕድሜን እግዚአብሔር እንዲሰጣቸው በጸሎታቸው የሚያስታውሷቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በርካታ የሀገራት እና የመንግሥታት መሪዎችም ለቅዱስነታቸው መልካም ምኞታቸውን የገለጹላቸው ሲሆን፣ በቻይና ሕዝባዊት ሪፓብሊክ የታይዋን ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ትሳይ ኢንግ-ዌን ሰኞ ሰኔ 28/2013 ዓ. ም. መልዕክት መላካቸው ታውቋል። በተመሳሳይ ዕለትም የፍልስጤም ነጻ አውጭ ድርጅት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ፕሬዚደንት ክቡር መሐመድ ሐባስ ለቅዱስነታቸው በላኩት መልዕክታቸው “በሕዝቦች መካከል ሰላም እና ፍቅር እንዲወርድ በሚያደርጉት ጥረት ወቅት እግዚአብሔር ጤናን እንዲሰጥ ጸሎታችንን በአንድነት እናቀርባለን” ብለዋል።

የቱርክ ሪፓብሊክ ፕሬዚደንትን ጣይብ ኤርዶጋንም በበኩላቸው በአገራቸው ሕዝብ ስም ባቀረቡት የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክታቸው ለቅዱስነታቸው ሙሉ ጤናን እና ለመላው ካቶሊካዊ ማኅበረሰብ መልካምን ተመኝተዋል። የቆጵሮስ ሪፓብሊክ መንግሥት ፕሬዚደንት ኒቆስ አናስታሲያደስም በበኩላቸው በእነዚህ የሕመም ሰዓታት ፈጣን ፈውስን ተመኝተው፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ሙሉ ጤናን እና ኃይልን ተመኝተውላቸዋል። አክለውም መንግሥታቸው እና መላው የቆጵሮስ ሕዝብ ለቅዱስነታቸው ሙሉ ጤናን የሚመኝላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የኩባ ሪፓብሊክ ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ሚገል ዲያዝ-ካኔል ቤርሙደዝም በበኩላቸው በራሳቸው፣ በሕዝባቸው እና በመንግሥታቸው ስም ለር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሙሉ ጤናን የተመኙላቸው ሲሆን፣ የቀድሞ የኩባ ፕሬዚደንት ራኡል ካስትሮ ሩዝ በአንድ ወቅት መልዕክታቸው “ህዝቦች ከመቼውም ጊዜ በላይ የቅዱስነታቸውን ጥበብ እና ሞራላዊ ሃላፊነትን ይመኛል” ማለታቸውን አስታውሰዋል። የፖላንድ ሪፓብሊክ ፕሬዚደንት ክቡር አቶ አንድሬይ ዱዳ በበኩላቸው ቅዱስነታቸው ሙሉ ጤናን አግኝተው ወደ መላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እና ወደ ቅድስት መንበር ሐዋርያዊ አገልግሎት እንዲመለሱ፣ በአስቸጋሪ ወቅት ለሚገኝ የዓለም ሕዝብ ቅዱስነታቸው የፍቅር እና የተስፋ አገልግሎት ማበርከት እንዲችሉ በማለት መልካሙን ተመኝተውላቸዋል።   

የላቲን አሜሪካ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ምክር ቤት ፕሬዚደንት ብጹዕ አቡነ ሄክቶር ሚገል ካብሬዮስ ቪዳርቴ ለር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በላኩት የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክታቸው በጤናቸው መሻሻል የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፣ ከመላው የላቲን አሜርካ ሕዝብ ጋር በጸሎት ከጎናቸው መሆናቸውን ገልጸው፣ ለቅዱስነታቸው የተደረገው የቀዶ ጥገና ሕክምና ዕርዳታ በስኬት መካሄዱ ያስደሰታቸው መሆኑንም ገልጸዋል። አክለውም  በዚህ የፈውስ ጊዜ በጸሎት የሚተባበሯቸው መሆኑን የላቲን አሜሪካ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ምክር ቤት ፕሬዚደንት ብጹዕ አቡነ ሄክቶር ሚገል ካብሬዮስ ቪዳርቴ ለቅዱስነታቸው ገልጸዋል።

የኒውዚላንድ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት እና የዊሊንግቴን ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ጆን አቼርልይ ጀው፣ የኒውዚላንድ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ምዕመናን ቅዱስነታቸውን በጸሎታቸው የሚያስታውሷቸው መሆኑን ገልጸው፣ ቅዱስነታቸው ባሁኑ ሰዓት በመልካም ሁኔታ በማገገም ላይ መሆናቸው ያስደሰታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በመጨረሻም የአይሁድ እምነት መምህር እና የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች የሆኑት ክቡር አቶ አርቱር ሽኔደር በበኩላቸው ለር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሙሉ ጤናን ተመኝተው፣ ቅዱስነታቸው ለመላው የሰው ልጅ የሚያሳዩትን ፍቅር እና ርህራሄ እንደሚቀጥሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። 

08 July 2021, 16:19