ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በግሪክ ባደረጉት ንግግር ይህን ቀደምት ሥልጣኔ መሰበር ማቆም ይኖርብናል አሉ!
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ከኅዳር 23 እስከ 27/2014 ዓ.ም ድረስ በቆጵሮስ እና በግሪክ በቅደም ተከተል ሐዋርያዊ ጉብኝት እያደረጉ እንደ ነበረ ቀደም ሲል መግለጻችን የሚታወስ ሲሆን በዚህም መሰረት ቅዱስነታቸው በቆጵሮስ ሲያደርጉ የነበረውን ሐዋርያዊ ጉብኝት አጠናቀው ቅዳሜ ሕዳር 25/2014 ዓ.ም እኩለ ቀን ላይ በግሪክ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት መጀመራቸው ይታወሳል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን
በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በሕዳር 26/2014 ዓ.ም እሁድ ቀን በግሪክ የምትገኘውን የሌስቦስ ደሴት ውስጥ የሚገኘውን የሚቲሊንን የስደተኞች መቀበያ እና መለያ ማእከል ጎብኝተዋል። እዚያ በነበሩበት ወቅት የስደተኞችን ምስክርነት ሰምተዋል፣ እናም በስፍራው ለነበሩት ስደተኞች ይህ የስደተኞች ጉዳይ ሁሉንም የሚመለከት ሰብአዊ ቀውስ እንደሆነ ተናግሯል።
ከአምስት ዓመታት በፊት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ወደ ሌስቦስ ደሴት ሂደው እንደ ነበረ የሚታወቅ ሲሆን በእዚያ ሥፍራ በተገኙበት ወቅት የስደተኞችን ችግር ራሳቸው በስፍራው ተገኝተው መታዘባቸው ይታወሳል። እሁድ ዕለት በግሪክ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በዚህ ደሴት በሚቲሊን ካምፕ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች “ፊታችሁን እና ዓይኖቻችሁን ለማየት እዚህ መጥቻለሁ” በማለት ቅዱስነታቸው ተናግረዋል፣ ስደተኞችም ቅዱስነታቸውን በደስታ ተቀብለዋል።
የቁስጥንጥኒያው የግሪክ ኦርቶዶክስ የሁደት ፓትሪያርክ የሆኑት ብጽዕ ፓትርያርክ በርተሎሜዎስ ከተናገሩት በመጥቀስ “እናንተን የሚፈሯችሁ ሰዎች ሁሉ ዓይኖቻችሁን ለማየር ይፈራሉ… ስደት የመካከለኛው ምሥራቅና የሰሜን አፍሪካ፣ የአውሮፓና የግሪክ ጉዳይ ብቻ እንዳልሆነ ረስተውታል። ነገር ግን ጉዳዩ የዓለም ጉዳይ ነው” በማለት ተናግረዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ንግግራቸውን ሲቀጥሉ አክለው እንደ ገለጹት ከሆነ ስደት “ሁሉንም ሰው የሚመለከት ሰብዓዊ ቀውስ” መሆኑን አስምረውበታል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝን እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እርምጃዎች እየተወሰዱ ባሉበት ወቅት “ከስደት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች የተረሱ ይመስላሉ” በማለት አክለው ገልጸዋል።
ከታሪክ የምንማረው ትምህርት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የግሪክ ደሴት በሆነችው በሌስቦስ ተገኝተው ለስደተኞች ባደረጉት ንግግር ቅዱስነታቸው እንደገለጹት “እራሳችንን መጠበቅ ብቻ በቂ ነው ብሎ ማሰብ ቅዠት ነው” ብለዋል ። "ለወደፊቱ ከሌሎች ጋር የበለጠ እና የተሻለ ግንኙነት እናደርጋለን። ወደ በጎ ነገር ለማሸጋገር፣ የሚያስፈልገው አንድ መስመር ሳይሆን ሰፊ ፖሊሲዎች አስፈላጊ ናቸው” ያሉ ሲሆን ታሪክ “ይህን ትምህርት ያስተምረናል፣ እኛ ግን ከዚህ ለመማር ዝግጁ አይደለንም” በማለት አክለው ገልጸዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በንግግራቸው ወቅት እያንዳንዱን ወንድና ሴት “ሽባ የሚያደርገውን ፍርሃት፣ ገዳይ የሆነ ግድዬሌሽነትን፣ በዳርቻው ላይ ያሉትን በሞት የሚቀጣውን ንቀትን እንዲያሸንፉ” ጥሪ አቅርበዋል።
ትንሽ ለውጥ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ከአምስት ዓመታት በፊት በግሪክ የምትገኘውን የሌስቦስ ደሴት መጎብኘታቸው የሚታወስ ሲሆን ቅዱስነታቸው ከጉብኝታቸው በኋላ በስደት ጉዳይ ላይ ምንም ለውጥ እንዳልመጣ አመልክተዋል። ነገር ግን ስደተኞችን በመቀበልና በማዋሃድ ስራ ላይ የተሰማሩትን ድርጅቶች እና ግለሰቦችን ጭምር አወድሰዋል።
“ይህች አገር እንደሌሎች ሁሉ በችግር ላይ የምትገኝ መሆኗን እና በአውሮፓም ጭምር የሚገኙ አገራት ችግሩ የማይመለከታቸው አድረገው ቆጥረው ማሰባቸው በራሱ እጅግ የሚያሳዝን ክስተት ነው ብለዋል።
"ለጋራ ጥቅም መዋል የሚገባቸው የጋራ ገንዘቦች ግድግዳዎችን እና አጥሮችን ለመገንባት እንደ መፍትሄ የሚውሉ ሀሳቦችን መስማት በጣም አሳዛኝ ነው" በማለት አክለው ገለጸዋል።
"ነገር ግን ግድግዳዎችን እና አጥሮችን ወደ ላይ በመገንባት ችግሮች አይፈቱም፣ አብሮ ለመኖር የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወን እና ሌሎችን ለመንከባከብ በመተባበር እጅግ ያስፈልጋል” ብለዋል።
ችግሮችን መፍታት
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “በሃሳቦች ላይ ከመጨቃጨቅ ይልቅ የአብዛኛውን የሰው ልጅ ችግር ለመፍታት እይታዎቻችንን እና ምልከታዎቻችንን ማስፋቱ ይሻላል፣ እነሱ ባልፈጠሯቸው የሰብአዊ አደጋዎች ሰለባ የሆኑ ሰዎችን መንከባከቡ እጅግ ይጠቅማል፣ በረጅም የብዝበዛ ታሪክ ውስጥ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሰው በመሰደዳቸው የተነሳ እኛ በዚህ ጉዳይ መጸጸት ይኖርብናል” ብለዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ንግግራቸውን ሲቀጥሉ “የሌሎችን ፍርሃት በማዳበር የሕዝብን አስተያየት ማነሳሳት ቀላል ነው” ያሉ ሲሆን ሆኖም ስለ ድሆች ብዝበዛ፣ አልፎ አልፎ ስለተጠቀሱት፣ ነገር ግን ብዙውን ጊዜ ጥሩ ገንዘብ ስለሚያስገኙ ጦርነቶች… ስለ ድብቅ ጦርነቶች በእኩልነት መናገር ለምን ያቅተናል። የጦር መሳሪያ ዝውውርን በመቃወም የጦር መሳሪያ ንግድ መስፋፋትን የሚደግፉ ተግባራትን መዋጋት ያስፈልጋል” ብለዋል።
የችግሮችን ሁሉ መንስኤዎች በጥንቃቄ መዋጋት እንደሚገባ የገለጹት ቅዱስነታቸው የችግሮችን ሁሉ "መዘዝ የሚከፍሉ እና ለፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ የሚውሉ ድሆች እንደ ሆኑ” ቅዱስነታቸው አጽኖት ሰጥተው የተናገሩ ሲሆን አክለውም “ችግሮችን ለማስወገድ የአደጋ ጊዜ ሁኔታዎችን ለመፍታት ከሚደርገው ጥረት የበለጠ ማድረግ ይገባል፣ የተቀናጁ እርምጃዎችን ማድረግ ያስፈልጋል” ብለዋል።
ስልጣኔን ከመሰበር እንታደግ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ "ባሕራችን ወደ ባድማ የሞት ባሕር እንዲለወጥ መፍቀድ የለብንም” ሲሉ የተናገሩ ሲሆን “ይህ የመገናኛ ሥፍራ ወይም ቦታ የግጭት ትያትር የሚከናወንበት ቦታ እንዲሆን አንፍቀድ። ይህ ማስታወሻ የሆነ ባህር ወደ ተረሳ ባህርነት እንዲቀየር አንፍቀድ። እባካችሁ ይህንን የስልጣኔ መሰበር እናስቁም” ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው ንግግራቸውን ደምድመዋል።