ር. ሊ. ጳ ቤኔዲክቶስ 15ኛ፣ የሰዎችን ከንቱ እልቂት የተቃወሙበት መልዕክት ተዘከረ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
እ. አ. አ. ነሐሴ 1 ቀን 1917 ዓ. ም. የመሳፍንት ቤተሰብ ወገን የሆነው ፍራንቸስኮ ፈርዲናንዶ የተባለ ግለሰብ በሳራዬቮ መገደሉን ተከትሎ ከሦስት ዓመታት በፊት በተጀመረው ታላቁ ጦርነት ምክንያት ዓለም መበታተኗ ይታወሳል። የአውሮፓ አህጉርን ክፉኛ የጎዳውን ጦርነት በዓይናቸው የተመለከቱት እና በጊዜው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ መሪ የነበሩት ር. ሊ. ጳ ቤኔዲክቶስ 15ኛ ለእገራት መሪዎች በላኩት መልዕክታቸው፣ የሕዝቦችን ሕይወት በከንቱ እያጠፋ የሚገኝ አስከፊ ጦርነት በፍጥነት እንዲቆም በማለት መጠየቃቸው ይታወሳል።
በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ጦርነት እየተካሄደ ባለበት በዚህ ጊዜም እ. አ. አ በ1917 ዓ. ም. ር. ሊ. ጳ ቤዴዲክቶስ 15ኛ ያቀረቡት ወሳኝ ጥያቄ በድጋሚ እየቀረበ ይገኛል። "እጅግ የከበረ እና በማበብ ላይ የሚገኝ አውሮፓ፣ በዓለም አቀፋዊ ክፋት ተውጦ ወደ ጥፋት እየሮጠ ይገኛል" በማለት የገለጹት ር. ሊ. ጳ ቤኔዲክቶስ 15ኛ፣ መንግሥታት “ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ጥሪ አቅርበዋል። ወደ ስምምነት ደርሰው ሰላምን ለማምጣት "መሠረታዊ ነጥቡ ስነ ምግባርን የተከተለ የሕግ የበላይነት በጦር መሣሪያ ቁሳዊ ኃይል ላይ የበላይነትን መቀዳጀት አለበት" በማለት ገልጸዋል። ር. ሊ. ጳጳሳቱ መልዕክታቸውን በመቀጠል "ስለዚህ በግዛቶች ውስጥ ሕዝባዊ ጸጥታን ለመጠበቅ አስፈላጊ እና በቂ በሆነ መጠን የጦር መሣሪያዎችን ቅነሳ ደንቦች በማጽደቅ ዋስትናን የሚሰጥ ፍትሃዊ ስምምነት" ላይ እንዲደረስ አሳስበዋል።
“እኛ ለተለየ የፖለቲካ ዓላማ ወይም የተፋላሚ ወገኖች አስተያየት ወይም ፍላጎት ለመደገፍ አይደለም። ነገር ግን የምእመናን የጋራ አባት የሆነውን የእግዚአብሔር ከፍተኛ ግዴታን በመገንዘብ ብቻ ተነሳስተን፣ ሐዋርያዊ አገልግሎታችንን የሚፈልጉ የእግዚአብሔር ልጆችን ለማጽናናት ድምጻችንን ከፍ በማድረግ ጩኸታችንን እናሰማለን። የሰላም እና የአገራትን እጣ ፈንታ በእጃቸው ለያዙት በሙሉ ጥሪያችንን እናድሳለን።” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈው ነበር።
ለሰላም መቃተት
በጣሊያን ውስጥ ጄኖቫ ከተማ እ. አ. አ. ኅዳር 21/1854 ዓ. ም. የተወለዱት የቀድሞ ር. ሊ. ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 15ኛ መልዕክት ዛሬ በተለያዩ ግጭቶች ውስጥ የሚገኙ አገራት መሪዎች ስልጣናቸውን በመጠቀም ጦርነት እንዲያስቆሙ በማለት የሚከተለውን መልዕክት በማስተላለፍ ይደመደማል፥
“ጸሎታችንን አድምጡ፣ በመለኮታዊው ቤዛ እና በሰላም አለቃ ስም የምናቀርብላችሁን አባታዊ ግብዣን ተቀበሉ፤በእግዚአብሔር እና በሰው ፊት ያላችሁትን ከባድ ሃላፊነት አስቡ፣ በውሳኔዎቻችሁ ላይ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ቤተሰቦች ሰላም እና ደስታ፣ የበርካታ ወጣቶች ሕይወት፣ የሕዝቦችን ደስታ በመገንዘብ፣ አገርን የመምራት ሙሉ ግዴታን አስታውሱ፤ ከቅዱስ ፈቃዱ ጋር በሚስማማ መልኩ የፖለቲካ ውሳኔዎቻችሁን እንድታስተካክሉ እግዚአብሔር ይርዳችሁ፤ የአሁኑ ዘመን ሕዝብ ምስጋና የሚገባችሁ፣ በመጪው ትውልድ መካከል የሰላም ፈጣሪነት መልካም ስም ይኑራችሁ። እኛም ሰላምን ከሚናፍቁ ታማኝ የእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር በጸሎት እና በንስሓ አንድ ላይ በመሆን፣ ብርሃንንና ምክርን ከመንፈስ ቅዱስ ዘንድ እንለምንላችኋለን።” በማለት፣ የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቤኔዲክቶስ 15ኛ ለአገራት መሪዎች የላኩትን የሰላም ጥሪ መልዕክታቸውን ደምድመዋል።