ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የተራበን ማብላት ሰብዓዊ ክብሩን መጠበቅ እንደሆነ አስታወቁ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ቅዱስነታቸው በዚህ መልዕክታቸው፣ ዓለማችን እርስ በርስ በተገናኙ በርካታ ቀውሶች ውስጥ በሚገኝበት በዚህ ወቅት፣ የኢየሱስ ክርስቶስን መልካም ዜና ለማያምኑትም ጭምር በማድረስ፣ ለተራቡት ሁሉ ምግብ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን የሰውን ልጅ ማዕከላዊነት በመገንዘብ እና በማረጋገጥ ራስን ለሌሎች አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል። ይህ ሊሆን የሚችለው በሕዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት በማሳደግ፣ ወደ ወንድማማችነት እና አብሮነት ስንመለስ ብቻ ነው ብለዋል።
ምግብ፣ የእግዚአብሔር ቸርነት መገለጫ እና የምድር ፍሬ ነው!
“በዓለማችን ያለውን ረሃብ እና ድህነት ለማጥፋት በየዕለቱ የሚተጉ ናቸው” በማለት ስበሰባውን በአውታረ መረብ አማካይነት በመካፈል ላይ ለሚገኙት በሙሉ ቅዱስነታቸው ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። “ምግብ ለሰው ልጅ ሕይወት አስፈላጊ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ በአቅርቦቱ ላይ መሳተፍ እንደ ሌሎች ሸቀጦች አቅርቦት መቆጠር የለበትም ብለው፣ ምግብ የእግዚአብሔርን ቸርነት የሚገልጽ እና የምድር ፍሬዎች ተጨባጭ ምልክት መሆኑን አስረድተዋል። አባቶች ለእንጀራ ያላቸውን አክብሮት የተናገሩት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ወደ ገበታ ሲያቀርቡት ስመው እንደሚያቀርቡት እና ፍርፋሪ እንኳን በመሬት ወድቆ እንዲባክን የማይፈቅዱ መሆኑን አስታውሰዋል። ኢየሱስ ክርስቶስም በቅዱስ ቁርባን ለዓለም ሕይወት የሚሆን ሕያው እንጀራ ማዘጋጀቱን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። ለምግብ ክብር መስጠት የሚቻለው፣ በሰው ሕይወትም የላቀ ቦታ መስጠት የሚቻለው፣ ተደራሽነቱን የማረጋገጥ እና የማስተዳደር ሃላፊነት በመውሰድ፣ የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን ስነገነዘብ እንደሆነ አስረድተዋል።
በሰው ልጅ እና ፍላጎቱ ላይ ማትኮር ያስፈልጋል
ጥቅምት 6/2015 ዓ. ም. በተከበረው የዓለም የምግብ ቀን፣ በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት የላኩትን መልዕክት ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ የመጀመሪያ ትኩረታችን በሰው ልጅ ላይ መሆን እንዳለበት በማሳሰብ፣ እውነተኛ ፍላጎቶቹን በተለይም ለኑሮው መሠረታዊ የሆኑ ነገሮችን ማግኘት የማይችሉ ሰዎችን ግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚገባ አሳስበዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ መልዕክታቸውን ሲያጠቃልሉ፣ የስብሰባ ፍሬዎች ለሰው ልጅ መልካም የወደፊት ዕድል የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ተነሳሽነት ያላቸው እንዲሆኑ በማለት ለእግዚአብሔር በአደራ ሰጥተዋል።
ለተሻለ የምግብ አቅርቦት ወጣቶችን ማበረታታት
ድህነትን እና ረሃብን በመቀነስ ረገድ እድገቶች ቢኖሩም፣ በቅርብ ጊዜ የተከሰቱት ግጭቶች፣ ወረርሽኞች እና የአየር ንብረት ለውጥ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በልማት ውስጥ የተገኘውን ውጤት በተመለከተ ለስጋት ማጋለጣቸውን የስብሰባው አዘጋጆች ገልጸው፣ እነዚህ ተግዳሮቶች በቀጣዩ ትውልድ ላይ ተፅዕኖ ስለሚኖራቸው፣ የዛሬው ወጣት የተሻለ እና በቂ ምግብ ለማቅረብ እንዲችሉ ማብቃት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
የአምስት ቀናት ውይይት
ከአራቱም የዓለማችን ማዕዘናት ስብሰባውን በመካፈል ላይ የሚገኙት ወጣቶች፣ ገበሬዎች፣ አነስተኛ የምግብ ምርት አምራቾች፣ ቀደምት ነዋሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የግብርና ባለሀብቶች እና የሳይንስ ጠበብት ተገናኝተው በአምስት ቀናት ውስጥ በጋራ ተወያይተው፣ የምግብ ዋስትና ሚዛንን በመጠበቅ፣ ማንንም ወደ ጎን ሳያደርግ ለሁሉ ሰው የሚበቃ የተሻለ ምግብ የማግኘት ግብ ያላቸው መሆኑን የስብሰባው አስተባባሪዎች ገልጸዋል።
"ጤናማ የአመጋገብ ዘይቤ እና ጤናማ ምድር"
ለሁለተኛው የስብሰባ መድረክ የተመረጠው ጭብጥ "ጤናማ የአመጋገብ ዘይቤ እና ጤናማ ምድር” የሚል እንደሆነ የገለጹት አስተባባሪዎቹ፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ የተመጣጠነ ምግብ እና በጤናማ የአመጋገብ ዘይቤ መካከል ያለውን ግንዛቤ በማሳደግ ወጣቶችን ማበረታታት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። የውይይት መድረኩ ባለሥልጣናት፣ የዓለም አቀፍ እና የግል አካላት፣ የልማት ባንኮች እና ለጋሽ ድርጅቶች እጅ ለ እጅ ተያይዘው፣ በገንዘብ ድጋፍ ዕድሎች ላይ እንዲወያዩ ማድረግ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ተነግሯል። ውይይቱ በመጨረሻም የሳይንስ እና ኢኖቬሽን መድረክ፣ የምግብ ስርዓታቶችን ለመለወጥ የሚያስችሉ ሳይንሳዊ እና ቴክኖሎጂያዊ ፈጠራ ወሳኝ ሚናን በማቅረብ ዕድገቶችን፣ ተያያዥ ዕድሎችን እና አደጋዎችን በመዳሰስ ቀልጣፋ፣ አካታች፣ ቋሚ እና ዘላቂ የግብርና-ምርት ሥርዓቶችን ለመገንባት ያለመ መሆኑ ታውቋል።