ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ “ንጉሡ ክርስቶስ ለእኛ ያለንን ፍቅር በመስቀሉ አሳይቶናል!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ኅዳር 10 እና 11/2015 ዓ. ም. የወላጆቻቸው የትውልድ ከተማ የሆነችው አስቲን ጎብኝተዋል። በከተማው ካቴድራል ተገኝተው በላቲን ሥርዓተ አምልኮ የቀን አቆጣጠር መሠረት እሁድ ኅዳር 11/2015 ዓ. ም. በተከበረው ክርስቶስ የዓለም ንጉሥ ዓመታዊ በዓል ላይ ተገኝተው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን መርተዋል። ቅዱስነታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ላይ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን እግዚአብሔር በመስቀል ላይ የገለጠልንን ፍቅር በማስታወስ፣ ምዕመናን በእምነት በርትተው እግዚአብሔርን እና ባልንጀራን እንዲያገለግሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ያለፈው ቅዳሜ ኅዳር 10/2015 ዓ. ም. የሰሜን ጣሊያን ከተማ ወደ ሆነች አስቲ የተጓዙት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ወደ ከተማዋ ሲደርሱ የክብር አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን በመቀጠልም ሁለት የአጎታቸውን ልጆች ጨምሮ ዛሬም በዚያ አካባቢ የሚኖሩ የቤተሰብ አባላትን ጎብኝተዋል። ቅዱስነታቸው ወደ አካባቢው ያደረጉት ጉብኝት ከቤተሰብ ሐረጋቸው ጋር ለማግኘት ዕድል የሰጣቸው መሆኑን አስረድተዋል።

የላቲን ሥርዓተ አምልኮ የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ ካቶሊካዊ ምዕመናን ዘንድ እሑድ ኅዳር 11/2015 ዓ. ም. በተከበረው የክርስቶስ ንጉሥ በዓል ዕለት ከሉቃ. 23: 35 – 43 ተወስዶ የተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል እኛም ወደ እምነታችን መሠረት ተመልሰን በመስቀል ላይ የተሰቀለውን እና በሞቱ የዘለዓለምን ሕይወት የሰጠንን ኢየሱስ ክርስቶስን እንድንመለከት አድርጎናል ብለዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰቀለበት መስቀል ላይ “ይህ የአይሁድ ንጉሥ ነው” የሚለውን ምልክት ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ንጉሥ የሚለው ቃል ከንግሥና ጋር የተገናኘ ግርማ እና ኃይል የሚያስገነዝብ ቢሆንም በኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ላይ የተመለከተው ጽሑፍ ግን አገልጋይ በመሆን በስልጣን ላይ ባሉት ሰዎች መገደሉን የሚያመላክት መሆኑን አስረድተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማከልም በምስማር እና በእሾህ ቢወጋም፣ ልብሶቹን ቢገፈፍም ኢየሱስ ክርስቶስ በፍቅሩ ብዛት ከዙፋኑ በመስቀል ላይ ሆኖ ሕዝቡን በቃላት ሳያስተምር፣ እንደ መምህር እጆቹን ሳያነሳ፣ በማንም ላይ ጣቱን ሳይቀስር የፍቅር እጆቹን  ለሁሉ በመዘርጋት ራሱን ንጉሣችን አድርጎ ማቅረቡን አስረድተዋል።

እግዚአብሔር ሁሉንም በፍቅር ያቅፋል!

“ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሣችን፣ የዓለም ሁሉ ንጉሥ ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እርሱ ሩቅ መንገድ በመጓዝ በሰው ልጆች ጥልቅ የጥላቻና የብቸኝነት ጉድጓድ ውስጥ የገባው ለእያንዳንዱ ሕይወት ብርሃንን ለማምጣት እና ሁሉንም ዓይነት እውነታን ለመቀበል እንደሆነ ገልጸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን እና ሕይወቱን ለአገልግሎት ሙሉ በሙሉ በመስጠቱ እና የእግዚአብሔር ፍቅር ለእያንዳንዳችን ቅርብ መሆኑን በተግባር የገለጸ መሆኑን አስረድተዋል። "ምስጋናችንን የምናቀርብለት ንጉሥቻችን ይህ ነው!" ብለው፣ በማከልም “የዓለም ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የሕይወታችንም ንጉሥ ነው ወይ?” ብለን እራሳችንን መጠየቅ መልካም እንደሆነ ገልጸዋል። “ንጉሥነቱን የምንረዳው ወደ እቅፉ ስንገባ ብቻ ነው!” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ እግዚአብሔር ወደዚህ ጽንፍ የሄደው፣ በመስቀል ላይ የተሰቀለው፣ ከእርሱ ብንርቅም በክንዶቹ ያቀፈን ስለሚያፈቅረን መሆኑን አስረድተው፣ በመስቀል ላይ ስቃዩ ሞታችንን፣ ሕመማችንን፣ ድህነታችንን እና ድክመቶቻችንን እርሱ መቀበሉን አስረድተዋል።

የእግዚአብሔርን ፍቅር መቀበል

ለእኛ ሲል የተሰቀለውን፣ የፍቅር እጆቹን የዘረጋልንን ኢየሱስ ክርስቶስ መመልከት ይኖርብናል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ የምንገኝበት ሕይወት፣ ታሪካችን ወይም ውድቀታችን ምን ያህል ቢሆንም፣ ፍቅሩን በልባችን ተቀብለን ሕይወታችንን እንድንለውጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘወትር የሚጋብዘን መሆኑን አስረድተዋል። በግድ ሳይጫነን በምርጫ ለሚያቀርብልን የዋህ ፍቅሩ የምንገዛ ከሆነ በሕይወት እንድንነግሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ዕድል የሰጠን መሆኑን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ይቅርታ የሚገኝበት፣ ራሳችንን ችለን እንድንቆም የሚያስችለን እና ክብራችንን የሚመልስ መሆኑን አስረድተዋል።

“የእግዚአብሔርን ፍቅር ከተቀበልን ከራስ ወዳድነት፣ ከኃጢአት እና ከጭንቀት ባርነት ነፃ መውጣት እንችላለን” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ የኢየሱስን ፍቅር የተቀበለው እና በጎኑ የተሰቀለው ወንጀለኛ በመንግሥቱ እንዲያስታውሰው በለመነው ጊዜ፣ ኢየሱስ ክርስቶስም “ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ!” ብሎት ማረጋገጡን አስታውሰዋል። “ኢየሱስ ክርስቶስ ከእኛ የሚፈልገው ይህን ነው!” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ይህን በማድረግ፣“በሰማያት ያለው ንጉሣችን ኃያል እና የቅርብ አምላክ እንደሆነ፣ ሩኅሩኅ እና እጆቹ ከፍቶ የሚያጽናናን እና የሚንከባከቡን አምላክ መሆኑን እንገነዘባለን” ብለዋል።

ቆሞ ተመልካች ወይስ ተሳታፊዎች?

በቅዱስ ወንጌል ላይ የተገለጹ የተለያዩ አስተያየቶች መኖራቸውን የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሁለት መንገዶች መኖራቸውን ገልጸው፣ አንደኛው መንገድ ኢየሱስ ክርስቶስን በመስቀል ሲሰቅሉት ቆሞ የተመለከቱበት፣ በሐዘን ውስጥ የወደቁበት፣ ወደ ፍርድ እንዲቀርብ በማለት በግዴለሽነት የተመለከቱበት፣ የሕዝብ መሪዎች እና ወታደሮች የሚገኙበት፣ ከኢየሱስ ጋር ከተሰቀሉት ወንጀለኞች መካከል "ራስህን አድን!" እያለ የተሳለቀበት መንገድ ሲሆን፣ ሁለተኛው መንገድ ቆመው የሚመለክቱበት ሳይሆን ተሳታፊዎች የሚሆኑበት የመልካምነት መንገድ መሆኑን ገልጸው፣ “ኢየሱስ ሆይ! በመንግሥትህ አስታውሰኝ” በማለት የለመነው ወንጀለኛ እንዴት ያንን ምርጫ እንዳደረገ አስታውሰዋል።  በዚህ ልመና ወንጀለኛው የመጀመሪያው ቅዱስ ሊሆን መብቃቱን ገልጸው፣ ኢየሱስም ወንጀለኛውን ለዘለዓም ከጎኑ ማስቀመጡን አስረድተዋል። “ቅዱስ ወንጌል ስለ መልካሙ ወንጀለኛ የሚናገረን ለጥቅማችን ነው!” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ተመልካቾች ብቻ ሆነን እንዳንቀር እና ክፉ መንፈስን ተቃውመን እንድናሸንፈው ጋብዘውናል።

የመልካምነት ጎዳናን መከተል

“የእግዚአብሔርን ስም በመጥራት” የመልካምነት ጎዳናን መጀመር እንደምንችል የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ ወንጀለኛው ስህተቱን ተቀብሎ በእምነት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መመለሱን ቅዱስነታቸው አስታውሰው፣ “እኛስ ይህን የመሰለ እምነት አለን?” ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የምንቀርበው ከልባችን ጥልቅ በሆነ ታማኝነት እና ግልጽነት ነው?” በማለት ጠይቀዋል። “ለኢየሱስ ክርስቶስ ግልጽ ከሆንን፣ በእርሱ ሙሉ በሙሉ ከታመንን፣ ከራሳችን ወጥተን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በዚህ ዓለም የሚኖሩት ራስን ብቻ ለማዳን እንዳልሆነ ማስረዳት፣ ንጉሣቸው በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር እንዲታቀፉ መርዳት እንችላለን” ብለዋል።    

እጃችን ማጠፍ የለብንም

እሑድ ኅዳር 11/2015 ዓ. ም. በወላጆቻቸው የትውልድ ሥፍራ በሆነችው አስቲ ተገኝተው በከተማው ካቴድራል ውስጥ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ያቀረቡትን ቃለ ምዕዳን  ሲያጠቃልሉ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመስቀሉ ላይ ሆኖ እጆቹን ዘርግቶ ዘለዓለማዊ ፍቅሩን እንድንቀበል መጋበዙን አስታውሰው፣ ይህን የምናደርገው ፍቅሩን ተቀብለን ከሌሎች ጋር ለመካፈል እና የሚሰቃዩትን በዝምታ ሳንመለከት የዕርዳታ እጆቻችንን ለመዘርጋት መሆኑን አስረድተዋል። ዛሬ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ራቁቱን ሆኖ የሚታየው፣ እግዚአብሔርን ለመግለጽ እና ንጉሥነቱን ለማርጋገጥ፣ እርሱን ተመልክተን ራሳችንን የመመልከት ድፍረት እንዲኖረን እና አስተማማኝ የጸሎት መንገድ ለመከተል፣ ራስን አገልጋይ የምናደርግበትን ድፍረት ለማግኘት እና ከእርሱ ጋር ለዘለዓለም መንገሥ እንድንችል ለማድረግ መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስረድተዋል።

21 November 2022, 16:27