ፈልግ

በኢንዶኔዥያ ጃቫ ደሴት ላይ የደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ በኢንዶኔዥያ ጃቫ ደሴት ላይ የደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመላው ዓለም ሰላም እንዲሰፍን ጸሎት አቀረቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ዛሬ ረቡዕ ኅዳር 14/2015 ዓ. ም. ሳምንታዊውን የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ካቀረቡ በኋላ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን ባደረጉት ንግግር፣ በኢንዶኔዥያ ጃቫ ደሴት በደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ሰለባ የሆኑትን በጸሎታቸው አስታውሰዋል። ከዚህም በተጨማሪ ለዓለም ሰላም በተለይም በጦርነት ውስጥ የምትገኝ ዩክሬንን በጸሎታቸው አስታውሰዋል። በማከልም በኳታር በመካሄድ ላይ ያለው የእግር ኳስ የዓለም ዋንጫ ውድድር በሕዝቦች እና በአገሮች መካከል መግባባትን እና ወንድማማችነትን እንደሚያጎለብት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። በኡጋንዳ ውስጥ ብጽዕናው የታወጀለትን የቅዱስ ኮምቦኒ ማኅበር ሚስዮናዊ ካህን አባ ጁሴፔ አምብሮሶሊን እና ዓለም አቀፍ የዓሣ ሃብት ቀንን አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የተጎዱትን በጸሎት አስታውሰዋል

ቅዱስነታቸው በዛሬው ዕለት ባቀረቡት ሳምንታዊ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ማጠቃለያ ላይ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሰዎችን በማሰብ ጸሎታቸውን አቅርበዋል። በዚህ ሳምንት ውስጥ በኢንዶኔዥያ ጃቫ ደሴት ላይ በደረሰው ኃይለኛ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ከመቶ በላይ ሰዎች መሞታቸውንና በርካቶችም መቁሰላቸውን በማስታወስ የአደጋው ሰለባ ለሆኑት ሰዎች ያላቸውን ቅርበት ገልጸዋል። አደጋው ባደረሰው ውድመት ወደ 13 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸው ሲነግር፣ የነፍስ አድን ሠራተኞች ለተጎጂዎቹ ዕርዳታን ለማድረስ ጥረት ላይ መሆናቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው ለምዕመናኑ ባደረጉት ንግግር በአደጋው የሞቱትን እና ጉዳት የደረሰባቸውን በሙሉ በጸሎት እንደሚያስታውሷቸው ገልጸዋል።

የኳታሩ የዓለም ዋንጫ ውድድር

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቀጥለውም በኳታር እየተካሄደ ያለውን የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር በማስታወስ ውድድሩን በሥፍራው ተገኝተው በመከታተል ላይ ለሚገኙት አትሌቶች፣ አድናቂዎች እና ተመልካቾች በሙሉ ሰላምታቸውን አቅርበዋል። "ይህ ጠቃሚ ክስተት በአገራት መካከል የእርስ በርስ ግንኙነትን እና መተሳሰብን የሚያሳድግ፣ በሕዝቦች መካከል ወንድማማችነትን እና ሰላምን የሚያጎለብትበት ይሁን" በማለት መልካምን ተመኝተዋል።

በዩክሬን እና በዓለም ሁሉ ሰላም እንዲሆን

ግጭቶች ቆመው በዓለም ዙሪያ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም ሰው እንዲጸልይ ጠይቀው፣ በዚህ ወቅት በአስከፊ ስቃይ ውስጥ የሚገኘውን የዩክሬን ሕዝብ ጠቅሰዋል። በማከልም እ. አ. አ. ከ1932-1933 ዓ. ም. ስታሊን ባቀነባበረው ሰው ሠራሽ ረሃብ በሆሎዶሞር ሕዝቦች ላይ የተፈጸመበትን እና ባለፈው ቅዳሜ የተከበረውን አስከፊ የዘር ማጥፋት ወንጀል የተካሄደበት ቀን በማስታወስ፣ የወንጀሉ ሰለባዎችን፣ ለመላው ዩክሬናውያን፣ ለሕጻናት፣ ለሴቶች እና ለአረጋውያን፣ ዛሬ በግፍ ለሚሰቃዩት በሙሉ እንጸልይ።" ብለዋል።

ብፁዕ አባ ጁሴፔ አምብሮሶሊ

ያለፈው እሑድ ኅዳር 11/2015 ዓ. ም. በኡጋንዳ ካሎንጎ ሀገረ ስብከት ብጽዕናቸው የታወጀላቸውን የቅዱስ ኮምቦኒ ማኅበር ሚሲዮናዊ ካኅን እና ዶክተር አባ ጁሴፔ አምብሮሶሊን ያታወሱት ቅዱስነታቸው፣ በጣሊያን ኮሞ ሀገረ ስብከት ውስጥ የተወለዱት ብጹዕ አባ አምብሮሶሊ እ. አ. አ በ1987 በኡጋንዳ ማረፋቸውን አስታውሰዋል። ለአካባቢው ሕዝብ የሕክምና ዕርዳታን እየሰጡ የክርስቶስን መልክ ላዩባቸው ሕሙማን ሲሉ መሰዋታቸውን ገልጸው፣ "ምስክርነታቸው በጉዞ ላይ በምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብቁዎች እንድንሆን ይርዳን!” በማለት ንግግራቸውን ደምድመዋል። 

23 November 2022, 16:01