ፈልግ

ቅዱስነታቸው የቀድሞ ር. ሊ. ጳ. ቤኔዲክቶስ 16ኛን በሚኖሩበት ገዳም ሄደው ጠይቀዋል ቅዱስነታቸው የቀድሞ ር. ሊ. ጳ. ቤኔዲክቶስ 16ኛን በሚኖሩበት ገዳም ሄደው ጠይቀዋል  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ የቀድሞ ር. ሊ. ጳ. ቤነዲክቶስ 16ኛን በጸሎት እንድናስታውሳቸው ጠየቁ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ ታኅሳስ 19/2015 ዓ. ም. ያባቀረቡትን ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ከማጠቃለላቸው አስቀድመው ባስተላለፉት መልዕክት፣ ዕድሜያቸው 95 ዓመት የሆናቸው የቀድሞ ር. ሊ. ጳ. ቤነዲክቶስ 16ኛ በጤና መጓደል ምክንያት ድካም እየተሰማቸው መምጣቱን ለምዕመናኑ ገልጸው፣ ለቤተ ክርስቲያን የሚያቀርቡትን የፍቅር ምስክርነት እስከ ፍጻሜው እንዲያደርሱት የእግዚአብሔርን ድጋፍ በጸሎት እንድንጠይቅ አደራ ብለዋል። የቫቲካን መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ማቴዎ ብሩኒ በበኩላቸው፣ የቀድሞ ር. ሊ. ጳ. ቤነዲክቶስ 16ኛ በእድሜ ምክንያት ባለፉት ጥቂት ሰዓታት ውስጥ የጤና ሁኔታቸው አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን አስታውቀው፣ በአሁኑ ጊዜ ዶክተሮች ሳያቋርጡ ክትትል እያደረጉላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ለመከታተል  በጳውሎስ 6ኛ የስብሰባ አዳራሽ ለተገኙት የጣሊያን ምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክት፣ ቤተ ክርስቲያንን ያለማቋርጥ በማገልገል ላይ የሚገኙትን የቀድሞ ር. ሊ. ጳ. ቤነዲክቶስ 16ኛን በጸሎት እንዲያስታውሱ ጠይቀዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን መልዕክታቸውን @Pontifex በተሰኘው የትዊተር ማኅበራዊ መገናኛ ገጻቸው ላይ ለመላው ካቶሊካዊ ምዕመናን በ9 ቋንቋዎች አስተላልፈዋል።

95ኛ  የልደት በዓላቸውን ሚያዝያ 8/2014 ዓ. ም. ያከበሩት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ የጤና ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን የቫቲካን መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ማቴዎ ብሩን አረጋግጠው፣ ባለፉት ሰዓታት ውስጥ የጤናቸው ሁኔታ እየተባባሰ የመጣ ቢሆንም ከዶክተሮች በሚሰጥ ድጋፍ በአሁኑ ጊዜ ቅዱስነታቸው በመልካም የጤና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል። የመግለጫ ክፍሉ ዳይሬክተር አቶ ማቴዎ ብሩን በማከልም፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ረቡዕ ታኅሳስ 19/2015 ዓ. ም. ካቀረቡት ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ቀጥለው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛን በሚኖሩበት ማተር ኤክሌሲያ ገዳም ጎብኝተው መመለሳቸውን ገልጸው፣ ምዕመናኑ በጸሎት ከእርሳቸው ጋር እንዲተባበሩ ጠይቀዋል። 

‘ማተር ኤክሌሲያ’ ገዳም

የቀድሞ ር. ሊ. ጳ. ቤነዲክቶስ 16ኛ የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ መሪነት ሥልጣናቸውን ካስረከቡበት ከየካቲት 4/2005 ዓ. ም. በኋላ ጥቂት ወራትን እንዳስቆጠሩ፣ እርሳቸው በመረጡት “ማተር ኤክሌሲያ” ገዳም ኑሮ መጀመራቸው ይታወሳል። በገዳሙ ውስጥ ባሳለፏቸው ዓመታት በሙሉ በገዳሙ ደናግል እና በግል ጸሐፊያቸው ሞንሲኞር ጆርጅ ጋንስዌትን በኩል ድጋፍ ሲደረግላቸው መቆየቱ ይታወሳል። ር. ሊ. ጳ. ቤነዲክቶስ 16ኛ ከገዳሙ አባላት እና ሐኪሞች በሚደረግላቸው እንክብካቤ እየታገዙ ጸሎትን፣ መንፈሳዊ ዜማን እና ንባባትን በማዘውተር፣ ያሳለፏቸው ዓመታትን በተመለከተ ለገዳሙ አባላት ሲመሰክሩ ቆይተዋል።

በር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ እና በር. ሊ. ጳ. ቤኔዲክቶስ 16ኛ መካከል ያለው ግንኙነት

ከር. ሊ. ጳ. ቤኔዲክቶስ 16ኛ ጋር ስላላቸው ግንኙነት ብዙ ጊዜ የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ር. ሊ. ጳ ቤነዲክቶስ 16ኛ የክህነታቸው 70ኛ ዓመት ባከበሩበት ወቅት ማለትም ሰኔ 22/2013 ዓ. ም. ባቀረቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ላይ “አባት” እና “ወንድም” ብለው መጥራታቸው ይታወሳል። በቫቲካን ውስጥ ወደሚገኝ ገዳም “ማተር ኤክሌሲያ” ገዳም ከመግባታቸው አስቀድሞ ይኖሩበት ከነበረው ካስተል ጋንዶልፎ የብጹዓን ጳጳሳት መኖሪያ በመሄድ መጎብኘታቸውም ይታወሳል። ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከዚህም በተጨማሪ በየዓመቱ በሚከበሩ የብርሃነ ልደቱ እና የብርሃነ ትንሳኤው በዓላት ወቅት እንዲሁም አዳዲስ ካርዲናሎች በሚሰየሙበት ጊዜ ሁሉ ር. ሊ. ጳ. ቤኔዲክቶስ 16ኛን ሲጎበኟቸው እና ሲጠይቋቸው ቆይተዋል።

የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ድጋፍ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ ታኅሳስ 19/2015 ዓ. ም. ከጠየቋቸው በኋላ በርካታ የድጋፍ እና የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክቶች ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ መድረሳቸው ታውቋል። ከእነዚህ መልዕክቶች መካከል ከጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ከብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ የተላከላቸው መልዕክት አንዱ ሲሆን፣ የቦሎኛ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ "የሕመም ወቅት” ባሉት መልዕክታቸው፣ የጣሊያን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት በጸሎት ከጎናቸው መሆናቸውን ገልጸውላቸዋል። ሕመም እና ስቃይ ቢበረታባቸውም ከእግዚአብሔር እጅ ውጭ አለመሆኑን ገልጸው፣ እነዚያ እጆቹ የፈጠሩን፣ የሚደግፉን፣ ወሰን በሌለው ታማኝ ፍቅሩ በጉዞአችን የሚመሩን ናቸው” በማለት ተናግረዋል። የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ ላይ፣  “በመስቀል ላይ ከተሰቀለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የሚያደርጉትን የቤተ ክርስቲያን ጉዞ በጸሎትና በማሰላሰል ወደ ፊት እንቀጥላለን” በማለት ለመላው ማኅበረ ቅዱሳን እና ኅብረተሰብ ጠንካራ መልዕክት አስተላልፈዋል።

29 December 2022, 16:36