ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የጽንሰተ ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ ለሰላም ጸለዩ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ቅዱስነታቸው ዓርብ ኅዳር 28/2016 ዓ. ም. የተከበረው የጽንሰተ ማርያም ዓመታዊ በዓል ዕለትን ምክንያት በማድረግ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ውስጥ ካቀረቡት ጸሎት ቀጥለው፥ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ሐውልት ወደሚገኝበት “ፒያሳ ዲ ስፓኛ” በመሄድ ለዓለም ሰላም በተለይም ለዩክሬን እና ለቅድስት ሀገር፥ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እንዲያወርድ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት በጸሎት ለምነዋል።
የሮም ከተማ ነዋሪዎች ጠባቂ ለሆነች እመቤታችን ማርያም የቀረበ የአበባ ስጦታ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዓርብ ከሰዓት በኋላ በቅድሚያ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም በታነጸው ባዚሊካ ውስጥ ተገኝተው ሦስት ወርቅማ ጽጌረዳዎችን፣ የሮም ሕዝብ ጠባቂ እመቤታችን ማርያም ጥንታዊ ምስል ሥር አስቀምጠዋል። ይህ ጥንታዊ ምስል ከፍተኛ ተምሳሌታዊ ምልክት መሆኑን ከገለጹት ሦስት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መካከል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አንዱ ሲሆኑ፥ የመጨረሻው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ አምስተኛ እንደ ጎርጎሮሳዊው በ1613 ዓ. ም. እንደ ነበር ይታወሳል። የርዕሠ ኪቃነ ጳጳሳትን ቡራኬ የሚያመለክተው የዚህ ስጦታ ልማድ ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ ሲከናወን የቆየ ሲሆን፥ ምልክቱም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከኢየሱስ ክርስቶስ እናት ቅድስት ድንግል ማርያም ጋር ያላቸውን ጥልቅ ትስስር የሚገልጽ ነው።
በፒያሳ ዲ ስፓኛ የተከናወነው ሥነ-ሥርዓት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የሮም ከተማ ነዋሪዎች ጠባቂ በሆነች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ውስጥ ካቀረቡት ጸሎት በኋላ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በየዓመቱ የሚቀርበውን ጸሎት ለማድረስ ወደ ፒያሳ ዲ ስፓኛ አቅንተዋል። 39 ጫማ ከፍታ ባለው በጽንሰተ ማርያም መንፈሳዊ ሐውልት ፊት ቀርበው የአበባ ጉንጉን ካስቀመጡ በኋላ ለዓለም ሰላም ባቀረቡት ጸሎት፥ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለማችን ሰላምን እንዲያወርድ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ለምነዋል።
የእመቤታችን አስተዋይነት እና የማያቋርጥ አለኝታነት መጽናናትን እና ተስፋን ይሰጠናል
የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልባዊ እና የማያቋርጥ አለኝታነት ስለሚሰጠን መጽናናት እና ተስፋ ምስጋናቸውን በማቅረብ ጸሎታቸውን የጀመሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ማንነት እና የእርሷ መኖር፥ ክፋት የመጀመሪያም ሆነ የመጨረሻ ቃል እንደሌለው ያስታውሰናል” ብለው፥ ዕጣ ፈንታችን ሞት ሳይሆን ሕይወት፣ ጥላቻ ሳይሆን ወንድማማችነት፣ ግጭት ሳይሆን ስምምነት፣ ጦርነት ሳይሆን ሰላም ነው” ብለዋል።
የዩክሬን፣ የፍልስጤም እና የእስራኤል ሕዝቦች አደራን ለማርያም መስጠት
ቅዱስነታቸው በመቀጠልም፥ “በግፍ፣ በድህነት እና በጦርነት የሚሰቃዩት እና የተጨቆኑ ሕዝቦች በሙሉ፥ በተለይም በስቃይ ውስጥ የሚገኝ የዩክሬን ሕዝብ እና በግፍ አዙሪት የተዘፈቁትን የፍልስጤም እና የእስራኤል ሕዝቦችን በመጥቀስ፥ የእነዚህ አገራት የምሕረት አደራን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሰጥተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ልጆቻቸው በጦርነት እና በሽብር የሞቱባቸውን፣ በተስፋ አስቆራጭ የስደት ጉዞ ላይ የሚገኙትን፣ ልጆቻቸውን ከጎጂ ሱስ ለመታደግ የሚጥሩትን፣ በከባድ ሕመም ውስጥ የሚገኙ ልጆቻቸውን በመንከባከብ ላይ የሚገኙትን እና ሐዘን ውስጥ የሚገኙትን በርካታ እናቶችን አስታውሰዋል።
ላዘኑት እናቶች እና ለጾታዊ ጥቃት ሰለባዎች ጸልየዋል
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም፣ የጥቃት ሰለባ የሆኑት ሴቶችን በሙሉ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንድትጠብቃቸው፥ እንባዎቻቸውን እና የሚወዷቸውን ዘመዶች እንባ እንድታብስላቸው አደራ ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማጠቃለያቸውም፥ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም “የመለወጥን መንገድ እንድታሳይ ተማጽነው፥ “ያለ ይቅርታ ሰላም የለም፤ ያለ ንስሐም ይቅርታ የለም” በማለት አስገንዝበዋል።
“ከእኔ ጀምሮ ሁሉም ሰው፥ ‘የሰዎች ልብ ከተቀየረ ዓለም ይለወጣል!’ ሊል ይገባል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ነገር ግን የሰውን ልብ በጸጋው ሊለውጠው የሚችል እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ ገልጸው፥ “ማርያም ሆይ! አንቺ ከመጀመሪያው አንስቶ በእግዚአብሔር ጸጋ የተጠመቅሽ፥ ለኛ የሞተው እና ከሞት የተነሣው፣ በሥጋ የገለጥሽው እና ሁልጊዜም የምትጠቁሚን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ነው” በማለት፥ “የእያንዳንዱ ሰው እና የዓለም መዳኛ የሆንክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! የፍቅር፣ የፍትህ እና የሰላም መንግሥትህ ይምጣ! አሜን” በማለት ጸሎታቸውን ደምድመዋል።