ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከኮንሰርቱ አቅራቢዎች ጋር የሰላምታ ልውውጥ ሲያደርጉ  ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከኮንሰርቱ አቅራቢዎች ጋር የሰላምታ ልውውጥ ሲያደርጉ   (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “ድሆች የተካፈሉት ኮንሰርት የክርስቲያናዊ መልዕክት ትርጉምን ይገልጻል"

በሮም ውስጥ የሚገኙ ወደ 3,000 የሚጠጉ መጠለያ የሌላቸው፣ ድሆች እና ስደተኞች በክብር እንግድነት የተገኙበት ዓመታዊ ኮንሰርት ዓርብ ታኅሳስ 5/2016 ዓ. ም. በቫቲካን ቀርቧል። በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ የቀረበው የኮንሰርት ዝግጅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም ከእንግዶቹ ጋር በመሆን ተካፍለውታል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለአራተኛ ጊዜ የተዘጋጀውን ይህን ዓመታዊ የዜማ ኮንሰርት ያስተባባረው፥ በቫቲካን የሚገኝ የፍቅር አገልግሎት መምሪያ ጽሕፈት ቤት እንደሆነ ታውቋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን የቸርነት ሥራ አገልግሎትን በገንዘብ ለመርዳት በማሰብ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2015 ዓ. ም. ለመጀመሪያ ጊዜ ተዘጋጅቶ የነበረው ኮንሰርቱ፥ የእራት ግብዣን ጨምሮ አስፈላጊ ዕቃዎችን ማከፋፈልን እንደሚያካትት ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የኮንሰቱን አዘጋጆችን ጨምሮ የዝግጅቱ መሪዎች የሆኑት አቡነ ማርኮ ፍሪሲና እና ወ/ሮ ስፔራንሳ ስካፑቺን ዓርብ ታኅሳስ 5/2016 ዓ. ም. ጠዋት በቫቲካን ተቀብለው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የመጋራት እና የወንድማማችነት ጊዜ ነበር

አዘጋጆቹን በሙሉ፥ “በርካታ ግለ ሰቦችን በማሳተፍ በሺዎች ለሚቆጠሩ ድሆች ነፃ የዜማ ኮንሰርት ዝግጅት ማቅረብ ስለቻላችሁ አመሰግንሃችኋለሁ” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በዝግጅቱ አማካይነት ሰዎች እርስ በርስ እንዲገናኙ እና ያላቸውን እንዲጋሩ ማድረጋቸውን አስታውሰው፥ “ይህም ከብርሃነ ልደቱ መልዕክት ጋር የሚስማማ ነው” በማለት ተናግረዋል። “በዜማ አማካነት በሌሎች ሰዎች መካከል ስምምነትን መፍጠር ነው...” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ አዘጋጆቹ በዚህ በዜማ ኮንሰርት አማካይነት በመካከላቸው አንድነትን መፍጠር መቻላቸውን አስረድተዋል።

"ለድሆች እና ከድሆች ጋር!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “የዜማ ኮንሰርቱ ለድሆች ብቻ ሳይሆን ከሁሉም በላይ ከድሆች ጋር ነው” በማለት አስረድተው፥ “ከድሆች ጋር” የሚለው ቁልፍ ሃሳብ፥ የክርስቲያን መልዕክት ትክክለኛ ትርጉም የሚገኝበት ልዩ ክርስቲያናዊ ጠቀሜታ ያለው እንደሆነ እና በእርግጥም እግዚአብሔር እኛን በመምሰል ከእኛ ጋር ለመኖር መምጣቱን እንደሚገልጽ አስረድተዋል።

“ይህ ምስጢር ዘወትር ያስደንቀናል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ልንረዳው የምንችለው ከሌሎች ሰዎች ጋር ስንገናኝ፣ በመካከላችንም መስጠትን እና መቀበልን ስንለማመድ እና ያለንን በመጋራት የወንድማማችነት እና የእህትማማችነት ፍቅር ስንፈጥር እንደሆነ ነው በማለት አስረድተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ሙዚቃ፣ ልዩ ልዩ ቀለማት ያሏቸው መብራቶች እና ማስዋቢያዎች ብቻውን በቂ አይደሉም፥ ነገር ግን መጸለይ ያስፈልገናል” በማለት በቦታው የተገኙትን በጸሎት እንዲበረቱ አደራ ብለዋል።

የኮንሰርቱ መርሃ ግብር

"ለድሆች እና ከድሆች ጋር" በሚል ርዕሥ የቀረበው ኮንሰርቱ፥ “ኦፔራ ኖቫ” በተሰኘ ለትርፍ ያልቆመ ድርጅት እና በሮማ ሀገረ ስብከት መዘምራን የተዘጋጀ ሲሆን፥ የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉትም የቫቲካን ከተማ አስተዳደር ከቫቲካን የፍቅር አገልግሎት መምሪያ ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር እንደሆነ ታውቋል።

የዜማ ኮንሰርቱ መሪዎች አቡነ ማርኮ ፍሪሲና እና ወ/ሮ ስፔራንሳ ስካፑቺ፥ በሮም የኦፔራ ቲያትር ኦርኬስትራን እና የሮም ሀገረ ስብከት መዘምራንን በየተራ መርተዋል። እንደ ከዚህ በቀደሙ ዓመታት 200 አባላት ያሉት የሮም ሀገረ ስብከት መዘምራን ከኦርኬስትራው ጀርባ በመሆን የተለያዩ ዜማዎችን አቅርበዋል።

ማሪያ ግራዚያ ስኪያቮ የተባሉት የሶፕራኖ ድምጽ ዘማሪ እና ደቡብ አፍሪካዊው የቴኖር ድምጽ ዘማሪ ሌቪ ሴክጋፓኔ ነጠላ ዝማሬያቸውን አቅርበዋል። የኮንሰርቱ መርሃ ግብር በሞዛርት፣ በሮሲኒ፣ በቻይኮቭስኪ እና በቤትሆቨን የተዘጋጁ ድንቅ ሥራዎችን ያካተተ ሲሆን፥ በዝግጅቱ ላይ ተወዳጅነት ያላቸው በርካታ የብርሃነ ልደቱ ወቅት ዜማዎች ቀርበዋል።

በኮንሰርቱ ማብቂያ ላይ የተሰበሰቡት የነጻ ፈቃድ ልገሳዎች፥ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮ የበጎ አድራጎት ዕቅዶች የሚውሉ መሆናቸው ታውቋል።

 

16 December 2023, 15:24