ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የመጀመሪያውን የዓለም የሕፃናት ቀን ይፋ አደረጉ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ዓለም አቀፍ የሀገረ ስብከት ወጣቶች ቀንን ተከትሎ በሮም ግንቦት 17 እና 18/2016 ዓ. ም. ዓለም አቀፍ የሕጻናት ቀን የሚከበር መሆኑን የጽንሰተ ማርያም ዓመታዊ በዓል በተከበረበት ዕለት ዓርብ ኅዳር 28/2016 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በደስታ አስታውቀዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባደረጉት ንግግር፥ “ተነሳሽነቱ አሁን በማደግ ላይ ለሚገኙት ሕጻናት ምን ዓይነት ዓለምን መተው እንፈልጋለን ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ይሰጣል” ብለው፥ "እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕጻናትን ማዕከል አድርገን ልንንከባከባቸው እንፈልጋለን" ብለዋል።
ለበዓሉ የባሕል እና የትምህርት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ድጋፍ ይሰጣል
ከመላው ዓለም በሺዎች የሚቆጠሩ ወንድ እና ሴት ሕጻናት ወደ ሮም መጥተው የሚሳተፉበት ይህ ዝግጅት በቅድስት መንበር የባሕልና የትምህርት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት እንደሚደገፍ ታውቋል።
ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ ከዚህ በፊት በያዝነው ኅዳር ወር መጀመሪያ አካባቢ፥ “ከወንድ እና ሴት ሕጻናት እንማር” በሚል ርዕሥ፥ ከዓለም ዙሪያ የመጡ 7,500 ሕፃናት በቫቲካን በሚገኘው ጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ውስጥ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ለተገናኙበት ዝግጅት የበኩሉን ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል። ቫቲካን ውስጥ በታላቅ የሙዚቃ ድግስ እና የምሥክርነት ሥነ-ሥርዓት ተካሂዶ ያለፈው ዝግጅቱ፥ በመጭው ግንቦት ወር ለሚከበረው ዓለም አቀፍ የሕጻናት ቀን ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል ተነግሯል።
በ9 ዓመቱ ሕጻን በአሌሳንድሮ የቀረበ ሃሳብ ነው
በቫቲካን ሚዲያ በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን ከተካሄደው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ቀደም ብሎ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር በተደረገ ሁለተኛ ዙር የኢንትርኔት የሬዲዮ ዝግጅት ላይ፥ የሕጻናት ቀንም እንዲከበር በማለት የ9 ዓመቱ ሕጻን አሌሳንድሮ ሃሳብ አቅርቦ እንደ ነበር ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በወቅቱ በሰጡት አስተያየትም ሃሳቡን እንደወደዱት እና በአያቶች እንዲዘጋጅ ማድረግ እንደሚችሉ እና እንደሚያስቡበትም መናገራቸው ይታወሳል።