ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከካርዲናሎች ምክር ቤት አባላት ጋር መወያየታቸው ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የካርዲናሎች ምክር ቤቱ ውይይት፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዓለም አቀፍ የሥነ-መለኮት ኮሚሽን ጋር ኅዳር 20/2016 ዓ. ም. በተገኙበት ወቅት የቤተ ክርስቲያን አንስታይ ገጽታ አስመልክተው ባቀረቡት አስተያየት ላይ ያተኮረ እንደነበር ታውቋል።
ቅዱስነታቸው ከካርዲናሎች ምክር ቤት ጋር ባደረጉት ስብሰባ፥ “ቤተ ክርስቲያን አንስታይ ናት” በማለት ገልጸው፥ “አንስታይ ገጽታ ምን እንደ ሆነ ወይም የአንስታይነት ሥነ-መለኮት ምን እንደሆነ ካልተረዳን፥ የቤተ ክርስቲያን ማንነትንም አንረዳም” ብለው፥ ቤተ ክርስቲያንን ተባዕታይ አድርጎ መውሰድ ገና መፍትሄ ያላገኘ ትልቅ ኃጢአት ነው” ሲሉ ገልጸውታል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በኢየሱሳዊው የነገረ-መለኮቶ ምሁር ሃንስ ኡርስ ቮን ባልዳዛር ባቀረበው የሐዋርያው ጴጥሮስ የአገልጋይነት መርሕ እና ማርያማዊ ወይም ሚስጢራዊ መርሕ መካከል ያለውን ልዩነት ገልጸው፥ ማርያማዊ መርሕ ከሐዋርያው ጴጥሮስ የአገልግሎት መርሕ የበለጠ አስፈላጊ እንደሆነ እና ሙሽሪት ቤተ ክርስቲያን መኖሯን አስረድተዋል።
በሰኔ ወር የተካሄደው የካርዲናሎች ምክር ቤት ስብሰባ
የመጨረሻው የካርዲናሎች ምክር ቤት ስብሰባ ከሰኔ 19-20/2016 ዓ. ም. ድረስ የተካሄደ ሲሆን፥ በዚህ ወቅት ምክር ቤቱ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር የተለያዩ ርዕሠ ጉዳዮችን በመመልከት መወያየቱ ይታወሳል። የውይይቱ ርዕሦችም፥ በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት፣ “ወንጌልን ስበኩ” የሚለውን ሐዋርያዊ ደንብ በአገራት አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ተግባራዊ ማድረግ እና የሕፃናት ድኅንነት ጥበቃ ጳጳሳዊ ኮሚሽን ተግባር የሚሉት እንደሚገኙበት ይታወሳል። ከርዕሠ ጉዳዮች መካከል፥ በጥቅምት ወር በቫቲካን በተካሄደው የጳጳሳት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ውይይት የተካሄደበት የሲኖዶሳዊነት መሪ ቃልም የውይይቱ ዋና ነጥብ እንደ ነበር ይታወሳል።
አዲሱ የዘጠኝ ካርዲናሎች ምክር ቤት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የካቲት 28/2015 ዓ. ም. የካርዲናሎች ምክር ቤትን በሚከተሉ ዘጠኝ ካርዲናሎች “C9” በአዲስ መልክ ማዋቀራቸው ይታወሳል። የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ፥ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፣ የቫቲካን ከተማ ጳጳሳዊ ኮሚሽን ፕሬዝደንት እና የቫቲካን ከተማ አስተዳደር ርዕሠ መስተዳድር፥ ብጹዕ ካርዲናል ፌርናንዶ ቬርጌዝ አልዛጋ፣ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ የኪንሻሳ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ ቤሱንጉ፣ በሕንድ የቦምቤይ ከተማ ሊቀ ጳጳስ፥ ብጹዕ ካርዲናል ኦስዋልድ ግራሲያስ፣ በሰሜን አሜሪካ የቦስተን ከተማ ሊቀ ጳጳስ፥ ብጹዕ ካርዲናል ሴያን ፓትሪክ ኦማሌይ፣ በስፔን የባርሴሎና ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ሁዋን ሆሴ ኦሜላ ኦሜላ፣ በካናዳ የኪቤክ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ጄራልድ ላክሮክስ፣ በአውሮፓ የሉክሰምበርግ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክላውድ ሆሌሪች፣ በብራዚል የሳን ሳልቫዶር ደ ባሂያ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ሴርጆ ዳ ሮካ እንደሆኑ ይታወሳል።
ቅዱስነታቸው በተጨማሪም፥ በጣሊያን የክሬዚማ ሀገረ ስብከት ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ማርኮ ሜሊኖ የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ ሆነው እንዲያገለግሉ የመረጧቸው ሲሆን፥ አዲሱ የካርዲናሎች ምክር ቤት የመጀመሪያ ስብሰባውን ሚያዝያ 16/2015 ዓ. ም. አክሂዶ እንደ ነበር ይታወሳል።
የካርዲናሎች ምክር ቤት አመሠራረት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ፥ የካርዲናሎች ምክር ቤትን በመስከረም 18/2005 ዓ. ም. በማቋቋም፥ በዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር እንዲያግዟቸው እና በ “ሮማ ኩሪያ” ወይም በቅድስት መንበር በሚገኙ ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ውስጥ የሚደረገውን የማሻሻያ ዕቅድ እንዲያጠና ለምክር ቤቱ በአደራ መስጠታቸው ይታወሳል። የተሃድሶው ዕቅዱ በመጋቢት 10/2005 ዓ. ም. በታተመው እና “ወንጌልን ስበኩ” በሚለው አዲሱ ሐዋርያዊ ደንብ መጽደቁ ሲታውስ፥ ምክር ቤቱ “C9” የመጀመሪያ ስብሰባውን ጥቅምት 8/2006 ዓ. ም. ማካሄዱም ይታወሳል።